top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10, 2025
  • 3 min read

የሰው ልጆች በሁሉም ወቅት የሚሰራ መመዘኛ የለንም። መመዘኛችን እና የሞራል እይታችን በደረስንበት የእይታ ጥራት እና አድማስ የሚወሰን ነው። ይሄ ማለት ዘመን እና ድንበር ተሻጋሪ የሞራል ልኬቶች (universal values) የሉንም አይደለም። ለምሳሌ ደግነትን የትኛውም ማህበረሰብ በየትኛውም ስፍራ እንደ ጥሩ እሴት ያከብረዋል። ጥያቄው በአንድ ወቅት ደግነት ተብሎ የሚወሰድ ጉዳይ በሌላ ጊዜ ክፋት ሊሆን ይችላል። ይሄ ተቀያያሪ የሆነ የይዘት ሁኔታዎች የሰው ልጅን የመመዘኛ ድክመት ነው የሚያሳየው። ይሄ ማለት ግን ጽንፎችን የሰው ልጅ አያውቃቸውም ማለት ላይሆን ይችላል። ለአንዱ ሙቀት የሆነ ለሌላው ኖርማል የዓየር ጸባይ ሊሆን ይችላል። ግን የትኛውም የሰው ልጅ ላይኖርበት የሚችል የሙቀት መጠን አለ። በሚዛን ደረጃ ጽንፎችን የማወቅ አቅም አለን ማለት ነው። ፍጹም ምቾትን እና ፍጹም የሆነ ስቃይን የማወቅ አቅምም እንደዚሁ። በፍጽምና መኃል ስላሉት ጉዳዮች ግን በትክክል የሚመዝን አዕምሮ የለንም።



ይሄን በሕመም እንየው። ከእግር በታች ሰውነታችን ሕመም ቢደርስበት፤ በዛ ቦታ ያለው የነርቭ ሥርዓታችን ለአዕምሮአችን መልዕክት ያስተላልፋል። መልዕቱን ተከትሎ አዕምሮአችን ያ ቦታ አደጋ ውስጥ እንዳለ በመግለጽ፤ እዛ ቦታ ላይ እብጭ፣ መቅላት እና ሕመም እንዲኖር ያደርጋል። አዕምሮአችን ያን የሚያስተላልፈው ያን ስፍራ ከመጠበቅ አንጻር ነው። ያ ሕመም ያለበትን አካል በመጠቀም የበለጠ እንዳንጎዳው ያሳብጠዋል ወይም ሕመም ያኖራል። የአዕምሮ ተቀዳሚ ሥራ እኛን ከአደጋ መከላከል ነው። ልክ ነኝ ወይም ልክ አይደለውም የሚለው የአዕምሮ ተቀዳሚ ተልዕኮ አይደለም። ተቀዳሚው ተልዕኮ መጠበቅ (protect) ወይም መከላከል ነው።



አንዳንድ ጊዜ ግን አዕምሮ የተሳሳተ ሲግናል ይልካል። ለምሳሌ Complex Regional Pain Syndrome (CRPS) የሚነግረን ምንም እንኳ የታመመው የሰውነት አካል ቢድንም አዕምሮ ግን እስካሁን እንዳልዳነ ሊቆጥረው ይችላል። ስለዚህ እነዛ የሕመም ምልክቶችን በመላክ እብጠት እና መቅላት፣ ሕመም እንዲቀጥል ሊያደርገው ይችላል። ይሄ መጀመሪያ ከደረሰው የሕመም ከባድነት የተነሳ፤ ሰውነታችን ቢድን እንኳ፤ አዕምሮአችን ግን ሕመሙ ላይ ቀርቷል። ከሰውነታችን ጋር አብሮ ራሱን አላሻሻለም። በዚህም የሕመም ሲግናል (ምልክት) በተከታታይ ይልካል።



ለዚህ አንዱ የሚደረገው አዕምሮ እነዛን የሕመም ሲግናሎች መላክ እንዲያቆም ማሰልጠን ነው። አዕምሮአችን በየዕለት ሕይወታችን የሚያደርገው ይሄንን ነው። እኛን የመጠበቅ ተልዕኮ ስላለው፤ ከዚህ በፊት ውሻ የነከሰው ሰው ፥ ለውሻ የሚኖረው ፍርሃት ወደር አይኖረውም። ሁሉም ሰው ውሻውን እየዳሰሰ እርሱ ግን ከዛ ውሻ ይሸሻል። አዕምሮ ይሄን ሰው በማንኛውም ሁኔታ መጠበቅ ስላለበት፤ ከዚህ በፊት በውሻ የደረሰበትን እንዳይረሳ በማድረግ ይጠብቀዋል። ምንአልባት ሰውዬው ለራሱ ማጽናኛ ቃሎችን ሁሉ ሊጠቀም ይችላል። “ውሻ አይወደኝም ወይም የውሻ መወደድ የለኝም” እና የመሳሰሉት እምነቶችን።



ይሄ ግን በግለሰብ ደረጃ ብቻ እንዳይመስላችሁ። በማህበረሰብ ደረጃም በወል አዕምሮ ውስጥም ተመሳሳይ እሳቤዎች አሉ። በፖሊሲም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ይገዛ የነበረን ብሔር ሌሎች የማህበረሰብ አካላት ሊፈሩት እና “ከመጣብን የቀደመውን ይደግማል” በሚል ፍርሃት ሊያሳዱት ይችላሉ። ለምሳሌ በሴፕቴምበር አስራ አንድ የደረሰው የሽብር ጥቃት እንዴት በዓለም ላይ ያሉ ሙስሊም ያልሆኑ ማህበረሰቦችን እይታ እንደቀየረ ተመልከቱ። የጥቂት ሰዎች አውሬነት የብዙ ሰዎች ተደርጎ በፖሊሲ ደረጃ ምንም በዚህ ጉዳይ ላይ የሌሉ የእምነቱ ተከታዮች ለአሰቃቂ ጥቃት ተጋልጠዋል።



አሁን በአሜሪካ ውስጥ የምናየው የኢሚግሬሽን ፖሊሲም የዚህ ስሁት ሪያክሽን ውጤት ነው። ጥቂት ከሌሎች ሀገራት የመጡ ሰዎች በፈጸሙት ወንጀሎች ብዙ መልካም ማንነት ያላቸው ሰዎች በጅምላ ይፈረድባቸዋል። ለሁሉም ጥላቻ ይኖራቸዋል። “ለምን እንደዚህ ታደርጋላችሁ?” ሲባሉ፤ አንድ ሰነድ አልባ ስደተኛ የሆነ ቦታ እና ጊዜ ያደረገውን ወንጀል እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ። ይሄ የሲግናል ግራ መጋባት ነው። ብዙ ጊዜ ለዚህ የሚዳረጉ ሰዎች የተጋላጭነት መጠናቸው በጣም ጠባብ የሆኑ ናቸው።



በቅርብ አንዱ ከኢትዮጵያ ስለ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለክርስትና መስፋፋት እንቅፋት እንደሆነች ጻፈ። ይሄ ሰው ምን አልባት ከአዲስ አበባ የዘለለ የሕይወት ተጋላጭነት የለው። ስለ ካቶሊክም የሰማው ከኢትዮጵያ ወጥተው በማያውቁ ሰዎች ከተጻፉ መጽሐፎች ይሆናል። አውሮፓ በየሀምሳ ሜትሩ ቤተክርስቲያንን የተከለች፣ በቢሊዮን የሚቆጠር አማኝ ያላት ቤተ እምነት እንደሆነች ምንም እውቀቱ የለውም።



አንድ ወዳጄ ስለነጮች ያለው አመለካከት በጣም ጠባብ ነው። የእኔ ጥያቄ የነበረው “ምን ያህል ነጭ የቅርብ ወዳጅ አሉህ? ወይም በበዓል ቀናቸው የምትሄድበት ነጮች አሉ? ወይም የሴት ጓደኛ ከነጮች ይዘህ ታውቃለህ? የሚል ነበር። መልሱም የሉኝም። አላውቅም ነበር።



ለComplex Regional Pain Syndrome (CRPS) የሚመከረው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የተጎዳውን የሰውነት ክፍል ለተለያዩ ቴምፕሬቸሮች፣ ንክኪ እና እንቅስቃሴ ማጋለጥ ነው። በዚህም አዕምሮ ቀስ እያለ ያ ቦታ መዳኑን ይማራል። ስለዚህ ቀስ እያለ የስህተት የሕመም ሲግናሎችን መላክ ያቆማል ማለት ነው።



ትግሬን ወይም አማራን ወይም ኦሮሞን የሚጠላ ሰው የምመክረው፣ ወጥቶ ከእነዚህ ብሔሮች ብዙ ወዳጆች እንዲያፈራ ነው። ቀስ እያለ ያለው አስተሳሰብ ፍጹም ከእውነት የተቃረነ እንደሆነ ይማራል። ለምሳሌ በወንድ የተደፈረች ሴት ሁሉም ወንዶች መጥፎ እንደሆኑ ልታስብ ትችላለች። ከዚህ ስሁት አስተሳሰብ ብቸኛ የሚያወጣት ራሷን ለሌሎች ወንዶች ስታጋልጥ ነው። ፍርሃትህን በመጋፈጥ ብቻ ነው የምታሸንፈው። ይሄም የአዕምሮ ካርታን (GPS/Map) ማደስ ይባላል። አዕምሮአችን የሆነ ቦታ ለመድረስ የሚያውቀው GPS (Map) አለው። ያ GPS (map) አሁን ላይ አይሰራም። ዓለም ተቀያይሯል። ቁስሎች ድነዋል። ግን አዕምሮአችን ያው የጥንቱ GPS (map) ላይ ነው። ያንን እንዲቀይር ማድረግ የሚቻለው ቦታዎቹ ላይ በመሄድ (exposing the brain) የተለወጠውን ነገር በግድ በማሳየት ነው። አለበለዚያ ግን ከእውነት የራቁ እና ለሕይወት እንቅፋት የሆኑ ውሳኔዎችን እየወሰንን እንቀጥላለን።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 3, 2025
  • 3 min read

የስነልቦና ሐኪሞች እንዲህ ይላሉ “ለማዳን በጣም ከባዱ በሽተኛ ራሱን ለማዳን የሚጥርን የማዳን ጥረቱን ማስቆም ነው።” ያሉን አስገራሚ ባህሪዎች ራሳችንን ለማከም የወሰድናቸው መድኋኒቶች እንደሆኑ ቢነገረን ምን የምንል ይመስላችኋል?



ማርክ ትዌን ስለዚህ ሲናገር በድመት ነው። ብረትምጣድ ላይ ለመቀመጥ የምትፈራ ድመት ካያችሁ፤ ከዚህ በፊት የጋለ ብረትምጣድ ላይ ተቀምጣለች ማለት ነው። የጋለ ብረትምጣድ ብቻ አይደለም የምታሶግደው ሁሉንም ብረትምጣዶች እንጂ። ሁለት ሦስቴ በሰዎች የተከዳ ሰው የሚክዱ ሰዎችን ብቻ አይደለም የሚያሶግደው፤ ለደስተኛ እና ጤናማ ሕይወት መሠረት የሆነውን ሰውን ማመን ሁሉ እንጂ። በየዓመቱ ከሀገር ወደ ሀገር ከቤተሰቦቹ ጋር እየተዘዋወረ ያደገ ልጅ ፥ ዘላቂ ጓደኝነትን እና ትውስታን መመስረት ይሳነዋል። ሁሉም ነገር ጊዜያዊ ነው የሚመስለው። በጣም በችግር ያደገ ሰው ፤ በጣም ገንዘብ ቢያገኝም ሁልጊዜ ወደ ዛ ችግር የሚመለስ ስለሚመስለው የድህነት ስነልቦና ላይለቀው ይችላል።



ቅናት እና ምቀኝነት እንስሳዊ ማንነታችን ለገጠመን በሽታዎች የለገሰን መድኋኒቶች ናቸው። እንስሳዊ ባህሪያችን በዙሪያችን ያለ ሰው ሲበልጠው ይደነግጣል። በዙሪያችን ያለ ሰው ከበለጠን ወይም ከኛ ትኩረትን ከተጋራ ይፈራል። ምክንያቱም በእንስሳት ዓለም መበለጥ ዋጋ ያስከፍላል። የበለጠን ሰው የኛ የሆነውን ሁሉ ሊወስድ እና ሊያጠፋን ይችላል። ውስጣቸው ነጭ ወረቀት ነው የምንላቸው ሕጻናት በቅናት ይጠቃሉ። የሦስት ዓመት ልጅ አዲስ በተወለደው ሕጻን ልትቀና ትችላለች። አዲሱ ሕጻን የወላጆቹን ትኩረት መሳቡ እንድትጠላው ያደርጋታል። ምክንያቱም ወላጆቿን እንደቀማት አድርጋ ነው የምትቆጥረው። ከወላጆቿ ይልቅ ምንም ራሷን መከላከያ የሌላት ልጅ ይሄን እንደ ትልቅ አደጋ ነው የምትቆጥረው። ስለዚህ በአዲሱ ሕጻን ትቀናለች። ችግሩ የሕጻኗ መቅናት አይደለም፤ አድገንም ሰውነታችን ይሄን መድኋኒት ለመበለጥ እንደ መፍትሔ ሲሰጠን ተቀብለን መዋጣችን ነው። ይሄን ነው ለማዳን ትልቁ ፈተና። ራሳችንን ለማዳን የምንወስደው መድኃኒት።



በሰዎች በልጅነቱ የተጎዳ ሰው ወይም በቤቱ ውስጥ የሌሎችን ትኩረት ለማግኘት የሚቸገር ሰው፤ ሰዎችን ለማስደሰት የሚሰራ ይሆናል። ምክንያቱም በዚህ ቤት ውስጥ ሰው ሆኖ ለመቆጠር ሌሎችን ማስደሰት ነበረበት። በዚህም የራሱን ስሜት የመተው እና የማይፈልገውን ነገር እንቢ የማለት አቅም ያጣል። ብዙ ሰዎች ወደ ሱስ የሚሄዱት በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለተቀበሏቸው ነው። ሌላ ቦታ ፍቅርን ያጡ እና ቅቡልነት ወይም ትኩረቱን ያላገኙ ሰዎች ሱስ ያን ከሰጣቸው ስሜታቸውን ለማከም ይገቡበታል።



ወላጆቿ ቢዚ ከመሆናቸው የተነሳ ጊዜ የማይሰጧት ልጅ፤ በመጨረሻ ራሷን በምላጭ መቁረጥ የጀመረችበትን ታሪክ አንብቤያለሁ። ምክንያቱም በደማች ቁጥር እናቷ ወይም አባቷ ከሥራ ቤት ቀርተው አብረዋት ይሆኑ ነበር። ራስን የማዳን ተልዕኮ ይሄ ነው። ብዙ የሰዎች ባህሪያት ለስሜት ማከሚያነት የተለበሱ ናቸው።



ራሳቸውን በፍጹም ሥራ የሚወጥሩ ሰዎችን አውቃለሁ። እነዚህ የማሰቢያ ጊዜ ካገኙ ማስታወስ እና ማከም የሚፈሩት ሀሳብ ስለሚወጥራቸው ሊሆን ይችላል። ወይም አንዳች የሚያሳዳቸው ድብቅ በእነርሱ ዓለም ብቻ ያለ አውሬ አለ።


ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኃን ይሄን ሽሽት “እንዳይነግርህ አንዳች እውነት!” በሚል ግጥሙ ገልጿታል፤


“ደንስ ጎበዝ፦ ደንስ ጀግና


.


.


.


ርገጥ፥ ጨፍር፥ ደንስ ጀግና!


ያን የሙዚቃህን ናዳ፥ የኮንትራባሱን መብረቅ


ልቀቀውና ይደብለቅለቅ


ምንም-ምንም እንዳታስብ፥ ሁሉሉ-ሁሉን እንድትረሳ


ደንስ! ካካታው ይነሳ


ጭንቅላትክን ግዘፍበት፥ እስኪያሰጥመው አጓራበት


ጭንቅላትክን ግዘፍበት፥ ውቀጥበት፥ ውገርበት ....


ዝግ ብሎማ ያስብ እንደሁ፥ ይነግርሃል አንዳች እውነት!”



ብዙ ሰው ለጤናማ እና በአግባቡ ለሚያስብ ሰው ግራ አጋቢ ሕይወት ውስጥ ገብቶ ታገኙታላችሁ። ማህበረሰብን ለማስደሰት ብቻ ወይም ሰው ምን ይለኛል የሚልን ለማስቀረት ብቻ ለራሱ ፍላጎት ተጻራሪ የሆነ ሕይወት ውስጥ የተዘፈቀ ይኖራል። ወይም ከሰው ጋር መቀላቀል፣ ከሌሎች ጋር አብሮ መተባበር እና የተሻለ አካባቢ መኖር ለጤናውም ሆነ ለሕይወቱ የተሻለ ሆኖ ሳለ ፥ መጋፈጥ የማይፈልጋቸው የስሜት ቁስሎች ይዘውት በብዙ ምሽግ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ። በብቸኝነት ምሽግ ውስጥ፣ ወይም በአልኮል እና እፅ ሱስ ምሽግ ውስጥ፣ በሥራ ማብዛት ምሽግ ውስጥ፣ በገንዘብ ማሳደድ ምሽግ ውስጥ፣ በቅናት እና ምቀኝነት ምሽግ ውስጥ፣ በፍርሃት እና ሁሉን ላስደስት በሚል ምሽግ ውስጥ፣ ሰውን ላለማስቀየም ባለ ምሽግ ውስጥ እና ሌሎች ውስጥ ያሉ አሉ። የማርክ ትዌን ድመት እኛ ውስጥም አለች። በጭቅጭቅ ቤት ውስጥ ያደገ ሰው አውቃለሁ። መከራከር እና ኮስተር ያለ ውይይትን እና ንግግርን ሁሉ ይሸሻል። ጠንከር ብለህ ስለ እንከኑ ልትነግረው ስትል ፥ ከመጋፈጥ ይልቅ ሮጦ ይሄዳል። ምክንያቱም እንደ ድመቷ እንደዚህ ዓይነት ንግግር የሚጭርበት የልጅነቱን ያ ከባድ የአባት እና የእናት ጭቅጭቅ እና ድብድብ ነው።



እኛ ግን እንስሶች ብቻ አይደለንም። ሌላ የምክንያታዊ ክፍልም አለን። ሞኝ የምንሆነው የእንስሳነት ክፍላችንን አሳንሰን ካየን ነው። የእንስሳው ክፍላችን እንደ ዝሆን ግዙፍ ነው። የምክንያት ክፍላችን እንደ አይጥ ድንቢጥ ናት። በኋይል አይጧ ዝሆኑን አትጎትተውም። ግን በጥበብ አይጧ ዝሆኑን ወደ ምትፈልገው ቦታ መምራት ትችላለች። ይሄ በጥበብ እና በትሪክ (trick) ብቻ ነው የሚሆነው።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Jul 13, 2025
  • 4 min read

በዚህ ሥራ ላይ የመሰማራት ስቃይ ከሀገሬ ርቄ የሀገሬን ችግር በቅርብ በየቀኑ ማስተዋሌ ነው። ብዙ ኢትዮጵያኖች ወደ ሀገራቸው ተመለሱ ከሚባሉ መሞትን ይመርጣሉ። በተቃራኒው ከሌሎች ሀገሮች የመጡ ስደተኞች የአሳይለም ኬዛችሁ ተቀባይነት አላገኘም ሲባሉ፤ እየሳቁ ነው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱት። ያነሰ ምቾት እና ተስፋ እንደሚጠብቃቸው ቢያቁ እንኳ ሀገር ግን እንዳላቸው ያውቃሉ። ሊኖሩበት እና ጠንክረው ደግሞ ከሰሩ ሊለወጡበት የሚችሉበት ሀገር እንዳላቸው ያውቃሉ። የኛ ግን ይለያል። ከሀገር የወጣን ሰዎች መጀመሪያ የምናደርገው ልክ እንደ ስፓን የጦር ጄኔራል ኸርናን ኮርቴዝ መርከባችን ኢትዮጵያን ማቃጠል ነው። እስቲ ስንት የዩትዩብ እና የሶሻል ሚዲያ አካውንት አለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልጆች የምዕራባውያንን እውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና የታላቅነት ምስጢር ሊያስቀስም የሚችል መልዕክት የሚያስጨብጡ?


ይልቁንስ ጦርነት የሚያፋፍሙ፣ ነፍጥ አንስተው የደሃ ልጅ የደሃ ልጅን እንዲገድል የሚያደርግ እና አንዱ ዘር አንዱን ዘር ለጠብ የሚያነሳሳ የይቱዩብ ቻናል ነው እንደ እንጉዳይ የበዛው። ዲያስፖራው የሚሰባሰበው እና ገንዘብ የሚያዋጣው፣ መቀነቱን የሚፈታው መመለሻ ሀገር እንዲኖረው የሚያስችል ቴክኖሎጂዎችን እና አውታሮችን ለመገንባት ሳይሆን ፥ መመለሻ ሀገር እንዳይኖረው የሚያስችል ጦርነቶችን ፈንድ ለማድረግ ነው።



ኢትዮጵያውያን ባለንበት ሀገር ገነባን ቢባል ራሱ ቢበዛ የምንገነባው የሃይማኖት ተቋማት (ቤተክርስቲያን) እና ሬስቶራንት ነው። ከ10 ሺ የማይበልጥ ምዕመን ባለበት ከተማ ሰባት እና ስምንት ቤተክርስቲያ ታገኛላችሁ። ይሄ እንዴት አያሳፍረንም?! እነዚህን የቤተክርስቲያን ሕንጻዎች ራሱ ከሰኞ እስከ ዓርብ ወላጆች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲሰሩ እና ገንዘብ እንዲያከማቹ የልጆቻቸው መዋያ ወደ ማድረግ እንኳ መቀየር አልተቻለም። ባሉት የአንድ እምነት ቤተእምነቶች መካከል ያለው የዘር ልዩነት እና የመገፋፋት መጠን ፥ የትኛው አምላክ በዚህ እንደሚከብርበት ግር ይላል።



ምንድ ነው ግን የነካን?



ለእኔ ሁልጊዜ መልሱ “ሥር የሰደደ መኃይምነት እና ድንቁርና ነው።” ከዚህ በፊት በሰንበት ዕይታዬ አተኩሬ እንደጻፍኩት የአይሁድ ማህበረሰብ ያለውን ሕብረት ተመልከቱ። አሜሪካ ውስጥ ካጠቃላይ ማህበረሰቡ 2.4 ፐርሰንት ብቻ ናቸው። ከዚህ ውስጥ ሊብራል አሉ። ቀኝ ዘመም አሉ። እስራኤልን አስመልክቶ ግን አንዳቸውም ወለም ዘለም የለም። ይሄ 2.4 ፐርሰንት የሚሆን አስደናቂ ሕዝብ ነው የአሜሪካንን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ የሚዘውረው። ልጆቻቸውን በማስተማር ወደር የላቸውም። ሲያስተምሩ ደግሞ ለጋራ ነው። ብቻ የሚባል ነገር የላቸውም። በሁሉም መስክ የበላይነትን ለመያዝ ይሰራሉ። የጉግል ባለቤት አይሁዳዊ ነው። የቻት ጂፒቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አይሁዳዊ ነው። የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባለቤት ዙከበርግ አይሁዳዊ ነው። ዋል ስትሪት ላይ እነሱ ናቸው። የኢንተርቴመንት ማዕከሉን ይዘውታል። ይሄ ግን እንደ ማህበረሰብ ስለሰሩ እና ዓለም አይሁዳዊያን ላይ ምን ያህል ጨካኝ እንደነበረ ስላዩት ነው። ስለዚህ ከአይሁድ ውጪ ለአይሁድ ሌላ ማንም እንደ ሌለ ገባቸው። ደካማ ሆነው በታዩ ወቅት አጥንታቸውን ለመፍጨት የሚጨክን ዓለም እንዳለ እና ያንንም ስለ ፍትሕ ብሎ ለማስቆም የፈቀደ ታላቅ ሀገር እንደ ሌለ ስለተመለከቱ ነው።



መጽሐፉ ቅዱስ ላይ ከአብርሃም እስከ ኤልያስ፤ ከኢዮብ እስከ ጳውሎስ አንድ ንግግር ተናግረው ነበር። “ብቻዬን ነኝ። ብቻዬን ቀረው።” የሚል። የእስራኤል አምላክ መልስ ግን ሁልጊዜ አንድ ነበር። “ብቻህን አይደለህም” የሚል ተግሳጽ ነበር ለእነዚህ ቅዱሳን የሚደርሳቸው ድምጽ። ብቻ ተኮኖ የሚሰራ ምንም ዓይነት ጽድቅ የለም። የምስጋና ጥማት ይዞት የፈጠረን አምላክ የለም። ፍቅሩን የማጋራት ፍላጎት ነው ፍጥረትን ሕያው ያደረገው።



ኢትዮጵያኖች ትልቁ መኃይምነታችን እዚህ ጋር ነው። ብቻ የመድመቅ ፍላጎት። ተልይቶ የመጥገብ እና የማብለጭለጭ ዝቅተኛ አስተሳሰብ አለን። ባህላችን ምቀኝነት መገለጫው እስኪሆን ድረስ። ይሄን መኃይምነት የምለው ማናችንም ቢሆን በመጨረሻ ጠንካራ እና በኢኮኖሚ ያደገ ማህበረሰብ ከሌለን በቀር ብዙ ርቀት መሄድ እንደማንችል ስለምንዘነጋ ነው። ብቻችን ፈጥነን ለጊዜው መሄድ እንችል ይሆናል። ሩቅ ግን አንሄድም። ቤተሰባችን ውስጥ ያሉ ታናናሾቻችንን ለመርዳት የማንፈጥን ካልሆነ፣ ማህበረሰባችን ውስጥ ሩቅ አስበን፣ ስትራቴጂክ ሆነን ወጣቶች ላይ መስራት ካልቻልን ነገ አደጋ ቢደርስብን ጠንካራ ሆኖ ሊቆምልን የሚችል ማህበረሰብ አይኖረንም።



ፖለቲካውን ይሄው ለባለፈው አርባ እና ሃምሳ ዓመት ሞከርነው። ቢያንስ ለምድነው በረጅም ጊዜ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስትራቴጂዎችን ማሰብ የማንችለው? በታላላቅ የምዕራባውያን ተቋማት ውስጥ ያለንስ ሰዎች ገፈን መጣል የምንችለው ማንነት ያለን ይመስል ያልሆነውን ለመሆን ከምንጥር ፥ ቢያንስ እኛ ከደረስንበት በላይ የነገው ትውልድ እንዲደርስ ጥቂት ግን ዘላቂ ነገሮች ላይ አተኩረን ለምን አንሰራም? በሞታችን አልጋ ላይ ሆነን ፥ በዚህ ዓለም ላይ ብቻችን እና ራሳችንን ብቻ አበልጽገን እና አዋቂ አድርገን ማለፋችን አይቆጨንም?


እንዴት ሁላችንም መፍትሔ የሌለው የዘር ፖለቲካ ውስጥ ራሳችንን ሁልጊዜ ነክረን እንሞታለን? የነበረንን አንድ ሕይወት፣ አንድ ሰማንያ እና ሰባ ዓመት አሁን ስልጣን የያዘው ትግሬ ነው፣ አማራ ነው፣ ኦሮሞ ነው ብለን ስንነታራክ ብቻ ጨርሰነው ስንሄድ እንዴት አያሳፍረንም? ወይም ቤተመቅደስ ብቻ በየቦታው እየገዛን ፥ ለትውልድ ግን ችግርን እና መከፋፈልን አስረክበን ስናልፍ እንዴት አያሳፍረንም?



አንዳንድ ጅሎች ደግሞ አሉ። ይሄን ጹሁፍ ሲያነቡ እኔ ምን ላድረግ፣ የኔ አቅም ደካማ ነው፣ ስልጣን የለኝ ወይም ፖሊሲ ላይ ያሉ ሰዎች ይሄን ካለወጡ እኔ ምንም አቅም የለኝም የሚሉ። እንደዚህ ዓይነት ጅሎች በሕይወት ይገጥሙናል። መስራት የማይወዱ። ስልጣን ሲይዙ ብቻ መስራት የሚችሉ የሚመስላቸው። ወይም ሁሉን የመቀየር ስልጣን ካልተሰጣቸው በቀር የእነሱ ኃላፊነት የማይታያቸው። ልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ሺ ዲናር ተሰጥቶ ፥ የተሰጠው አንድ ሺ ብቻ መሆኑ ላይ አተኩሮ ጌታው እንደ መጣበት ሰነፍ ያሉ።



ማዕበሉ ብዙ አሣዎችን እየገፈተረ ወደ አሸዋው ያወጣቸዋል። በዚህ ሰዓት በዚህ ዓለም ላይ ብቻውን እንዳልሆነ የገባው አንድ መልካም ሰው የሚችለውን አሣዎች እያነሳ ወደ ባህሩ ይመልሳቸዋል። ማዕበሉ ባያቋርጥም የእርሱ ድርሻ ግን የሚችለውን ማድረግ እንጂ የማይችለውን ማዕበል ማስቆም እንዳልሆነ ስለገባው አሣዎችን ወደ ባህሩ መመለሱን ቀጠለ። በዚህ ሰዓት ሁልጊዜ ብቻውን እንደሆነ የሚታየው አንድ ሰነፍ ተከሰተ። እየገላመጠው ፥ “ምን ሆነሃል?” አለው። “ምን ሆኛለው?” አለው። “ይሄ ሁሉ አሣ በማዕበሉ ተገፍትሮ እየወጣ ያንተ ሁለት አሣዎች እያነሱ ወደ ባህሩ መመለስ ምን ሊፈይድ ነው?” አለው! ቂልነቱ እያሳዘነው ፥ ወደ እጆቹ ወዳሉት አሣዎች እያመለከተው ፥ “የማደርገው ነገር ለእነዚህ አሣዎች ይረባል” አለው።



የችግሮችን ማዕበሎች እያሳዩን በእጃችን ያሉትን ፥ እርዳታችንን ልንሰጣቸው የምንችላቸው ሰዎችን ሳይቀር እንድንተዋቸው የሚነግሩን ሰነፎች አሉ። እነዚህ ሰነፎች ሁልጊዜም አሉ። በኛ ማህበረሰብ ደግሞ በብዛት አሉ። ከእነዚህ ጋር ያለን ትግል ጥቅም የለውም። በመካከላችን የተማርን እና የነቃን ካለን ፥ ቤተሰቦቻችን ውስጥ የእህት ልጅ፣ የአክስት ልጅ፣ የአጎት ልጆች ካሉ ፥ እነርሱን መርዳት፣ ከቲክቶክ እና ኢንስታግራም ይልቅ መጽሐፍት ላይ እንዲያተኩሩ፣ የተሻለ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ካደረግን ቢያንስ በእጃችን ላይ ያሉ ነፍሳትን አድነናል። በዚህ ቤተሰብ ስኬት ብዙ ሌሎች ነገ ይነቃቃሉ። አካባቢያችን የኢትዮጵያኖች ቢዝነሶች ካሉ እነርሱን እናበረታታ። ነገ ልጆቻችን የሚያዩት እና የሚነሳሱት በኢትዮጵያዊ ስኬት ነው። ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት እና ከፍ ለማድረግ እንጣር። ጦርነትን፣ መለያየትን ለሚያበረታቱ የገንዘብ መቀነታችን አይፈታ። የእምነት ተቋሞቻችን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ማስፋፋት ላይ ሲያተኩሩ እንቢ እንበል። ይልቁንስ ትምህርት ቤት እንዲሰሩ ወይም እንዲገዙ እናስገድዳቸው። እኔ በበኩል በዚህ ጉዳይ ፍጹም አቋም አለኝ። ይሄ ባህል መቆም አለበት። ለምንድነው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያኖች ልክ እንደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት እና የነገው ትውልድ የሚፈጠሩበት ተቋሞች ላይ ማትሰራው? ኢትዮጵያዊ ተሰባሰበ ማለት ቤተክርስቲያን መግዛት እና መስራት ላይ ብቻ ለምን ያተኩራል? ይሄን ለባለፉት አርባ እና ሃምሳ ዓመታት አደረግን። ስደትን አላቆመ። ረሃብን አላቆመ። ከመንፈሳዊነት አንጻር ራሱ መከፋፈልን አላቆመ ወይም አንድነትን አልፈጠረ። ምክንያቱም መኃይምነትን የሚቀንሱ ተቋሞች ላይ ስለማንሰራ ነው። እንደዚህ ዓይነት ሃሳብ ለማንሳት ደግሞ ብቻችን ነን ብለን እናስባለን።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page