ቃየን እና አቤል
- Mulualem Getachew

- Aug 10
- 2 min read
የሰንበት ዕይታ - 12

በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ላይ ያለ ታሪክ ነው። ምንድነው ይሄን ታሪክ ስታነቡ የሚደንቃችሁ? ለምን የቃየንል መሥዋዕት እግዚአብሔር እንዳልተቀበለው? ወይስ ለምን የአቤልን መሥዋዕት እንደተቀበለው?ወይስ ቃየን ላይ እግዚአብሔር ያደረገበት ምልክት ምን ይመስል ነበር?
አሁን አሁን በጣም መማር ያለብኝ ሥርዓት (discipline) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ትኩረት እንዳናረግበት የፈለጉትን የታሪክ ክፍተቶች ትኩረት አለማድረግን ነው። ያልተሰጡንን የታሪክ ክፍተቶች ለመሙላት በጣርን ቁጥር፣ ከመጽሐፉ ዓላማ እየወጣን (distracted) መሆናችንን ማወቅ አለብን። እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት መጣር ለምርምር አስደሳች ይሆናል። እግዚአብሔር ግን እንዳናተኩርባቸው የፈለጋቸው ጉዳዮች ናቸው። ለምሳሌ ቃየን ያገባት ሴት ከየት መጣች? ከተማን ለመመሥረት የሚያስችል ሰዎች ከየት መጡ? የእነዚህን መልስ ማወቅ ያስደስት ይሆናል።
የዘፍጥረት ጸሐፊ (ሙሴ) ግን እየነገረን ያለው ይሄ የመጽሐፉ ትኩረት እንዳልሆነ ነው።
የቃየን እና የአቤልን ታሪክ ሳነብ ከሚመጡብኝ ጥያቄዎች አንዱ፣ ጸሐፊው እንድናተኩርበት ከፈለገው ታሪክ ውስጥ የሆነው ነው። ይህም የአቤልን ገዳይ ቃየንን እግዚአብሔር ወዲያው እንዳልገደለው። ያ ብቻ ሳይሆን ነፍሰ ገዳዩን ቃየንን ሌሎች ሰዎችም እንዳይገሉት እግዚአብሔር ምልክት እንዳደረገበት። ቃየንን የሚገድል ሰባት እጥፍ እንደሚበቀልበት ነው የነገረን።
እግዚአብሔር ክፋትን ወይም ክፉን ወዲያው ማጥፋት እንዳልፈለገ ከዚህ ታሪክ ማየታችን ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያው ሰማዕት የሃይማኖት ሰማዕት ነው። ማለትም ስለእምነቱ ነው የመጀመሪያ ሰው የተገደለው። በእምነቱ በተገደለ ሰው መገዳደል ወደ ምድር ገባ። በአምላኩ በመወደዱ ነው አቤል የተገደለው። የመጀመሪያውን ክፉ ነገር ከሰው የተቀበለው ሰው ስለጽድቁ ነው። በጣም ክፉ ስለሆነ ሳይሆን የመጀመሪያ ሰው የተገደለው፣ በጣም ጥሩ ስለሆነ ነው። ይልቁስ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ሌሎች እንዳይገዱለት እግዚአብሔር ፈለገ። ለምን?
መጽሐፈ ኢዮብ ላይ የሰው ልጅ የመጨረሻውን ክፉ ነገር ይቀበላል። ያም ሰው ኢዮብ ነበር። ለምን ብላችሁ ስትጠይቁ፣ "በጣም ጥሩ ስለሆነ ነው" መልሱ። ክርስቲያኖች ይሄ የታሪክ ሂደት ለእናንተ አዲስ አይደለም። የሃይማኖታችን ራስ እኮ የተገደለው ንጹሁ ስለሆነ ነው።
ክፉስ ቃየን?
የእንክርዳዱን እና የስንዴውን ታሪክ ስንቶቻችን እናስታውሳለን? (ማቴ 13፥24)። ክፉም ደጉም አብረው እንዲቀጥሉ እግዚአብሔር ለምን ፈለገ? እግዚአብሔር እንክርዳዱን በኛ ሰዓት እንዳንነቅል የፈለገ እንደሆነ እየገለጸልን አይደለምን? በግለሰብ ተነሳስተን ክፉን በራሳችን ወስነን፣ እኛው እርምጃ እንዳንወስድ እያዘዘን አይደለምን? ይሄስ በጦርነት ከመሳተፍ፣ ለነጻነት ከመታገል ጋር እንደምን ታስታርቁታላችሁ? ከሞአብ እስከፍልስጤም የተዋጉት እስራኤሎችስ ከዚህ አንጻር እንዴት ይታያሉ?
አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። ክፉ ከደጉ ጋር አብረው መኖር እንደሚቀጥሉ። ይሄንንም የፈቀደ እግዚአብሔር መሆኑ። ክፉም በርሱ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ። በበቀል ስሜት ክፉን ሰው መግደል እንደሌለብን፣ ይልቁስ ያን በቀል እግዚአብሔር በሰዓቱ እንደሚያደርግ ነው ይሄ ታሪክ የሚነግረን። "እንክርዳዱን ተውት፣ ቃየንን አትግደሉት" ነው የተባልነው፤ እግዚአብሔር በጊዜው የአቤልን ገዳይ ይበቀለዋል። የበቀል ጦርነት የሚባል ክርስቲያኖች የሚሳተፉበት ጦርነት የለም።
ክርስቲያኖች ከበቀል ውጪ ባለ ጦርነት ውስጥ መቼ እንደሚገቡ ከዚህ በፊት ጽፌያለው።






Comments