ገልብጦ ማሰብ
- Mulualem Getachew

- Aug 10
- 3 min read
የሰንበት ዕይታ - 11

ሰዎች ስኬታማ ሕይወት ለመምራት ይፈልጋሉ ወይም ይጥራሉ። ብዙ ሰዎች ለተመሳሳይ ግብ በሚሮጡበት ዓለም ያን ግብ ማሳካት በጣም ከባድ ነው። ሳይንቲስቶች ችግር ሲገጥማቸው ፥ ከዛ ችግር ለመውጣት የሚጠቀሙበት ጥሩ ጥያቄ አላቸው። ይሄም “ምንድነው ለማሶገድ እየጣርኩ ያለውት?” የሚለውን ጥይቄ ነው። የምንሰራቸውን ሥራዎች ሁሉ ከማድረጋችን በፊት ይሄን ጥይቄ እንጠይቅ። “ምንድነው ግን ይሄን ሥራ በመስራት ለማሶገድ እየጣርኩኝ ያለውት?” ለምሳሌ ሀብታም ለመሆን እንፈልግ ይሆናል። ሀብታም ለመሆን የምንጥረው ምን ለማሶገድ ነው?
ብዙዎቻችን ዋነኛ ፍላጎታችን ድህነትን ማሶገድ ነው። ይሄ አስተሳሰብ የሚረዳን ሀብታም ላለመሆን እንቅፋት የሆኑብንን ቀላል ነገሮችን ያሶግድልናል። ድሀ ላለመሆን ቀላሉ ነገር ፥ “ከምታስገባው በላይ አለማውጣት ነው፣ ከፍተኛ ኢንተረስት ሬት ያላቸውን ብድሮች ማሶገድ ወይም ቶሎ ከፍሎ መገላገል፣ መቆጠብ መጀመር ነው”፥ እነዚህ ቀላል ነገሮች የመጀመሪያውን በሽታ ያሶግዳሉ። እሱም ድሀ መሆንን። ይሄን ጥይቄ በሌሎች ስራችንም ላይ እንጠይቅ። ለምሳሌ ለሰው በጣም ትለፊያለሽ ፥ በዚህም የራስሽን ጤና አደጋ ውስጥ ሁሉ ትከችያለሽ። “ምን ለማሶገድ ነው ይሄን ሁሉ የሆንሽው?” ምን አልባት ያ ሰው እንዳይቀየምሽ ወይም ያ ሰው እንዳይታዘብሽ ይሆናል ይሄን ሁሉ ክፍያ የከፈልሽው። ስለዚህ መቀየምን ለማሶገድ ራስን ጎድቶ የሆነ ነገር ከማድረግ ውጪ ያለ ሌላ አማራጭ የለም? በግልጽ ማውራት፣ ያለብሽን ፈተና ለዛ ሰው ማስረዳት የበለጠ እንዲወድሽ ሊያደርግ ሁሉ ይችላል። ብዙ ጊዜ ግን እኛ የምናደርገው ይሄን ነው፤ የሆነ ነገር ለማድረግ እናስባለን። ከዛ እሱን ለማድረግ የሚያስችሉ ነገሮችን እንሰራለን። ለምን ማድረግ እንደፈለግን ወይም ምን ለማስቀረት እየጣርን እንደሆነ አናስብም። ከዛ በዋናነት ደግሞ የምንፈልገውን ነገር ለማሳካት “ምን እንቅፋት ሊሆነን እንደሚችል” ፈጽሞ አንገምትም።
ለምሳሌ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት እናስባለን። ለዚህ የሚያስፈልገው ጥሩ አልጋ እና ወደ አልጋ መሄድ ላይ ብቻ ይሆናል የምናተኩረው። ጥሩ አሳቢ ስንሆን ግን ሦስተኛ ደረጃ እርከንን እናስባለን። “ጥሩ እንቅልፍ ላለመተኛት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ምንድናቸው?” የሚለውን። “ስልክ ይዞ ወደ አልጋ መሄድ፣ ከስልክ እና ከቲቪ የሚወጣው ብሉ ላይት፣ በማታ ፕሮቲን ያለበት ምግብ መብላት፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ”፤ ስለጥሩ እንቅልፍ ስናስብ እነዚህ ነገሮች ቶሎ አዕምሮአችን ውስጥ አይመጡም። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የምናስበው አንድን ነገር ስለማሳካት ነው እንጂ ምን ነገሮች ያን ነገር ከማሳካት እንደሚያሰናክሉት አይደለም።
ቻርሊ መንገር አንድ የሚለው ጥሩ አባባል አለው። “ማወቅ የምፈልገው ብቸኛ ነገር የት እንደምሞት ነው፤ ስለዚህ እዛ ፈጽሞ አልሄድም።” ይሄ ነገሮችን ገልብጦ የማሰብ ዘይቤ የመነጨው ካርል ጉስቶቭ ጃኮብ ከተባለው የጀርመን የሒሳብ ሊቅ ነው። ጃኮብ ከባባድ የሆኑ የሒሳብ ጥያቄዎችን የፈታው በቀላል ስትራቴጂ ነው። “man muss immer umkehren” (invert, always invert) “ገልብጠው፣ ሁልጊዜ ገልብጠው” እንደማለት ነው። ጃኮብ የተገነዘበው ነገር ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶች የሚፈቱት ነገሮችን ከኋላ ወደፊት በመመልከት እንደሆነ ነው። ብዙ ችግሮች ከችግሩ ተነስተን ወደፊት (forward thinking) በማሰብ የሚፈቱ አይደሉም። መገልበጥ ይሻሉ።
ለምሳሌ በተቋማቹ ውስጥ የፈጠራን ክህሎት ማዳበር ትፈልጋላችሁ። ፈጠራን ለማዳበር ማድረግ ያለባችሁን ዘርዝራችሁ ታስባላችሁ። ወደፊት ማሰብ ማለት ነው። ግን ይሄን ጉዳይ ገልብጣችሁ እዩት። “ፈጠራን ለማቀጨጭ ወይም ለማዳከም ምን ምን ማድረግ አለብን?” ብላችሁ አስቡ እስቲ። ቢሳካላችሁ እነዚህ ፈጠራን የሚያቀጭጩ ተግባሮችን አለማድረግ ነው። በተመሳሳይ “ምንድነው ጥሩ ሕይወትን የሚሰጠን? የሚለውን ከማሰብ ይልቅ “ምንድነው መጥፎ ሕይወት እንዲኖረን የሚያደርገው?” የሚለውን አስቡ። እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችን መጥፎ ሕይወት እንዲኖረን የሚያደርጉ ብዙ ሥራዎችን ዛሬ እየሰራን ነው። ማህበራዊ ሚዲያ ከተገቢው መጠን በላይ ከመጠቀም ጀምሮ።
በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚያደርሰን ስማርት ወይም ብሩሕ አዕምሮ እንዲኖረን በመጣር አይደለም። ደደብ ነገሮችን ከመስራት በመቆጠብ ነው። ለምሳሌ “ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያላቃት ምንድነው?” ብላችሁ ከምታስቡ “ኢትዮጵያን ድህ አድርጎ ሊያስቀራት የሚችለው ምንድነው?” ብላችሁ አስቡ። ይሄን ጥያቄ ሁላችን በቀላሉ እንመልሰዋለን። በእርስ-በርስ ጦርነት የሚታመስ ሀገር መቼም ቢሆን በልጽጎ አያቅም። አንድ ሀገር መጥቀስ የሚችል የለም። ሀገራትን ወደ ብልጽግና ለመምራት ግን መቶ አይነት እርስ በእርሱ የሚጋጩ የብልጽግና ንድፈ ሀሳቦችን እና ፍልስፍናዎችን ልታመጡ ትችላላቹ። አንዱን መርጣችሁ በሀገራችን በደንብ ልትተገብሩ ትችላላችሁ። ነገር ግን ሀገራትን ድሀ አድርጎ የሚያስቀርን ዋነኛ ድድብናን፣ ማለትም የእርስ በእርስ ጦርነትን እስካላቆምን ድረስ ብልጽግና የሕልም እንጀራ ነው። መቶ ጊዜ ስፖርት ብትሰራ፣ አጥንትህን የሚያዳክሙ ምግቦችን ከመመገብ እስካላቆምክ ወይም በሽታህን እስካልታከምክ ድረስ ስፖርት በመስራትህ ብቻ ጠንካራ አጥንት አይኖርህም። በተመሳሳይ “ምንድነው ጠንካራ ሀገር እንዲኖረኝ የሚያደርገው?” የሚለውን ትንታኔ ለጊዜው ገታ አድርግ እና “ምን ባደርግ ነው ደካም ሀገር የምፈጥረው?” ብለህ ጠይቅ። ከዛ እነዛን ነገሮች ከመስራት ተቆጠብ።
ይሄ አስተሳሰብ ነው ዋረን በፌትን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የአሜሪካንን የቢዝነስ ኢምፓየር እንዲመራ ያስቻለው። ድድብናችንን ማስቀረት ካልቻልን፣ ማለትም የምንሞትበትን ቦታ አውቀን ወደ ዛ መሄድ እስካላቆምን ፥ ብልሃታችን ከመጥፋት አይታደገንም።
ይሄ ደካማ አስተሳሰብ ነው ደርግንም ሆነ ዐብይን የጦር ሠልፍ በማሳየት እንዲጠመዱ ያደረጋቸው። ድድብናን ማሶገድ ሳይሆን ፥ ጉልበትን ማጠንከር ይመስላቸዋል የአሸናፊነት ምስጢር። ፈጽሞ።






Comments