ዲፕሎማሲያችን ፦ ጭልፊቶችን የታቀፈች ዶሮ
- Mulualem Getachew

- Aug 10
- 7 min read
የሰንበት ዕይታ - 6

የአፍሪካ ልማት ባንክ ሁለት ከፍተኛ ኃላፊዎች በፋይናንስ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጠባቂዎች ታፍነው እንደተደበደቡ፣ ለዚህም ምክንያቱ ከ5.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለባንኩ የኢትዮጵያ ባንክ በተጭበረበረ የባንክ አካውንት ማስገባቱ እና ያ በሚኒስትሩ እና በባንኩ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊዎች መካከል የተፈጠረ መካረር ለዚህ ድብደባ እና መታፈን እንደዳረጋቸው በማህበራዊ ሚዲያ ሲገለጽ ነበር። እ.ኤ.አ በኦክቶበር 30 2023 የአፍሪካ ልማት ባንክ ባወጣው መግለጫ ሁለት ከፍተኛ ኃላፊዎቹ ተደብድበው መታፈናቸውን ገልጾ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ሲሰሙ ባደረጉት ፈጣን ጣልቃ ገብነት የታፈኑት ግለሶቦች መለቀቃቸውን ገልጿል። ነገር ግን ባንኩ በሰጠው መግለጫ ስለታፈኑበት ምክንያትም (ስለ 5.2 ሚሊዮን ዶላሩ) ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ ስለተሰራጨው ዜና ከመታፈናቸው እና መደብደባቸው ውጪ ያለው ነገር የለም።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ራሳቸው መኪና እየነዱ አህመድ ሽዴ እና ማሞ ምህረቱን አስከትለው የተደበደበው የባንኩ ኃላፊ ጋር እንደሄዱ እና በዚህም የአህመድ ሽዴ ጠባቂዎችን ደብዳቢዎቼ እነሱ ናቸው ብለው መለየታቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ተገልጿል። ይሄን ግን በባንኩም መግለጫ አልተገለጸም፤ ታማኒነት ካላቸው የመረጃ ምንጮችም ማረጋገጥ አልቻልኩም። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅም ጉዳት ቅነሳ (damage mitigation) በሚመስል መልኩ የራት ግብዣ ለተደብዳቢዎቹ አድርገዋል። ይሄ ሁሉ ግን ግለሰቦቹን ከሀገር ጥለው እንዳይወጡ አላደረጋቸውም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሚኒስትሮች በዚህ ደረጃ የሀገሪቷን አጠቃላይ ሉአላዊ ክብር እና ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ሥራዎችን የራሳቸውን ጠባቂ ተጠቅመው የሚያደርጉበት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማያውቁበት ሁኔታ ይሄን የማድረግ ድፍረት ሚኒስትሮቹ ከገቡ ፥ ሀገሪቷ ያለችበትን ሥርዓት አልበኝነት የሚያሳይ ነው።
በዛሬ ጹሁፌ በጥቂቱ መዳሰስ የምፈልገው ኢትዮጵያ በዓብይ ዘመን የገባችበትን የዲፕሎማሲ ውድቀት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤትን ክሽፈት ነው።
ዓብይ ከሕወኃት የተረከበው የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ኢትዮጵያን በጸጥታው ምክር ቤት ለአባልነት ያስመረጠ፣ በጎረቤት ሀገራትም ሆነ አጠቃላይ በአፍሪካ በብዙ መልኩ ዲፕሎማቲካዊ ተቀባይነቷ እየጨመረ የመጣ፣ በጸጥታ ጉዳይ፣ በስደት እና አከባቢያዊ ደህንነት (regional security) ፣ በኢኮኖሚ ልማት ከአፍሪካ የኢትዮጵያ ድምጽ የሚሰማበት ወቅት ነበር። በዓባይ ጉዳይ ከግብጽ እኩል ድምጻ የሚከበር ያደረጉ ዲፕሎማቶች ታይተዋል። በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ከተቀሰቀሱት ሕዝባዊ ተቃውሞች በፊት የነበረው የሀገሪቷ ዲፕሎማሲያዊ ቁመና በብዙ መልኩ አመርቂ የሚባል ነበር። ይሄም ቢሆን ሀገራችን ካላት አቅም፣ ታሪካዊ ማንነቷ እና መድረስ ከምትችልበት ልዕልና አንጻር ሲነጻጸር በጣም ትንሽ ነበር። ነገር ግን ወደ ኋላ ተመልሰን ያለፈውን ስንገመግመው ግን፤ በብዙ መጠን የተለየ እና የሚደነቅ ነበር።
በውጭ ጉዳይ መ/ቤት ውስጥ ለብዙ ጊዜ ሰዎች በዲፕሎማሲ መስክ ይቀጠሩ የነበሩት ባላቸው አካዳሚያዊ ብቃት ወይም ፖለቲካው ቅርበት ነበር። በሕወኃት ዘመን ብዙ አካዳሚያዊ ብቃታቸውን ያስመዘገቡ ልጆች ቀጥታ ከዩኒቨርስቲዎችም ሆነ ከሌሎች መስሪያ ቤቶች በዝውውር መልክ ወደ ዲፕሎማሲው አገልግሎት ገብተዋል። በተመሳሳይ ለሕወኃት ባላቸው ታማኝነትም ይሄን ዘርፍ የተቀላቀሉ ሰዎች ነበሩ። የ1997ኑን ምርጫ ተከትሎ፤ ዲፕሎማሲውን በአካዳሚክ ብቃታቸው የተቀላቀሉ ሰዎች ለቅንጅት ባሳዩት ውግንና መስሪያቤቱ ጥልቅ የሆነ ግምገማ አድርጎ ቀላል የማይባሉ ዲፕሎማቶችን አባረረ። ከውጭም የተጠሩ ዲፕሎማቶች የሚገጥማቸውን ጠርጥረው ሳይመለሱ በዛው ከዱ።
ይሄ የ1997 ምርጭ ነው የውጭ ጉዳይን የዲፕሎማሲ መስክ በመጠኑም የቀየረው። ዛሬ ድረስ የካድሬው ቡድን የሚባለውን ስብስብ ወደ መስሪያ ቤቱ አስገባ። በበረከት ስምዖን መልማይነት ከየክልሉ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ እና በሰዓቱ ያላቸውን አካዳሚያዊ ብቃት በመጠራጠር ሥራ ላለማጣት ኢህአዴግን ተቀላቅለው የነበሩ ካድሬዎችን መስሪያ ቤቱ በዲፕሎማትነት አስገባቸው። እነዚህ የካድሬው ቡድኖች በ1997 የተባረሩትን እና የከዱትን ዲፕሎማቶች ለመተካት በዙር የገቡ ነበሩ። ይሄ የመስሪያ ቤቱን መልክ ቀየረው ፥ ምንአልባትም እስከወዲያኛው።
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከቶሎ፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ ወደ ሚኒስትርነት ሲመጣ ፥ ዲፕሎማሲው ገጥሞት የነበረው የሰው ኃይል ጥራት ኪሳራ ከፍተኛ የሚባል ነበር። የካድሬው ቡድን በአመዛኙ ኖት ቨርባል በእንግሊዘኛ መጻፍ የማይችል፣ ጆሮውን ቢቆርጡት እንግሊዘኛ የማይሰማ እና እምብዛም ‘critical thinking’ ችሎታ ያልነበረው ነበር (ከእነዚህ ውስጥ ጥቂት ብቃት ያላቸው ሰዎች ግን ነበሩ)። በዚህ ሰዓት ነው በአምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶ አማካይነት (በሰዓቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካል ዘርፍ ስቴት ሚኒስትር የነበረ) አዳዲስ ዲፕሎማቶችን ለመመልመል ታቅዶ ወደ ሥራ ተገባ። በዚህም የዲፖሎማቲክ ማሰልጠኛ ተቋም ተቋቁሞ፣ በትምህርት ችሎታቸው ከ3.2 ጂፒኤ በላይ ያላቸው እና ሁለት ዙር ፈተና (አንድ የጹሁፍ አንድ የቃል) ተቀምጠው ማለፍ የቻሉ ወጣቶች ተቋሙን ተቀላቀሉ።
መስሪያ ቤቱ በካድሬው ቡድን እስከቴዎድሮስ መምጣት ድረስ ገጥሞት የነበረውን ከፍተኛ የሰው ኃይል ጥራት ክፍተት እነዚህ ወጣቶች በተወሰነ መጠንም ከአንድ ዓመት ስልጠና በኋላ ማስተንፈስ ቻሉ። ምንም እንኳ አብዛኞቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ ጥቂቶች ደግሞ ከክልሎች ዩኒቨርስቲዎች ጥሩ ውጤት ያመጡ ልጆች ቢሆኑም፤ የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት መላሸቅ ግን በአዲሶቹ ዲፕሎማቶች ጥራት ላይም የራሱ ጥላ ነበረው።
እነዚህ ዲፕሎማቶች ለመስሪያ ቤቱ እና ለሀገራችን ዲፕሎማሲ ውጤት ማምጣት በጀመሩበት የአራት እና አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው፤ የዓብይ መንግስት ሥልጣን የተረከበው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ላይ ከወጣ ቀን ጀምሮ ግልጽ ያደረገው ለውጭ ጉዳይ መ/ቤት በጎ ምልከታ እንደሌለው ነበር። ሰውዬውን በቅርብ ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ስለዚህ ጉዳይ ማውራት ብችልም ምክንያቱ ግን ለእኔ ግልጽ አይደለም። አንድ ነገር ግን አውቃለው። ዓብይ አህመድ ሥርዓት እና ደንብ፣ ፕሮሲጀር ይጠየፋል። አንድን ነገር ለማድረግ ሥርዓት አለው፣ ሂደት አለው፣ ዘው ብለህ እንደፈቀድክ አታደርግም፣ ከአለባበስ እስከ ሰላምታ አሰጣጥህ፣ ከማንኛውም የሰውነት ቋንቋ እስከ መመገቢያ ጠረጴዛ ላይ ሹኪያ አቀማመጥህ ድረስ ትርጉም አለው የሚለውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ደንብ እና ያን ዓይነት የሥርዓት አካሄድ ይጠየፋል። ነጮች እንደሚሉት ግለሰባዊ (personal) ነው የሚያደርገው። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በፈረንሳይ ቤተመንስግት በተደረገለት ግብዣ ወቅት ምግቡን ቢጨርስም የሹኪያ አቀማመጡ ልክ ስላልነበረ አስተናጋጆቹ የመመገቢያ ሳህኑን ሳያነሱ ይቀራሉ፣ ይሄም ሁሉንም ሂደት ማስተጓገል ይጀምራል፣ ማለትም የሌሎች ሳህንም ሳይነሳ እና ወደ ውይይት ሳይገባ ደቂቃዎች ይነጉዳሉ። በዚህ ወቅት ነው የዛሬዋ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ብድግ ብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ሲነግሯቸው ወዲያው ታርመው ሳህናቸው ሊነሳ እና ወደ ውይይት ሊገባ የተቻለው።
እነዚህን የመሰሉ ጥቃቅን ነገሮች በዲፕሎማሲ ትልቅ ውጤት አላቸው። ሀገሪቷ ሁሉ የራሱ ንብረት ነው የምትመስለው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ግን እነዚህ እንደተራ አላስፈላጊ ጉዳዮች ነው የሚያያቸው። ብድግ ብሎ ማቀፍ፣ ጺም ማሻሸት፣ ቀለበት ማድረግ፣ አጎንብሶ ማውራት፣ ቡና ማቅረብ ምንም ትርጉም ያለው አይመስለውም። ሲ ኤስ ሉዊስ ሰው ለሰውነት እንቅስቃሴው ትርጉም እንዳይሰጥ ማድረግ ትልቁ የሰይጣን ስትራቴጂ ነው ይላል። ምክንያቱም የሰው ነፍስ በሰውነቱ እንቅሳቃሴ የተወሰነች ናት። ያን ሰው ሲረሳ ነፍሱን ያደክማታል ይላል። ይሄን የሲ ኤስ ሉዊስ እዚህ ጋር ያነሳውት የኦክስፎርዱ ሊቅ ሉዊስ እንዴት የሰው አዕምሮ ከሰው ሰውነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ካሳየበት በላይ ፥ የሺ ዘመን የዲፕሎማሲ ልምድን ያለምንም እውቀት እና ምርምር እንደተራ ኤቲኬት (etiquette) በመቁጠር ለማጥፋት መጣር ጥልቀት የሌላቸው ሰዎች ባህሪ መሆኑን ለማሳየትም ነው።
ዓብይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመጣ፤ የሲቪል ሰርቪስ ምሩቅ (የመመሪቂያ ወረቀቷን የሰራላት ባልደረባዬ ነው) የሆነችው እና በዘር ድልድል በካናዳ አምባሳደር ተደርጋ የተሾመችውን፣ ከዛም በከፍተኛ የአቅም ማነስ ክስ ከካናዳ አምባሳደርነት ተነስታ፣ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በተራ ሠራተኝነት ሳይቀር አልቀበላት ብሎ፤ ኦሮሚያ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚሽን ውስጥ የተቀጠረችውን አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዳዲን ውጪ ጉዳይ ስቴት ሚኒስትር አድርጎ ጉብ አደረጋት። የሷ ሹፌር የነበረው እንዳጫወተኝ ፥ በገዱ አድርጋቸው ጊዜ ቤተመንግስት ዓብይ ጋር ሳትሄድ የምትውልበት ቀናት ጥቂት ነበሩ። በተለይ በፕሮቴስታንት እምነት ምክንያት ከዓብይ ሚስት ዝናሽ ጋር የቀረበ ግንኙነት አላት። የተቀመጠችበ ዘርፍ የሰው ኃይል ሚኒስቴር ዴኤታ ቢሆንም (ምንም የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካል እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች የማይመለከቷት ቢሆንም) ከሚኒስትር ደመቀ መኮንን በላይ ከዓብይ አህመድ ጋር የዞረችው እርሷ ነች። ይሄ ማለት የፖለቲካ ዘርፍ ሚኒስትሩ አምባሳደር ምስጋናው እያለ ማለት ነው። በቅርብ ወደ አንድ ዲፕሎማት ጓደኛዬ ደውዬ ስለደመቀ ስጠይቀው ከዚህ በፊት ያለኝን ነው የነገረኝ፤ ምን ባክህ “እሱ የብርቱካን ልጣጭ ነው።”
ዓብይ አህመድ መስሪያ ቤቱን ያዳከመበት መንገድ አንዱ ምንም ስለውጪ ጉዳይ እውቀትም ሆነ ልምድ፣ የሥራ ተጋላጭነትም የሌለውን ገዱ አዳርጋቸውን ከላይ አስቀምጦ ፥ ሌላ ከገዱ የባሰች ሴትዮን በሚኒስትር ቦታ አስፍሮ በውስጡ ያሉ ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶች እንዲማረሩ እና የውጭ ጉዳይ አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጥገኛ እንዲሆን ነበር። በርግጥ ገዱ አንዳርጋቸው የመ/ቤቱን ክብር ለማስጠበቅ፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የሚደርስበትን ጫና ተቋቁሞ፣ ብዙ ሙያተኞች ከውስጥ እንዲያድጉ ያደረገ ሰው ነበር። በዚህም ሙያተኞችን በመስማት እና ቦታ በመስጠቱ የሚያመሰግኑት ቀላል የማይባሉ ናቸው።
በዚህ ወቅት የትግራይ ጦርነት መጣ። ቀላል የማይባሉ ብቃት ያላቸው የትግራይ ልጆች ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክ ነበሩ። መንግስት እነዚህ ዲፕሎማቶች ተቋሙን ተጠቅመው ሕወኃትን እያገዙ እና የመንግስትን የዲፕሎማሲ አቅም እያዳከሙ እንደሆነ መረጃ ይደርሰዋል። በዚህም ዘዴ ተፈየደ። መንግስት ነጥሎ አንድን ብሔር ከሚያባር ፥ ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው የሚል ዘዴ። ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እ.ኤ.አ በጁላይ 5 2021 ዓ.ም. ፓርላማ ተገኝቶ አብዛኛው ኤምባሲ እንደሚዘጋ እና ዲፕሎማቶችም ከሀገራቸው ሆነው እንደሚያገለግሉ ለፓርላማው ገለጻ አደረገ።
ይሄን የሰሙ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ዲፕሎማቶች ወደ ሀገር ሳይመለሱ በዛው ቀሩ። ቀላል የማይባሉ የኦሮሞ ተወላጆች ሳይቀር ፥ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ከሀገር ቤት የሚሰራ ዲፕሎማሲ አልታይ ስላላቸው በዛው ሳይመጡ ቀሩ። ነገር ግን መንግስት በዋነኝነት ይሄን ያደረገው ለማጥራት ስለነበረ፤ ወደ ሀገር ቤት የተጠሩት አብዛኛው ዲፕሎማቶች ተመልሰው ተመደቡ። ከጥቂቶች በቀር ብዙም ኤምባሲዎች ሳይዘጉ ቀሩ (ቆንስሎች በአብዛኛው ተዘግተዋል)።
በተለይ በዶ/ር ቴዎድሮስ ዘመን ተመልምለው በብቃታቸው የገቡ ወጣት ዲፕሎማቶች ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል። የእነዚህ ልጆች አንዱ ብቃት ማሳያ ቀላል የማይባሉ ወጣት ዲፕሎማቶች በአሜሪካ Ivy league ስኩሎች ሳይቀር (እንደ ኮሎምቢያ እና ኖተርዳም) ሙሉ ስኮላርሽፕ አግኝተው ዛሬ እየተማሩ ያሉ መኖራቸው ነው፤ አንዳንዶቹም ፕሮፌሽናል ሥራ ላይ ተቀጥረው ጥሩ ተከፋዮች ሆነው የሚሰሩ ሆነዋል። እነዚህን ነው ኢትዮጵያ ያጣችው። ከትግራይ ጦርነት በኋላ ያለው ዲፕሎማሲ አቅሙ የላሻቀ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ ፍቃድ የሚመራ፣ በውጭ ጉዳይ ደግሞ ለብርቱካን አያኖ የማይሰግድ እና ወሬ የማያቀብል የዲፕሎማሲ ዕድገቱ አደጋው ውስጥ የገባበት፣ ተቋሙ ወጣት ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶች ገብተው ፍሬያቸው መታየት ሲጀምር ፥ ጨለማ ውስጥ ተመልሶ የገባበት ሆኗል።
በውጭ ጉዳይ በነበረኝ ቆይታ ሁሉንም ሊባል በሚችል ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሚኒስትር መስሪያቤቶችን ጎብኝቻለው፣ አይቻለው። በአንድ ወቅት ከአውስትራሊያ የመጣ እንግዳ ይዜ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ቢሮ ውስጥ ስገባ፤ ጸሐፊዋ የቡና ሲኒዎችን በሳፋ አድርጋ የቢሮ ጠረጴዛ ላይ ታጥባለች። በቀጠሮ እንደመጣን ነግሬያት፣ በዚህ ሰዓት ይሄን ማድረጓ ለገጽታ ነውር እንደሆነ ስነግራት፣ ሳፋውን ይዛ የቢሮው መስኮት ላይ ራሷን በመጋረጃ ከልላ ማጠቧን ቀጠለች።
ይሄን የጠቀስኩት፣ በትዝብቴ ሁሉ ያየውት በሥርዓት በመስራት፣ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ሀገራቸውን በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ሲያገለግሎ የነበሩ እንደ ጋሽ ውሂብ ሙሉነህ ያሉ ድንቅ ሙያተኞችን የምታገኙበት፣ ስለኢትዮጵያ የትኛውም ድንበር እና የድንበር ውል ጥያቄ ሲኖራቹሁ በራቸውን አንኳኩታችሁ መጠየቅ ብቻ የሚጠበቅባችሁ ድንቅ ሰዎች የነበሩበት መስሪያ ቤት አላየውም። አልገጠመኝም።
ከልባቸው ሀገራቸውን የሚያገለግሉ፣ ከእውቀት ያልተነጠሉ ሰዎች ለብዙ ዘመን ሲሰሩ የምታገኙበት በኢትዮጵያ ውስጥ ውጭ ጉዳይ መ/ቤት ነው። እውነት ነው ዲፕሎማሲው የሚሰጠው የውጭ ምደባ ዕድል እና የውጭ ተጋላጭነት ከሌሎች ሚኒስትር መ/ቤቶች በላይ ሰዎች በዛ እንዲቆዩ አድርጓቸው ይሆናል። አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ግን እነዚህ ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶች በየትም ሥፍራ ከዛ ያልተናነሰ ማግኘት ይችላሉ። በተለይ በሀገር ውስት በሚቆዩባቸው አራት ዓመታት የሚሰጣቸው ደሞዝ እና የኑሮ ድጎማ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ክብረ ነክ ነው። ግን የእነሱን ሞራል በማላሸቅ ብቻ የበላይ መሆን የሚችሉ ሰዎችን ሚኒስትር አድርጎ መንግስት ስለሚሾም ፥ እነዚህን ኢንቴሌክቿል ካሊበራቸው ከፍ ያለ ዲፕሎማቶችን ከመ/ቤቱ ለቀው እንዳይሄዱ የሚደረግ ምንም ጥረት የለም።
ከዛ ይልቅ የሊሴ ተማሪ እና የፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነችውን የኢትዮጵያ በፓሪስ አምባሰደር ማህሌትን ከአትዮጵያ ኤርፖርት ወደ ምደባዋ ፈረንሳይ በምትሄድበት ሰዓት በመመለስ እና ባልታወቀ ምክንያት መውጣት አትችይም ብሎ በማፈን ሌሎች የብልጽግና አባል ያልሆኑ ዲፕሎማቶቹ በከፍተኛ ፍርሃት እና ለነገ ማረፊያቸው በማሰብ ውስጥ እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል።
አክሊሉ ሀብተወልድን፣ ዶ/ር ሚናሴን፣ ከተማ ይፍሩን፣ ኮነሬል ጎሹን የሚያህሉ ለሀገር የከበዱ ሰዎች መሪ የሆኑበት ፥ እነ እጓለ ገብረዮሐንስ (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ መጽሐፍ ጸሐፊ)፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ዲፕሎማት ኦፊሰር ሆነው የሰሩበት ያ ተቋም ዛሬ ሀሳቧን በአግባቡ መግለጽ በማትችል በብርቲካን አያኖ ሲመራ ማየት ያስደነግጣል።
ዛሬ ድረስ በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ዲፕሎማት ሆኖ የሚያገለግል አንድ አለቃዬ የነገረኝ እና በሕወኃት ዘመን መ/ቤቱን የለቀቀ አዕምሮ ብሩህ የሆነ የሕግ ባለሙያ ዲፕሎማት የተናገረውን የጹሁፌ መዝጊያ ላድርግ።
ይሄ የሕግ ባለሙያ መልቀቂያ እንዳስገባ ሲሰማ፣ አለቃዬ እንዳይለቅ ይማጸነዋል። በዘረኝነቱ ምንም ብትማረር ለኢትዮጵያ ግን ታስፈልጋታለህ ሲል ተማጸነው። “ይሄውልኽ የጭልፊትን እንቁላል ወስደው ለዶሮ አሳቀፉት። ሁሉም ተፈለፈሉ። ሲያየው በቁመት፣ በጉልበት፣ በክንፍ ጥንካሬ ከጫጩቶቹ ይለያል። ወገኖቹ አልመስሉት አለው። አሻግሮ ሲያይ ደግሞ እሱን የሚመስሉ የጭልፊት ጫጩቶች ተመለከተ። እነዚያ ይበራሉ። እሱንም ይመስላሉ። ሲመለከት እነዚህ አይበሩም ፥ ድኩማን ናቸው። ከዛ አይ የኔ ቦታ ከጭልፊቶች እንጂ ከጫጩቶች አይደለም ብሎ ለቆ ሄደ” አለው። የኔም ቦታ ከጭልፊቶች እንጂ ከጫጩቶች አይደለም ብሎ መስሪያቤቱን እስከወዲያኛው ለቀቀ። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ እና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጭልፊቶችን የታቀፈች ዶሮ ይመስላል።






Comments