top of page
Search

የጥቃቅን ሕግ

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • 1 minute ago
  • 3 min read
ree


የጠቢበኛው የጥበብ መዝሙር ላይ እንዲህ ይላል “ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን።” መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 2፥15።



ለመውደቅም ለመነሳትም የጥቃቅን ሕግ ወሳኝ ነው። የጥቃቅን ሕግን የሚያውቅ ሰው፣ በአግባቡ የገባው ሰው በዚህ ምድር ብዙ ርቀት ይጓዛል። የጥቃቅን ሕግ የሰው ልጅን ተፈጥሮ የስንፍናም ሆነ የውንብድና፣ የጉብዝናም ሆነ የዝናን ተፈጥሮ ያገናዘበ ነው።



ሰው ትንሣኤውም ሆነ ሞቱ በጥቃቅን ሕግ ነው።



ስናድግ በወላጆቻችን የሚነገረን ተረት ነበር። በሬ ሰሮቆ የተያዘው ልጅ። ያ ልጅ በበሬ ስርቆትን አልጀመረም ነበር። አንድ ቀን መርፌ ሰርቆ መጣ። ዝም አለችው እናቱ። ከዛ ዳቦ፣ ከዛ የሆኑ ተራ እቃዎችን፣ ከዛ እያደገ ሄደ። በበሬ ግን ተያዘ። ያኔ ወደ እናቱ ዞሮ “በመርፌ ብታቆሚኝ!” አላት። የጥቃቅን ሕግ ማለት ይሄ ነው።



አንዳንድ ጊዜ በመንገድ ስሄድ ቤት አልባ የሆኑ እና በሱስ የወደቁ ሰዎችን አያለሁ። እነዚህ ሰዎች መንገድ ላይ ከሆነ ጊዜ በኋላ ነው የወጡት። እዛው አልተፈጠሩም። ግን የትኛው ሱስ ነበር ለዚህ ያደረሳቸው? የመጀመሪያ ቀን የሳቡት፣ ሁለተኛው ቀን የሳቡት ወይስ ከሳምንት በኋላ የሳቡት ሲሻ ወይም ኮኬን ነው እዚህ ላይ ያደረሳቸው? አላውቅም። የማውቀው ግን ያን መሳብ የጀመሩ ቀን ዛሬ እዚህ ላይ እንደሚድርሱ ማናቸውም አልገመቱም ነበር።



አባት ልጁን ሌላ ከተማ ወዳለሁ እርሻው ላከው። የላከው እርሻውን እንዲያርም ነው። ልጅ ወደ እርሻው ሲደርስ ፥ የእርሻው ግዙፍነት እና መላው እርሻው በአረም መዋጡ የሥራ ቅስሙን ሰበረው። ስለዚህ ማረሙን ትቶ ተኛ። አባት ከሆነ ጊዜ በኋላ ሲመጣ ልጅ ተኝቷል። ለምን እንዳላረመ ሲጠይቀው፤ ይሄን ሁሉ እርሻ ብቻውን ማረም ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ነገረው። የጥቃቅን ሕግ የገባው አባት ነበርና፤ ልጁን ሳይቆጣ እንዲህ አለው። “በየቀኑ በቁመትህ ልክ ብቻ አርም። ከዛ ተኛ።” ልጅ እያንገራገረ ጀመረ። ቀስ እያለ ማረሙን ወደደው፣ ከቁመቱ በላይ፣ ሁለት እና ሦስት እጥፍ ማረም ጀመረ። በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እርሻውን ሁሉ አርሞ ጨረሰ። የጥቃቅን ሕግ በሬ ብቻ አይደለም የሚያሰርቀው። ጋሻ የሚያክልን እርሻም ያሳርማል። የርግማን ብቻ ሳይሆን የበረከትም ሕግ ነው።



በሕይወታችሁ ተኝታችሁ ካላችሁ እና ሰማይ ምድሩ በላያችሁ ላይ የተጫነ ከመሰላችሁ፤ ሰማዩን ከላያችሁ ለማንሳት ከመታገል ፥ ማንሳት ከምትችሉት ቀላል ነገር ጀምሩ። ምንም ስፖርት ከማይሰራ ሰው ይልቅ አራት ፑሽ አፕ ብቻ በየቀኑ ሰራለሁ ብሎ የተነሳ ሰው በዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ጤነኛ ሆኖ ራሱን ያገኘዋል። ብዙ ሰው ስለቢዝነስ፣ ስለ ስኬት እና ስለሥራ ሲያስብ ዓይኑ ላይ ድቅን የሚለው የትልልቅ ሕግ እንጂ የጥቃቅን ሕግ አይደለም።



የሆነ ነገር ሥራ የምትሉት አብዛኛው ሰው ትልቅ ብር ይጠራላችዋል። ወይም ይሄን ያህል ገንዘብ ያስፈልጋል ይላል። ግን ትልልቅ ብር ያላቸው ሰዎች ሁሉ ከዛ አልጀመሩም። ይልቁንስ በእጃቸው የነበሩ ጥቂቶችን ዘሩ። ከዛ ያጨዱትን መልሰው እየዘሩ ፥ ዛሬ ጋሻው የእነሱ ሆነ። ከትንሽ ለመጀመር ያልፈቀደ ሰው ትልቅ ሆኖ መቀጠል አይችልም።



ብዙ ሰው ስለ ስርቆት፣ ሌብነት፣ ማጭበርበር ሲያስብ ፥ የሚያስበው ስለ ሳንቲሞች እና መርፌዎች አይደለም። ግን የጥቃቅን ሕግ የሚነግረን ወደ ገሀነም የሚወስደው መንገድ በቅን ልቦና የተጠረገ መሆኑን ነው። “ምንም አይደል” ብለን ዛሬ የሰበርናት ትንሽዬ ሕግ ነገ ገሀነም ላይ ታደርሰናለች።



አብይ አህመድ በአንድ ቀን አንባገነን አልሆነም። ደራሲ ሀዲስ አለማየው ስለ መንግስቱ ኃይለማርያም መለወጥ ለቪኦኤ በተናገሩበት ወቅት እንዲህ ነበር ያሉት። መንግስቱን እዚህ አውሬነት ላይ ያደረሱት ዙሪያው ያሉ ጓዶቹ ናቸው። “አንተ እኮ ነብር ነህ” አሉት። መጀመሪያ “ጓዶች እኔ እንደናንተው ነኝ” አላቸው። ግን ደገመቱ። “ነብር ነህ” አሉት አሁንም። ተቃወመ። በትህትና “እንደናንተው ነኝ” አላቸው። ቀስ እያለ ግን እርሱም ተቃውሞውን ቀነሰ። በመጨረሻ ነብር ሳልሆን አልቀርም ብሎ መጠራጠር ጀመር። በመጨረሻ ጭራሽ ነብር ነህ ካላሉት መግደል ጀመረ። ከዛ ነብር ሆኖ ፈጃቸው። ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም ብሎ የተጀመረ አብዮት፣ በአንዱ ሰው ጄኔራል አማን አንዶም መገደል ቀስ እያለ ስልሳዎችን ፈጀ። ከዛ ስልሳ ሺ ሕዝብ ፈጀ። አብይ አህመድም ዛሬ ላይ ለመድረስ የጥቃቅን ሕግን ተከትሏል።



ራሳችሁን በመጥፎ ባህሪ እና በማትፈልጉት አስተሳሰብ ውስጥ ካገኛችሁት፣ የጥቃቅን ሕግን ፍልስፍና ተከተሉ። ችላ ያላችሁት ደካማ ወይም መጥፎ ባህሪ ካላችሁ ፥ ነገ የሞት አፋፍ ላይ ራሳችሁን ከማግኘታችሁ በፊት ዛሬ ንቁ።



ብዙ ትዳሮች ፍጹም በሆነ ፍቅር ይጀምራሉ። ልነጠፍልሽ ያልተባባሉ፣ በሕልምም በቁምም ያልተነፋፈቁ ፍቅረኛሞችን ማግኘት ከባድ ነው። ከዛ ከዓመታት በኋላ ወደ ዛ ትዳር ተመለሱ። የጥቃቅን ሕግ ወይ ፍቺ ላይ አድርሷቸዋል ወይም ፍቅር የሞተበት ቤት አስታቅፎአቸዋል። መቼ ነው ግን እንደዚህ መሆን የጀመሩት? አንድ ቀን!!! ያ ችላ ያሏት አለመግባባት፣ በቶሎ ያልፈቱት ልዩነት፣ ያዳፈኑት እና ከውይይት አርቀው የቀበሩት ያ አጀንዳ ነው የጥቃቅን ሕግን ተከትሎ የትዳራቸው ካንሰር ወደ መሆን ያደገው።



ወይናችሁ እንዲያብብ የምትፈልጉ ሰዎች ፥ ጥቃቅን ነገር ማድረግ ጀምሩ። ወይናችሁ ያበበም ሰዎች ወይናችሁ እንዳይጠፋ ጥቃቅን ነገሮችን በቶሎ ፈልጋችሁ ፥ እነሱን ነቅላችሁ አሶግዱ። ትልልቁን ነገር ችላ ብትሉት ይሻላል፤ ጥቃቅኑን ችላ ከምትሉ።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page