
ከውድ ጓደኛዬ ጋር በቅርብ በስልክ ስናወራ አንዱ ርዕሳችን ሰዎች ማጣትን እና መተውን የሚወስዱበት መንገድ ነበር። ሰው በተፈጥሮ ማጣት ከማግኘት በላይ ይሰማዋል። አስር ሺ ብር ያጣ ሰው እና 12 ሺ ብር ያገኘ ሰው የሀዘን እና የደስታ መጠናቸው በጣም የተለያየ ነው። ያጣው ሰው የሚያዝነው ካገኘው ሰው ደስታ ይልቅ በብዙ እጥፍ ነው። ለምሳሌ ጠዋት ላይ 10 ሺ ብር አግኝተን ከሰዓት 5 ሺ ብር ብናጣ ፥ እጦታችን ሁሉመናችንን ይቆጣጠረዋል። በዚህም የተነሳ ሰዎች ብዙ ጊዜ በከሰረ ነገር ላይ ተጨማሪ ጊዜያቸውን ማጥፋት ይቀላቸዋል፤ ያ ነገር ላይ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ።
የዚህ አንዱ ማሳያ በመጥፎ ግንኙነቶች ውስጥ የምናጠፋው ጊዜ ነው። ቀላል የማይባሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከጎዷቸውሰዎች ጋር ወዳጅነታቸውን ይቀጥላሉ። እየጠቀማቸው ካለ ወዳጅነት ይልቅ፣ የተጣመመን ለማቅናት የሚወስዱት ጊዜ ይበልጣል። ስኬት ማለት ግን የሚሰራን ነገር በብዛት ማድረግ ፥ የማይሰራን ነገር በቶሎ መተው ነው። ለዚህ ደግሞ መጨከን ያስፈልጋል። ግራ የሚያጋቡንን ሰዎች፣ ፍላጎታቸውን በግልጽ ማኖር የከበዳቸውን እና ለወዳጅነታችን ያላቸው አክብሮት እምብዛም የሆኑ ግለሰቦችን መቁረጥ ፥ ስሜታችንን ከመጥቀሙ ባሻግር ለጥሩ ግንኙነቶች የበለጠ ጊዜ እና ዕድል እንድንሰጥ ያደርገናል። ይሄን ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ተፈጥሮአችን ማጣትን ከማግኘት በላይ ይፈራል። ስለዚህ ከተፈጥሮ ተቃራኒ መቆምን ይጠይቃል።
በኢኮኖሚክስ opportunity cost የሚባል ጽንሰ ሀሳብ አለ። ይሄ ማለት እያንዳንዱ ድርጊታችን እና ምርጫችን opportunity cost አለው። ከመጥፎ ወይም አሉታዊ ወዳጅነት ጋር የማሳለፍ opportunity cost ከጥሩ ወዳጅነት ጋር የማሳለፍ ነው። ከዛ ሰው ጋር የምናሳልፈው ሰዓት opportunity costቱ ጥሩ መጽሐፍ የማንበብ፣ ስሜታችንን የሚጠግኑ ነገሮችን የመስራት ሊሆን ይችላል። ግን ይሄን በማግኘት አናስበውም። በማክበር፣ በፍቅር፣ በታማኝነት እና በመልካም ቃላት ከጎናችን ሊሆኑ የማይችሉ ሰዎችን መተው (መቁረጥ) አለመቻል የሚያሳጣንን ነገር ማሰብ ለተፈጥሮአችን የተመቸ አስተሳሰብ ይሆናል። በመጥፎ ወዳጅነት ላይ የሚጠፉ እያንዳንዱ ደቂቃዎች ከጥሩ ወዳጅነት ጋር ልናሳልፋቸው የምንችላቸው ሰዓቶች እንደሆኑ ካሰባችሁ ፥ ለውሳኔ አሰጣጥ ይቀለናል።
ማቋረጥ፣ መተው፣ መልቀቅ፣ ተስፋ መቁረጥ የሚሉ ቃላት አሉታዊ (negative) ስሜት ብቻ ነው ያላቸው ብዙ ጊዜ። ለዚህ ነው አብረውን የሚሰሩ ሰዎችን፣ ወዳጆቻችንን ወይም የቅርብ ሰዎቻችን መተው እና ከእነሱ ጋር ማቆም የሚያስፈራን። ግን ለጥሩ ነገር ጅማሮ መጥፎ ነገር መቋረጥ ይኖርበታል። የበጎ ነገር መንደርደሪያ የመጥፎ ነገር ማብቂያ ነው። መጥፎ ነገር ወይም ለእነሱ የማይሰራን ነገር መተው ያልቻሉ ሰዎች ለእነሱ የሚሰራ እና በጎ የሚሆንላቸውን ለመጀመር አይችሉም። ቅድም እንዳልኩት በምንም መስክ ያለ ስኬት ማለት የሚሰራን ነገር አብዝቶ መስራት እና የማይሰራን ነገር መተው ነው።
በማይሰራ ነገር ላይ የምናጠፋው ጊዜ ከሚሰራ ነገር ላይ እየተቀነሰ እንደሆነ ካልገባን፤ ስለ አለን ውስን ሰዓቶች እና ሪሶርሶች ብዙ ግንዛቤ የለንም ማለት ነው። ሌላው ሰብአዊ ባህሪያችን የታዳጊነት እና ሰዎችን የመቀየር ስነልቦና እንዲኖር አድርጓል። እውነታው ግን ይሄን አስተሳሰብ የምንጠቀመው ሰዎች ከኛ የዓለም እይታ ጋር የሰመረ ባህሪ እንዲኖራቸው ነው። ወዳጆቻችን በራሳቸው ለራሳቸው የሚሆን ባህሪ ይዘው ይሆናል። ጥሩ ጓደኛ፣ ጥሩ ሚስት ወይም ጥሩ ቤተሰብ ላይሆኑ ይችላሉ። ግን እንደዛ የመሆን መብት እንዳላቸው መዘንጋት የለብንም። ብቸኛው ምርጫችን ያ ሰው ለኛ የሚሆን nurturing (ጠጋኝ) ባህሪ እንደሌላቸው መወሰን እና ያን ወዳጅነት ማብቃት ነው። ያ ሰው መጥፎ ስለሆነ ላይሆን ይችላል። ከኛ ጋር የሚስማማ ማንነት ግን እንዲኖረው ስላልመረጠ፤ የታዳጊነት እና ነገ ይሻሻላል የሚለው ባህሪያችን ያን ሰው ከኛ ጋር እንዲስማማ በማድረግ ጊዜያችንን በከንቱ እናጠፋለን።
በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ከቁጥር 11 ጀምሮ ያለው አፍቃሪው አባት ታሪክ ብዙ አስተማሪ የሕይወት ምክሮች አሉት። አንዱ ትምህርት ልጁ ወደ ሞት ቀጠና እንደሚሄድ እያወቀ ገንዘቡን ከፍሎ ሰጥቶ መሸኘቱ ነው። እኛ ብንሆን የምናደርገውን ተመልከቱ። ፈጽሞ ልጃችንን አደጋ ውስጥ አንከተውም። በሽማግሌ ማስመከር፣ ማሳፈር፣ በጭቅጭቅ እና በኃይል ፍላጎቱን እንዲተው ማድረግ ነው። ያ ምን ያህል ልቡ የከጀለን ሰው ያስቆመዋል? መቼም የሚሰራ ስትራቴጂ ግን አይደለም።
ሲ ኤስ ሉዊስ እንዲህ ይላል “እየሰመጠ ያለን ሰው ለመርዳት እስከሚሰምጥ መታገስ ያስፈልጋል። ያለመስመጥ ትግሉን ሳይጨርስ የእርዳታ እጅ መዘርጋት ፥ ራስን ለአደጋ ማጋለጥ ነው።” በተመሳሳይ ሰዎች የውሳኔያቸውን ክፉ ውጤት በአግባቡ ተመልክተው፣ ሪፍሌክት አድርገው፣ የኛን እርዳታ ለመቀበል እጃቸውን እስከሚዘረጉ ድረስ ለመርዳት እና ለመታደግ መጣር የመማርን እና ፍጹም የመቀየርን ዕድል ነው የሚዘጋው። ለዚህ ነው የታዳጊነት ፓራሹታችንን ያለ ሰዓቱ ላለመክፈት መጠንቀቅ ያለብን።
ሰዎች ለምርጫቸው ኃላፊነት የሚወስዱ እና ከዛ የሚማሩ ካልሆኑ፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ጉዳቱ ለኛ ብቻ አይደለም፤ ለእነዛም ሰዎች የመማርን እና የመለወጥን ዕድል ነው የሚነሳው።