top of page
Search

እምነትህን ማንም እንዳይወስድብህ

Writer: Mulualem Getachew
Mulualem Getachew
3 hours ago
4 min read

ያለንበት ወቅት፤ በርግጥ ያለፉትም በየነበሩበት ዘመን አንዱ መለያ የእምነት ትግል ነው። የመርህ ትግል ነው። የፕሪንስፕል ትግል ነው።



በለጋነት ዘመኔ ከማይገቡኝ ጸሎቶች መካከል መዝሙረ ዳዊት አንዱ ነበር። ከተወሰኑት መዝሙራት ውጪ። ምክንያቱም ከክርስትናዬ ጋር የሚጋጭ እየመሰለኝ። ስለ ጠላት መደምሰስ፣ ስለ ክፉዎች ጥፋት፣ ስለ ሕጻናቶቻቸው ሁሉ በአለት መቀጥቀጥ ነው የሚያወራው። ክርስትናዊ ፍቅር እና ይቅር ባይነት ጋር ሲጋጭብኝ ብዙ ማስተባበያ ሁሉ አስቀምጥ ነበር።



የብሉይ መጽሐፍ ስለሆነ ነው፣ ስለ ሰዎች ሳይሆን ስለ ዳይብሎስነው የሚናገረው እያልኩኝ። ይሄ የኔ ችግር ብቻ አልነበረም።የተወሰኑ ቀደምት አባቶችም ችግር ሆኖ ወደ አሊጎሪ ትርጉም ውስጥ ገብተው ሕጻናት ማለት ጥቃቅን የሆኑ ኃጢአቶች ማለት ነው በሚል ለማስታረቅ ጥረት አድርገው ነበር። መዝሙረኛው ግን በእውነትም ስለ ሰዎች፣ መዝሙራቱም ስለ ሰው ልጆች ነበር የተናገሩት እንጂ ስለ ሰይጣን ወይም መናፍት አይደለም። የሰይጣንን ሃሳብ ስለተሸከሙ ሰዎች እንጂ።




የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው ብለን እንዳንተወው፤ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ ብዙዎች ሐዋሪያት ከመዝሙረ ዳዊት ብዙ ጠቅሰው አስተምረዋል። ከብሉይ ኪዳን መጽሐፎች ሁሉ መዝሙረ ዳዊት በአዲስ ኪዳን በብዛት የተጠቀሰ ነው። በዚህም ምክንያት የአዲስ ኪዳን ክፍል እስኪመስል ድረስ።



አሁን ግን ምንም ሳይከብደኝ፣ መዝሙረኛው በሚልበት የበቀልና የጥላቻ ስሜት ነው እነዛን መዝሙሮች የምላቸው። ለንባብ ለጸሎት የምጠቀማቸው።



መዝሙረኛው እነማንን ነው እንደዛ የሚለው? የግሉን ጠላቶች? የጠሉትን? በንግስናው ወይም በራሱ ባህሪ ወይም በሥጋዊ ፍላጎቱ የቀኑበትን?



በፍጹም። በጭራሽ። መዝሙረኛው የግል ጠላቶቹን በመዝሙሩ ሊያነሳ ቀርቶ ትዝ ብለውት ራሱ የሚያቅ አይመስልም።



መዝሙረኛው ጠላቶች የሚላቸው የእምነት ጠላቶችን ነው። “እግዚአብሔር አያድንህም!” ብለው የሚያምኑ፣ መዝሙረኛውን የመጥላታቸው ምንጭ ጽድቁ እና በእግዚአብሔር መታመኑ የሆነባቸውን፣ ለሌሎች “እግዚአብሔር ይታደጋል በመጨረሻም ይፈርዳል፣ እውነት ታሸንፋለች” ብሎ በመናገሩ የተገዳደሩትን፣ እስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለሆነ ብቻ (ያለሌላ ምክንያት) የጠሉትን ሰዎች ነው ጠላቶች የሚላቸው። ትንሣኤ በሌለው መደምሰስ እንዲጠፉ የሚለምነው። ምክንያቱም የእውነትን መሸነፍ፣ የሃይማኖትን አለመኖር፣ እግዚአብሔር የሚባል አምላክ የለም፣ የሚታደግ የለም የሚለው እምነታቸው እውነት እንደሆነ ለማሳየት የሚጥሩ እና ያንን ለማሳየት ምንም ለማድረግ የማይመለሱ ሰዎች ስለሆኑ ነበር ዳዊትም ሆነ ዘማሪዎቹ በእንባ ጭምር እግዚአብሔር በእነዚህ ላይ እንዲፈርድ የለመኑት።



ወዳጆች ሆይ ዛሬም ጠላቶቻችን እነዚህ ናቸው። ድሃ አደጉን የሚፈርድ የለም ብለው የሚበዘብዙ፣ ስደተኛውን የሚታደገው የለም ብለው የሚያሰቃዩ፣ ስልጣን አልባውን የሚደርስለት የለም ብለው የሚያፈናቅሉ፣ ግፋቸውን 'የእግዚአብሔርን አለመኖር' እንዲያሳይ አድርገው የሚሰሩ፣ በዚህም ኃይል እና ጉልበት ነው ይሄን ዓለም የሚያስተዳድረው ብለው ኃይል እና ጉልበት ለሌለው የሚሰብኩ፤ ተመልከቱ ግፈኛው፣ ተንኮለኛው፣ ሙሰኛው፣ቀጣፊው፣ ዘራፊው ሲደላው እና ሲበለጽግ የሚሉ፤ አንተም ይሄን ካደረክ ብቻ ነው የምትድነው ብለው ለክፋት እንድንሰግድ፣ እምነታችንን እንድናስገብር የሚጥሩ እና የሚሰብኩ ፥ እነዚህ ናቸው ጠላቶቻችን።




በዚህ ዓለም ውስጥ “ወንድምን እንደ ራስ መውደድ” የሚባል ነገር አይሰራም ብለው የሚሰብኩን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና መምህራንን ውድቀት እያሳዩን ሃይማኖት እኮ ውሸት ነው፣ ሃይማኖት መብያ ነው፣ ላልተማረ ሕዝብ ጨቋኞች የቀረጹት ማታለያ ነው ብለው የሚሰብኩ፤ እነዚህ ናቸው ጠላቶቻችን።



 የጌታችንን ቃላት በወረቀት ብቻ ያለ ፍልስፍና፣ ፈጽሞ መሬት ላይ ሊወርድ የማይችል፣ በሕይወት መኖር የማይቻል ፍልስፍና (ideal) እንደሆነ የሚነግሩን ፥ እነዚህ ናቸው የመዝሙረኛው ጠላቶች። በባቢሎን ወንዝ ዳርቻ ከነ ሕጻናቶቻቸው በድንጋይ እንዲወገሩ የጸለየባቸው። በዚህ መንፈስ ልጆቻቸውን ያሳድጋሉና።



ወገኖቼ ትግሉ ይሄ ነው። ትግላችን በሥጋ ከሚጎዱን ጋር አይደለም። ይልቁንስ የእኛን የሥጋ ውድቀት ለእምነታችን ሽንፈት ምሳሌ አድርገው ለማቅረብ ከሚጥሩት ጋር ነው ትግላችን።




ስቴፈን ሚለር የተባለው የትራምፕ ቀኝ እጅ በCNN ላይ ቀርቦ እንዲህ ነበር ያለው፦ “የምንኖርበት ዓለም፣ ይሄ የሚታየው ዓለም፣ ጄክ (የCNN ጋዜጠኛ ስም ጠርቶ) ፥ የሚተዳደረው በኃይል ነው፣ የሚገዛው በጉልበት ነው፣ የሚመራው በስልጣን ነው። እነዚህ ናቸው የዚህ ዓለም የማይነቃነቁ ሕጎች። ዓለም ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ያሉ ሕጎች። ዓለም አቀፋዊ መልካምነት እና ጥሩነት የሚባል ነገር የለም።”


"You can talk all you want about international niceties and everything else. But we live in a world, in the real world, Jake, that is governed by strength, that is governed by force, that is governed by power. These are the iron laws of the world."



ዛሬ ስቴፈን ሚለር የታላቂቱ ሀገር፣ የዓለም ልዕለ ኃያል ሀገር አሜሪካ መሪ ዋነኛ አማካሪ፣ እልፍኝ አስከልካይ፣ ፊርማ ያዥ፣ አስገቢ እና አስወጪ ሆኖ ተሹሟል። ልክ የእውነት ጠላት፣ የእግዚአብሔር ህዝብ ጠላት፣ የእውነተኛው ሰው የመርዶክዮስ ጠላት የነበረው ሐማ በመቶ ሃያ ሀገር ላይ የበላይ በነበረው በአርጤክስ ንጉሥ ዘንድ አማካሪ እንደነበረው ሁሉ ማለት ነው።



ስቴፈን ሚለር (ሐማ) የዓለም ሕግ “ኃይል፣ ጉልበት እና ስልጣን” ነው ብሎ ስለሚያምን፤ መጀመሪያ ያጠቃቸው እነዚህ ሦስቱ ነገሮች የሌላቸውን ስደተኞች ነበር። ራሳቸውን የሚሸሸጉበት ሀገር የላቸውም፣ ከሀገራቸው ሁሉን ጥለው ወጥተዋል፣ ከለላ የሚገዙበት ገንዘብ የላቸውም፤ በሰዓት የሚያገኙት ገንዘብ ትንሽ ነው፣ መልካቸው ሀገሬውን አይመስልም ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው፣ ቋንቋቸው አክሰንት አለው ገና አፋቸውን ሲከፍቱ ስደተኞች እንደሆኑ ይታወቃሉ። ስልጣን ላይ ያለው የእነሱ ወገን አይደለም። ስለዚህ የስቴፈን ሚለር ዱላ ያርፍባቸዋል። ስደተኞቹን በግል ስለሚያውቃቸው አይደለም። ይልቁንስ የአይዶሎጂው፣ የፍልስፍናው እውነተኝነት ማሳያ ሊያደርጋቸው እንጂ።




“ይሄ ዓለም የምርጦች ነው። ይሄ ዓለም የኃያላን ነው። ደካሞችን ወደ ሀገር መጋበዝ፣ ማስጠለል ፥ ሀገርን ያዳክማል። ታላቅነትን ወደ ታናሽነት ይቀይራል” ብሎ ስለሚያምን፤ የእምነቱ ማሳያ ሊያደርጋቸው ስደተኞችን ያጠቃል።




ይሄን የምታነቡ እንደምትገነዘቡት ትግሉ የእምነት ነው። ትግሉ የመርህ ነው። በዚህ ዓለም የታላቁ አምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንጂ አሸናፊ የሚያደርገን ፥ ኃይል፣ ጉልበት እና ስልጣን አይደለም። ስቴፈን “በዚህ ዓለም ትልቁ ግብ ሌሎችን መግዛት ነው” ይለናል። የኛ ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “የተጠራችሁት ለማገልገል ነው” ይለናል።



ወገኖቼ ደጉ ሳምራዊ እንድንሆን በተጠራንበት ዓለም ላይ ደካሞችን እና ስልጣን የሌላቸውን ሁሉ እንድንገፋ እና እንድናሳድድ የሚገፋንን በጠቅላላ ትንሣኤ በሌለው ሞት እንዲጠፉ ወደ ክርስቶስ እንለምናለን። ስቴፈን እንዲሞት አይደለም። ስቴፈን ሚለርን የሰጠን እምነቱ እንጂ። ስቴፈን ሚለር እኮ ያለ እዚህ እምነቱ እና ፍልስፍናው አናውቀውም ነበር። ስቴፈን ሚለር የፍቅር ሰው ከሆነ እኮ ከስሙ በቀር ስቴፈን ሚለር አይደለም። ለዚህ ነው እነዛ ዘማሪዎች የእስራኤልን ጠላቶች በባቢሎን ድንጋይ ላይ ከነሕጻናቶቻቸው እንዲጨፈጭፍ የሠራዊት ጌታን እግዚአብሔርን የጠየቁት። ሕጻናቱ ራሱ አድገው ጎልምሰው እንደነሱ ከሚሆኑ በጊዜ ከዚህ ዓለም እንዲወስዳቸው በዚህም እስራኤልንም እንዲጠብቅ፣ እነዛ ሕጻናትም ከግፍ ኃጢአት እንዲታደግ (ከሞቱ ከዛ ኃጢአት ነጻ ናቸውና) የለመኑት። የባቢሎን የኃጢአት ጥልቀት ሕጻናቱ በዛ ስርዓት ውስጥ አድገው ጥሩ ሰው የመሆን ምንም ተስፋ አስጥቷቸዋልና።




ስለዚህ አቤቱ ጌታችን ሆይ ተነስ። ጠላቶችህንም እርታ። የዚህ ዓለም ብርቱ ሕግ፤ የማይነቃነቀው ሕግ ፍቅር ነውና። ወገኖቼ እምነታችንን ይሄ የኃይል ፍልስፍና እንዳይወስድብን እንጠንቀቅ። ስደቱ ቢበዛ፣ ነውሩ ቢበዛ፣ ቤተመቅደሱን ቢያረክሱ፣ በየቀኑ ቢያርዱን፣ የእውነት ፈራጅ የለም፣ እግዚአብሔር በመንበሩ የለም፣ ፍቅር የሚባል ነገር አይሰራም እንዳንል አደራ። ያን አልን ማለት እነሱ አሸነፉ ማለት ነው።




ዳዊት (ትንሹ ዳዊት)፣ ምንም አቅም የሌለው ዳዊት ይሄ ገብቶት ነበር። ለአርባ ቀን ሙሉ እስራኤል ላይ ኃይል ነው አሸናፊ፣ ጉልበት ነው አሸናፊ፣ ቁመት ነው አሸናፊ ብሎ ሲፎክር የነበረውን ጎልያድን እንዴት እንዳናገረው ታስታውሳላችሁ?




እንዲህ ነው ያለው “ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው።” .... “እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።” ቀዳማዊ ሳሙኤል 17፥45።



ዳዊት በጉልበት አይደለም ታላቁን ጎልያድን የረታው። በእግዚአብሔር ስም እንጂ። ለሕዝቡም ያወጀው ያንን ነው። እግዚአብሔር በሰይፍ እና በጦር የሚያድን አምላክ አይደለም። በፍቅሩ እንጂ። በምህረቱ እንጂ። በስሙ እንጂ።




ስለዚህ እምነታችሁን ጠብቁ።


 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

​

Designed and built by Abel

​

bottom of page