በሀሳብ መጫወት
- Mulualem Getachew
- Oct 26
- 3 min read

የአዕምሮ ጅምላስቲክ ሕጻናት ጋር የተለመደ ነው። ምንም ነገር ያስባሉ። ምንም ነገር ለመሆን ፈቃደኛ ናቸው። ምንም ነገር ከመጣላቸው ይጠይቃሉ። እንደ ወፍ ለመብረር፣ እንደ ጉንዳን ለመዳህ፣ እንደ ጉዑዝ ነገር ለመድረቅ ፈቃደኛ ናቸው። ማሰሪያ የሌለው የሀሳብ ዋና ውስጥ ራሳቸውን ያስገባሉ።
አዋቂዎች ጋር ይሄ የተለመደ አይደለም። እንሸማቀቃለን። ትላንት የተናገርነውን ላለመቃረን ዛሬ ስህተት መድገም ይቀለናል። ብዙ ልጓሞች አሉብን። እንዲህ ሆኜ እንዴት እንደዚህ ሆናለሁ ብለን ራሳችንን ከፈጠራ እንገድባለን።
በዚህ ሳምንት ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ፤ እንዲህ ተባባልን። ብዙ አፍሪካኖች ወደ አሜሪካ መምጣት ይፈልጋሉ። ምንአልባትም በአንዳንድ ሀገሮች ሁሉም ሰዎች ከዛ ተነስተው ኢዚህ መግባት ይሻሉ። ለምሳሌ ይሄ ሀሳብ መጣልን። አሜሪካኖች እና አውሮፓኖች ለሁሉም አፍሪካኖች “እሺ ወደ ሀገራችን መምጣት ትፈልጋላችሁ። ሁላችሁም ኑ። እንደውም እናንተ የኛን ሀገር ውሰዱ። አሁን እንዳለው። ምንም ነገር ሳንቀንስ እንስጣችሁ። እናንተም የናንተን አፍሪካ ስጡን። ማለትም አሁን ባለንበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ቦታ እንቀያየር።”
ይሄ አይሆንም። ግን ቢሆን ምን የሚመስል ይመስላችዋል? በእኔ ግምት አሜሪካውያን እና አውሮፓውያን አፍሪካን ልክ ለቀው እንደሄዱበት ሀገራት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያደርጉታል። በተቃራኒው አፍሪካውያን አሜሪካንን እና አውሮፓን ያወድሙታል። የመጡበት አፍሪካን ያስመስሉታል።
የብዙ ሰው ግምት ይሄ የሚሆን ይመስለኛል። ለምን እንደዚህ አሰብኩኝ? ምክንያቱም አፍሪካ በዓየር ጸባይ እና በመልካ ምድር ምቹነት ከብዙ የአውሮፓ ሀገራት እና የአሜሪካ ስቴቶች የተሻለች ነች። ግን በዛ ምድር የምንኖር ሰዎች አመለካከታችን፣ ባህላችን እና የትምህርት ደረጃችን በጣም ዝቅ ያለ ነው። ሰጥቶ መቀበል የሚባለው ባህል፣ ስትራቴጂክ ሆኖ ማሰብ፣ የፖለቲካ ባህላችን እና መሰል ለሰው ልጆች በሰላም እና በብልጽግና የመኖር ዋስትና የሆኑ ከአዕምሮ የሚነሱ ሀብቶች ላይ በጣም ዝቀተኛ ነን።
ይሄ ለምን እንደሆነ በርግጠኝነት እኔ መናገር አልችልም። ብዙ ጥናት የሚሻው ይመስለኛል። የማውቀው አንድ ነገር ጥቁሮች ዝቅተኛ IQ ስላለን እንዳልሆነ ነው። ምክንያቱም በአውሮፓ እና አሜሪካ መጥተን እንደ ነጮች በእነሱ ዘርፍ ጥሩ የሆኑ ብዙ ስላሉ። በተለይ ጥሩ ትምህርት ገና በልጅነታቸው ያገኙ ሰዎች በብቃት ደረጃ ምንም አይተናነሱም።
ይሄ ዓይነት የሀሳብ ጨዋታ የሚጠቁመን ብዙ ነገሮች አሉ። አንደኛው የጎደሉንን ነገሮች ቆም ብለን እንድናስብ እና ችግሮቻችንን በተለየ መነጽር እንድናይ ያደርገናል።
ለምሳሌ በአሜሪካ ውስጥ ሁለት በጣም ሀብታም ስቴቶች አሉ። ኒው ዮርክ እና ካሊፎርኒያ። በአሜሪካ ውስጥ ሁለት በጣም ቅይጥ (diverse) የሆኑ እና ከነጩ ይልቅ ሌላው ማህበረሰብ በቁጥር የሚበልጥበት ስቴቶች አሉ። ኒው ዮርክ እና ካሊፎርኒያ። በደቡቡ የአሜሪካ ስቴቶች ውስጥ በጣም ሀብታሙ ከተማ አትላንታ ነው። በጣም ቅይጡ (diverse) ከተማም አትላንታ ነው። የአትላንታ ሀብት ብቻ በደቡቡ ካሉት ስቴቶች ሁሉ ይበልጣል። ደቡቡ እንደ ሚሲሲፒ፣ አላባማ፣ ሚዙሪ፣ አርካንሳ፣ ሉዊዚያና የመሰሉ ስቴቶች ከ90% በላይ ነጭ ሲሆን፤ እጅግ ደሃ ስቴቶች ናቸው።
ከዚህ ምን እንማራለን?
ለምሳሌ ወደ ሀገራችን እንሂድ። ሐዋሳ የዛሬ አስር ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት እያደጉ ከነበሩ ከተሞች አንዷ ነበረች። ብዙ ሀብታሞች መፈጠር እና ሆቴሎች፣ ንግዶች መስፋፋት ጀመሩ። የመሬት ዋጋ ሰማይ መንካት ጀመረ። ሐዋሳ የዛሬ አስር ዓመት የነበራት ቅይጥነት አስገራሚ ነበር። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሉ የስልጣን ቦታዋች በብዙ ብሔሮች የተያዙ ነበሩ። አንድ ዓይነት ነገር የለም። ማንም ቤቱ የሚመስለው ከተማ ሐዋሳ ነበር።
ከዛ ምን ሆነ? የክልል ጥያቄን ያነሱት ሰዎች ብዙ ስህተት ሰሩ። የክልል ጥያቄን መጠየቃቸው አይመስለኝም ስህተቱ። ይልቁንስ የከተማዋን የእድገት ምስጢር ፈጽሞ አለመረዳታቸው ነበር። ዛሬ የመሬት ዋጋ ወድቋል። ማውቃቸው ትልልቅ ባለሀብቶች ሁሉም ለቀው አዲስ አበባ ገብተዋል። ለመመለስም ፈጽሞ አያስቡም። ያሉትም መውጣት ይሻሉ። ለምን? መልሱ ግልጽ ይመስለኛል።
ኦሃዮ፣ ስፕሪንግ ፊልድ የዛሬ ስምንት እና ሰባት ዓመት የጎስት ከተማ እየመሰለ ነበር። የከተማው ባቡር ቆመ። ባዶ የሆኑ ቤቶችን መመልከት የተለመደ ሆነ። ፋብሪካዎች ተዘጉ። ከዛ ዲሞክራት ሲመጡ ከተማዋን ለማነሳሳት ከሄቲ የመጡ ስደተኞችን በገፍ ወደ ስፕሪግ ፊልድ ወሰዷቸው። ከተማዋ መነሳሳት ጀመረች። የከተማው ባቡር መንቀሳቀስ ጀመረ። የቤቶች ዋጋ ከፍ ማለት ጀመረ። ለምን? መልሱ ግልጹ ነበር። ከተማዋ በአዲስ መጤዎች ጉልበት እና የፈጠራ አቅም መነሳሳት መጀመሯ ነበር።
አንድ ብልህ መሪ ምንድነው የሚያደርገው? ከዚህ በፊት በሌሎች ቦታዋች የሰሩ ሙከራዎችን በርሱም ግዛት መሞከር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የትም ቦታ ብትሔዱ ከነባሩ ሕዝብ በላይ ለዛ አከባቢ መጤ የሆነው ማህበረሰብ ንግድ ውስጥ አለ። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የካቢኔ ስብሰባዎች የጻፈው አምባሳደር ዘውዴ ረታ የኢትዮጵያን የንግድ አውታሮች ተቆጣጥረው ይዘውት ስለነበሩ አረቦች ጽፏል። መጤዎች ነበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድ የተሳካላቸው። የአረቦች መብዛት ያስፈራው የንጉሱ ካቢኔ ሀሳብ ዘየደ። ይሄን ሀሳብ ለንግድ ሚኒስትሩ መኮንን ሀብተወልድ የነገረው አንድ የተማረ ጉራጌ ነበር። ጉራጌዎች የንግድ ክህሎት አላቸው። አረቦችን ሊተኩ የሚችሉት እነርሱ ናቸው። ስለዚህ አረቦችን ገፍትረን ከምናሶጣ ጉራጌዎችን አምጥተን ብድር እንስጣቸው። ከዛ ጎን ለጎን ሱቅ ይክፈቱ። በዓመቱ አረቦቹ ሲከስሩ በራሳቸው ለቀው ይወጣሉ አለው። የሀብተወልድ ልጅ ይሄን ሀሳብ ተቀበለ። መንግስት ጉራጌዎችን በገፍ አምጥቶ መርካቶ ላይ በማስፈር ብድር በመስጠት ንግድ እንዲሰሩ አደረገ። በዓመቱ አረቦች ከስረው በራሳቸው ጊዜ ለቀው ወጡ። መርካቶ ከአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል ሆነ።
ስለሀገሩ ትልቅነት የሚያስብ ሰው በሀሳብ ይጫወታል። የሰዎችን ዝቅተኛ የዘረኝነት እና የጎሳነት ስሜት በመጫር ሳይሆን ከእውነት ጋር ማህበረሰብ እንዲጋፈጥ ያደርጋል። መጽሐፉ ቅዱስ የስደት ታሪክ የተከተበበት መጽሐፍ ነው። ሰዎች ከእናት አባታቸው ተለይተው ታላቅ የሆኑበትን ታሪክ የምናነብበት መጽሐፍ ነው። በሀገራችንም ከቀዬ ውጣ ከምንል ይልቅ ወደ ቀያችን እና መንደራችን አዳዲስ ማህበረሰቦች እንዲመጡ፣ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፉ ላይ ገብተው እንዲወከሉ ብናደርግ ተዓምር መስራት እንችል ነበር።
ከኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፣ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር እየመጡ በነጻነት እንደ ዜጋው ንግድ ውስጥ እንዲገቡ፣ የራሳቸውን ባህል እና ማንነት እንዲያጎለብቱ ብንፈቅድላቸው ተዓምራዊ ለውጥ ማየት እንችል ነበር። ከቦታ ቦታ ሰዎች እንደልብ ተዟዝረው መስራት እና ሀብት ማፍራት ቢፈቀድላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከተሞች ተዓምር መስራት ይችላሉ።
ዛሬ በስደተኞች ታላቅ የሆነችው ሀገረ አሜሪካ የታላቅነቷ መሠረት የሆነው ስደት ላይ በሯን እየቆለፈች ነው። የዛሬ ዓመት የነበረው የኢኮኖሚ መነቃቃት ዛሬ የለም። በሁሉም ከተሞች ድብታ እየሰፈነ ነው። ኢኮኖሚው በጣም ተቀዛቅዟል። እስከዛሬ የነበረው የአሜሪካ ብልሃት ነገሮች እንዲህ ሲከፉ መንገዳቸውን (course) ቶሎ ማቃናት ይችላሉ። አሁንም ሳይረፍድ ዘረኝነት ያነሳሳው እብደት እና ዕውረነት ይሰክናል የሚል እምነት አለኝ።


