
ለምንድነው የሶቅራጦስ “ያልተመዘነ ሕይወት እንዳልተኖረ ይቆጠራል ወይም the unexamined life is not worth living” አባባል ከሶስት ሺ ዘመናት በላይ ትርጉም ለሰው ልጅ ውሳጣዊ ልቦና የሰጠው?
ግን ብዙዎቻችን ይሄን አባባል ምን ማለት እንደሆነ አናውቀውም ወይም ልምምዱ የለንም። በሕግ ትምህርት ቤት እያለው ሁለት ሦስት ፕሮፌሰሮቼ ስለዚህ አባባል በተደጋጋሚ ሲነግሩኝ ግራ ይገባኝ ነበር። ሪፍሌክሽን። “ሪፍሌክት አድርግ” ሲሉኝ። እንዴት አድርጌ ነው ሪፍሌክት የማደርገው? ምንድነው እነዚህ ሰዎች እያሉኝ ያሉት? የምን ሪፍሌክሽን?
ሪፍሌክሽን ሳይሆን ዶግማ፣ መመራመር ሳይሆን ማመን፣ መጠየቅ ሳይሆን መታዘዝ፣ ለምን ማለት ሳይሆን እሺ ማለት፣ ፍለጋ ሳይሆን መረጋጋት የማህበረሰቡ እሴት ከሆነበት ሀገር ለፈለቀ ሰው ሪፍሌክሽን እንግዳ ነገር ነው። በዛ ወቅት ከሃይማኖት ልቦናዬ በጣም የራኩበት ዘመን ቢሆንም የአስተሳሰብ መዋቅሬ ግን ሁሌም ሃይማኖተኛ ነበር። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ስለእኔ ሪፍሌክት ቢያደርጉልኝ ራሱ እመርጥ ነበር።
የሰው ልጅ አዕምሮ በተቀረጸበት ማህበረሰብ መነጽር ነው የሚያየው። ከዚህ የዕይታ ግርዶሽ ተሻግሮ ማየት ለሰው እጅግ ፈተኝ ነው። የመኖር እና የመመሳሰል፣ ማህበረሰብ የሚያስቀምጠውን ደረጃ የመያዝ ፍላጎት ፥ ከእንስሳዊ ባህሪው ጋር ማለትም ከሞት ራስን የመከላከል ፍላጎት ጋር ተጣምሮ መጠየቅን ይፈራል። የራሱን አዕምሮ ጭምር ይፈራዋል። የተጠየቅ ቀስቶች ሲወረውርበት በእምነት ማህተም ይመክተዋል። ስለዚህ ሪፍሌክሽን እንዲርቀው ያደርጋል።
ያልተመዘነ ሕይወት እንዳልተኖረ ይቆጠራል ያለው፣ በመጠየቅ አቅሙ የማንንም የእምነት እና ያልተፈተነ ሰንፋፋ የእውቀት ዝናር በቀላሉ የሚያራግፈው ሶቅራጦስ ሳይቀር በዚዎስ ያምን ነበር። ዛሬ ማንም ስላለመኖሩ የማይጠራጠረው ዚዎስ ከሞት በኋላ ለእውነት በመቆሙ እንደሚሸልመው ያምን ነበር። ይሄ በቀላሉ የሚነግረን ሰው ምን ያህል የቆመበትን የፍልስፍና መሠረቶች የመጠየቅ አቅሙ ደካማ እንደሆነ ነው።
ሪፍሌክሽን ከራሳችን እውነተኛ ተፈጥሮ ጋር ለመገናኘት የድልድዩ ጅማሬ ነው። ሩጫን፣ እምነትን፣ ግብን፣ ዓላማን፣ ተግባርን፣ ቃልን ከዛም ራስን የመጠየቅ እና በጥልቅ የመፈተሽ ከዛም የመታዘብ ልምምድ ነው ሪፍሌክሽን። ብሌዝ ፓስካል እንዳለው “የሰው ልጅ ችግር ሁሉ የሚነሳው ብቻውን በአንድ ክፍል ውስጥ ለመቀመጥ ካለመቻል ነው።” ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ለዚህ ነው “እንዳይነግርህ አንዳች እውነት አናፋበት ፥ ሸልልበት፤ ሆይ፡ሆይ! በል ጩኽበት፤ ጭንቅላትክን ግዘፍበት ፥ ውቀጥበት ፥ ውገርበት፤ ዝግ ብሎማ ያስብ እንደሁ ፥ ይነግርሃል አንዳች እውነት!” ያለው።
የሰው ልጅ አዕምሮ እንደ እውነት የሚፈራው ነገር የለውም። አዕምሮውን ካሳረፈው ያን እውነት እንደሚደርስበት ስለሚያውቅ፤ በዶግማ፣ በሽምደዳ፣ በመደዴ ትንታኔ፣ በአይዶሎጂ ይሞላዋል። ምክንያቱም ዝግ ካደረገው ያጋፍጠዋል። ያጋፍጠዋል ከባከነው ዕድሉ ጋር፣ ያጋፍጠዋል ከከንቱ እና ከውሸት እምነቱ ጋር። ካልተኖረው የአስመሳይነት መርሁ ጋር። ስለዚህ ያን ከመጋፈጥ ፥ በላይ በላይ ይግተዋል ይሄን መረጃ። ጭንቅላቱን ይገዝፍበታል። አዕምሮውን ከማህበራዊ ሚዲያ እስከ ዜና በሚገኝ ብጣሽ እና ቅራቅንቦ ይሞላዋል። በዚህም ሕይወትን እንደሸሻት ፥ የራሱን ሕይወት ሳይኖር ይሞታል። ለዚህ ነው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን “እስቲ ለአንድ አፍታ እንኳ ዝም እንበል። አጉል ነው ብለን ሳንፈረድ፣ ድንቅም ነው ብለን ፈጥነን ሳንወድ፣ መንጋነትን አርቀን እስቲ ዝም እንበል። ብቻ ይሄን አለማድረግ ነው ሞት” ይለናል። ዳግመኛ ሞት መሞት ፥ የአዲስ ኪዳን ጨለማ ማለት ይሄ ነው። ራስን ለመፈተሽ ፥ ተረጋግቶ ለማሰብ ፥ ከዛም ለመታዘብ አለመፍቀድ።