top of page
Search

ደግነት

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • 2 days ago
  • 3 min read
ree

አሸናፊው ስብዕና ነው ደግነት። በዚህ ምድር ላይ ሰውን ወደ ሕይወታችሁ ለማስጠጋት አንድ መለኪያ፣ አንድ ሜቲሪክ፣ አንድ ሚዛን ብቻ ቢኖራችሁ። ያ ደግነት መሆን አለበት። ጥሩ ነገሩ ብዙ መለኪያዎች አሉን። ግን ደግነት የጎደለው ሰው ሁሉ ነገር ቢኖረው እንኳ በፍጹም ወደ ሕይወታችን መግባት የለበትም። ደግነት የሰው ልጅ የመልካምነቱ ውሃ ልክ ነው። ምንም እውቀት ቢኖረው ሰው ደግ ካልሆነ በዚህ ዓለም ላይ እዳ እንጂ ትሩፋት አይደለም። ምንም ገንዘብ እና ጠቃሚ ምግባሮች ቢኖሩት ደግነት የሌለው ሰው ይሄን ዓለም የመረዳት አቅም የለውም።

 

ደግነት ሕጻን ሲያይ ይራራል። ደግነት ሰው ሲያይ ያ ሰው ምስኪን እናት እንዳለችው፣ እህት ና ወንድም እንዳሉት፣ ልጆች ሊኖሩት እንደሚችሉ ያስባል። ደግነት የሰው ልጅን የዓለም መጋረጃ ከፍቶ በዛ ሰው ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ ለመመልከት ይችላል። ደግነት የሰውን የውጣ ውረድ ታሪክ ሲሰማ እንባውን ያፈሳል። ሕይወት በሞት አላዝር ፊት እንባውን እንዳፈሰሰ።

 

ሁላችሁን እስቲ ወደ ጋዛ ልውሰዳችሁ። የዋህ እና ደግ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዛ ሕጻናት መካከል በእግሩ ቢራመድ ምን የሚል ይመስላችዋል? እናንተ ሙስሊሞች፣ እናንተ የነገ ሀማሶች፣ እናንተ የእፉኝት ልጆች የሚል ወይስ እነዛ ያለ አባት፣ እናት፣ ወንድም እና ቤት ከቀሩ ልጆች ጋር የሚያነባ ይመስላችዋል? ደግነት የሚያደርገው ያቺን ሳምራዊት ሴት ያሳያትን ደግነት ነው ለእነዚህ የጋዛ ሕጻናት የሚያሳየው። አብሮ ቁጭ ብሎ ያነባል። አብሮ መከራቸውን ይጋራል።

 

ደግነት ፍርሃቱ እንዲያሸንፈው አይፈቅድም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሥጋ ፍርሃት ራሱን አሳልፎ የሰጠ ቢሆን ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት። በቀራጩ ቤት ምሳ አይበላም። በዛች በዘማዊት ሽቱ ለመዳሰስ እና ለመታጠብ አይፈቅድም ነበር። ምክንያቱም ሰው ምን ይለኛል፣ ባህሉ እና የተዘረጋው መዋቅር ምን ይፈርድብኛል ብሎ ከፈሪሳውያን ጋር ይቆም ነበር።

 

ደግነት ግን ድንጋይ በእጃቸው ጨብጠው አንዲት ምስኪን ሴትን ለመውገር በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት አጎነበሰ። ያቺን ሴት ሊያድን መሬቱን ፋቀ። ደግነት ድንጋይ (መሳሪያ) ከያዙ ሰዎች ጋር አይተባበረም። ደግነት የክፋትን ሠራዊት ይበትናል እንጂ። ዘማዊቷን ለማዳን ደግነት ምንም አይሸማቀቅም። የሌሎች ክፋት ለእነርሱ በችግራቸው ጊዜ ለመድረስ የእርሱን ርህራሔ አያጎድለውም። ልቤ ሆይ ደግነትን በየቀኑ ተማር።

 

ደግነት ፊት ለፊቱ ላለው የሰው ልጅ የውጣ ውረድ ሕይወት ቦታ ይሰጣል። ከፍርሃት ጋር አይቆምም። ቡዙዎቻችን በሚገባ ፍቅር እና የሰው ልጅ ደግነት መካከል ያደግን አይደለንም። ዛሬም በሕግ ማስከበር ሰበብ ከሀገራችን ኢትዮጵያ እስከ አለንበት የስደት ቦታ ድረስ የምናየው የክፋትን ጥግ ነው።


በቤተመንግስት ውስጥ ሆኖ ስለ አትክልቱ እና በእግሩ ስለሚራመድበት የውበት ኮሊደር የሚጨነቅ መሪ እንጂ በእርሱ ወታደሮች እና ድሮኖች ስለሚናጋው የቤተሰብ ሕይወት እምብዛም የማይገደው የጭካኔ መሪን ነው የምናየው። ግን ይሄው መሪ ጩጬ ምስኪን ወንድ ልጅ አለው። ወንድ ልጁን ይወዳል። ሌሎችም እንደርሱ የሚወዱት ልጆቻቸው እየተገደሉባቸው እንደሆነ ግን ማሰብ አይፈቅድም። ልቡን ለደግነት አልከፈተውም። ነጻ አውጪ ነን ያሉትም ነጻ እናወጣዋለን ያሉትን ሕዝብ በግፍ ቀንበር ይገርፉታል።

 

ተሰደን በመጣንበትም ሀገር ማስክ ያጠለቁ ሰዎች የጭካኔ እና የዘረኝነት ክፋታቸውን በኢሚግሬሽን ሰበብ በምስኪን ሰዎች ላይ ያዘንቡበታል።



ዛሬ ያለን የነገ አፈሮች ነን። ነገ በታሪክ መጻፍ ውስጥ እንኳ የማንገባ ኢምንቶች ነን። ይሄ እድሜያችን በሚገርም ፍጥነት ይበራል። ከዛም ያልቃል። በሞት ወደ ምንምነት እንቀየራለን። እንግዲህ ለዚህ ሕይወት ነው ሰው ጎድተን፣ በሌሎች ላይ ጥቅም ይዘን፣ ተቆሳስለን የምናልፈው። ከልጅነት ጀምሮ በጭቆና ያደግንበትን በሌሎች ላይ ድጋሚ ያን ክፋት እና ጭቆና አንጸባርቀን እናልፋለን። የተጎዳ እና ያልታከመ ልብ ፥ ሌሎችንም ጎድቶ እና አቁስሎ ያልፋል።

 

ደግነት የሌለው ሰው ሌላው ሁልጊዜ ያስፈራዋል። ደግነት የጎደለው ሕይወት ሌላው ጥቅም እንደሚይዝበት፣ የእርሱ. የሆነውን ነገር ሊነጥቀው እንደሚፈልግ ነው ሁልጊዜ የሚያስበው። ደግነት አልቦ ሰው በቁስ ማጠራቀም ሕይወቱን ያፍናታል። ከሰው ጋር ነጻ ሆኖ መደሰት አይችልም። በትንንሽ ነገሮች መሳቅ አይችልም። ነጻ ያልሆነ፣ ያልተላቀቀ፣ የሚከብድ ስብዕና ነው ያለው። ሁልጊዜ ያስመስላል። ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሲሆን ደግሞ ይጨቁናል። እድሉን ሲያገኝ ያሰቃያል።

 

በየቀኑ በጉዞአችን፣ በየቀኑ በሥራችን፣ በየቀኑ በመንገዳችን የተጎዱ ሰዎች ይገጥሙናል። ደግነትን ሆን ብለን ካልተለማመድን ፍርሃት ነው ባህሪያችንን የሚቆጣጠረው። ያን ጊዜ እነዚህን ሰዎች መልሰን እንጎዳለን። ለዚህ ነው የበራችን መቀነት ላይ፣ የየቀን መንገዳንች ላይ “ልቤ ሆይ ደግ ሁን!!!” ማለት ያለብን። ቢያንስ ባንደበታችን ሰው ላለመጉዳት መጠንቀቅ ይኖርብናል። ክፉ ከመናገር እና ሰውን ከማቁሰል ራሳችንን መገደብ ይኖርብናል። “ልቤ ሆይ ደግ ሁን” ልንለው ይገባል። ለሰዎች ብለን ብቻ እንዳይመስላችሁ። ደግነት የራሳችንን የልጅነት እና የአዋቂነት የመንፈስ ትሮማ (ስቃይ) እና የውስጥ ቁስል መፈወሻ ብቸኛው መድኃኒት ስለሆነም ጭምር እንጂ። የደግነት እንባ የውስጥ ቁስል ፈዋሽ ፋፋቴ ነው። ከመፍረድ ያዘገያል ደግነት። የማናውቀውን የሰው ልጅ ሕይወት መጋረጃ ከፍቶ ያሳየናል።


ለጊዜያዊው ለዚህ ሕይወት ውበቱ እና ክብሩ ደግነት ነው። ደግ የሆነ ሰው ትንሿን ዘመኑን ያከብራታል።


በሞቱ አልጋ ላይ የመጨረሻ ዓይኖቹን ሲጨፍን ለዚህ ነበር ብሎ አይዘጋውም። ይሄ ሕይወት አጭር እንደነበረ ገና ድሮ እንደገባው ግን ደግሞ የሌሎችን ቁስል ፈውሶበት ያሳለፈው መሆኑን በማየት እየሳቀ ዓይኖቹን ይጨፍናል።

 

ልቤ ሆይ ደግ ሁን።

 
 
 
  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page