የተገናዘበ ሕይወት
- Mulualem Getachew
- Aug 24
- 3 min read

አንዱ ፍላጎታችን መሉ በኩልሄ መልስ ማግኘት ነው። የትኛውንም ጉዳይ ብንችል በአንድ ሳጥን ውስጥ መክተት እና መረዳት እንፈልጋለን። የምናቃቸውን ሰዎች በምድብ ከፍለን ጥሩ እና መጥፎ ብቻ ወይም ወዳጅ እና ጠላት እንዲሆኑልን እንፈልጋለን። ስለሕይወትም ያለን አረዳድ ሕይወት ትግል ወይም ሕይወት ከባድ እንደሆነ ብቻ ነው። ስለ መንግስትም ሥርዓቶች ያለን ግንዛቤ ጨቋኝ፣ በዝባዣ፣ ፋሺስት ወይም ከኛ የሆነ እና ስህተቱ ይቅርታ የሚባልለት ወይም ነጻ እና ተራማጅ የሆነ ጥቅል ሳጥኖች ናቸው። በመንፈሳዊ ዓለምም የሚድን እና የማይድን፣ ሲዖል ወይም ገነት የሚገባ ብቻ ነው ያለን።
አሁን ላይ በጣም እየተረዳውት የመጣውት ነገር ለሰው ልጅ አዕምሮ ሪያሊትን መረዳት በጣም ከባድ ነገር እንደሆነ ነው። ይሄ ዓለም ከአዕምሮአችን የመረዳት አቅም በላይ በጣም እና እጅግ ውስብስብ ነው። ለምሳሌ ከሰዎች ጋር ስንኖር ግንኙነታችን እከሌ የሚባለው ሰው ሁልጊዜ ጥሩ ስለሆነ አይደለም ወዳጃችን የሚሆነው። ይልቁንስ እኛ የምህረት አቅም ለእርሱ ስላለን ጭምር ነው ወዳጅነት የሚጸናው። ወዳጅ ያልነው ሰው ስለእኛ የሆነ ጊዜ ክፉ ያስባል። እኛም ከዛ ክፋት ነጻ አንሆንም። ከቅናት ወይም ከሌሎች ያልተገናዘቡ ስሜቶች ተነስተን ያን ሰው የሚያሳዝን ባህሪ ወይም ንግግር ልናሳይ፣ ልናወጣ እንችላለን። ለዚህ ነው የምህረት እና የይቅር ባይነት አቅም ያላቸው ሰዎች ብቻ ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት የሚገነቡት። እራሱ ውስጥ ያሉትን የክፋት ባህሪዎች እና ሀሳቦች ማስተዋል ያልቻለ ሰው ከሌሎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ሊኖረው አይችልም።
ዴቭ ሻፔል ስለ ቢል ኮዝቢ አንድ ያለው ነገር ነበር። ከገደለው ይልቅ ያዳነው ይበልጣል። ከሰዎች ጋር ስንኖር ይሄ ይመስለኛል ውሃ ልኩ። ከሚገለው ይልቅ የሚያድነው ይበልጥ እንደሆነ መጠየቅ። ለብዙ ነገሮች ውሃ ልኩን ማግኘት ነው ወሳኝ። በሕይወት ውስጥም ብዙ ሰዎች የተዛባ ሕይወት የሚኖራቸው ውሃ ልክ ሳይኖራቸው ሲቀር ነው። ወይ አብልጠው ከብዙ ነገር ይልቅ ገንዘብ ይወዳሉ። ወይ ፍጹም አባካኝ ይሆናሉ። ፍጹም የሥራ ፍቅር ይይዛቸው እና ሁሉን ችላ ይላሉ ወይም ሰነፍ ሆነው የሰው ጥገኛ ይሆናሉ። ወይም ፍጹም ሰውን ያምኑና ሲታለሉ ይኖራሉ ወይም ሁሉን ተጠራጣሪ ሆነው ለደስተኛ ሕይወት መሠረት የሆነውን ሰውን ማመን ይሳናቸዋል። በእንግሊዘኛ ይሄ Adjusted ያልሆነ ሕይወት ይባላል።
አጀስት ያልሆነም እውቀት አለ። ሁሉን ነገር በኛ የፕሮፌሽን ዓይን የማየት ብቻ እውቀት። ወይም ጥቂት መጽሐፍ ብቻ በሕይወት ያነበበ ሰው ዓለምን በእነዛ መርሕሆች ብቻ ለመዳኘት እንደሚሞክረው ማለት ነው። በቅርብ የሠላሳ ዓመት ሴት ልጅ ያላት አንድ የሰባ ስድስት ዓመት ነጭ ጋር እያወራን፤ ሴት ልጇ የእርሷን ምክር ለመስማት ምንም ፈቃደኛ አለመሆኗ ገርሟት ታወራኛለች። የስነ ልቦና ባለሙያ ስለነበረች የሴት ልጇ ችግርን ከነ መፍትሔው ታውቀዋለች። ግን መች ለመስማት ፈቅዳ። ሕይወትን ተዋግታ ሕይወትን የኖረች ሴትዮ ፊት ለፊቷ እያለች ሴት ልጇ የርሷ የዓለም ዕይታ የተሻለ ጥራት እንዳለው ታስባለች። አስባ ስኬታማ ብትሆን አንድ ነገር ነው። ግን በሕይወት ከውድቀት ወደ ውድቀት ነው እየሄደች ያለችው።
አንድ ጥሩ የሚያነብ በአስራዎቹ መጨረሻ ያለ የዘመድ ልጅ አለ። ከእኔ ጋር ሲያወራ የእርሱ ፍላጎት የእርሱ የዓለም ምልከታ ትክክል እንደሆነ ለማሳየት ነው ጥረቱ። አንዳንዴ እገረማለሁ። የምገረመው በወጣቶች አዕምሮ ነው። ሁላችንም ያለፍንበት ዓለም ነው። የእኔም የዛ የሃያ ዓመቶቼ አዕምሮ ጭምር ነው የሚደንቀኝ። የሆነ መስመር አንበን ወይም ሰምተን ሁሉን ነገር በዛ የመመዘን ፍጥነታችን እና ከኛ ተለቅ ያሉ ሰዎች የሚያሳዩንን የሕይወት ዝግታ እንደ ሞኝነት የመቁጠራችን ዝንባሌ ማለቴ ነው።
ትልቁ ጥበብ ራስን መግዛት የሆነው ለዚህ ነው። ራስን መግዛት በራሱ እውቀት ሆኖ ሳይሆን ራሱን የገዛ ሰው ብዙ ውሳኔዎችን ማዘግየት ስለሚችል ነው። ያዘገየው ተገዶ ሳይሆን ፈቅዶ ሲሆን ማለቴ ነው። ያን የሚያደርግ ሰው እውነትን ለማግኘት ጥረቱን ስለማያቆም በትግስቱ ውጤቱን ይለውጠዋል።
ሕይወት በነጠላ አትሰራም። እያንዳንዱ ነገር የተያያዘ ነው። አንድ ሰው አንዳች ጥሩ ነገር ሲያደርግ ለኛ በጎ ብቻ አስቦ አይደለም። ለራሱም አስቦ ነው። መጥፎ የሚያደርግም ሰው ለራሱ ብቻ ጥሩ ስላሰበ አይደለም። በዛ ውስጥ የተጎደለ ፍትሕን በራሱ መንገድ ለማሻሻልም በመጣር ነው። በአንድ ጊዜ ብዙ ነገሮች አብረው እንደ ድር ይሰራሉ። ሕይወት ስትሰራ ይሄ ባይሎጂ ነው፣ ይሄ ኬሚስትሪ ነው፣ ይሄ ፊዚክስ ነው፣ ይሄ ቲዎሎጂ እያለች አትንቀሳቀስም። ሕይወት ጭራሽ እነዚህን ክፍፍሎች አታውቅም። ለምሳሌ አንድ መጥፎ ነገር የሚያደርግ ሰው በአንድ ጊዜ የሞራሉ ስንኩልነት፣ የዓየር ጸባዩ መጥፎ መሆን፣ መጥፎ ከማድረጉ በፊት የገጠመው ሕይወት፣ ጥሩ እንቅልፍ አለመተኛቱ በትክክል እንዳያስብ አድርጎት እና ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች በአንድ ላይ መጥተው ሊሆን ይችላል። ብዙ ጊዜም እውነታው ይሄ ነው። ለዚህ ነው ብዙ ነገሮችን የሚያውቁ ሰዎች በጣም ጥሩ ውሳኔ የመወሰን አቅማቸው ከፍ የሚለው። ምክንያቱም ሪያሊትን በተሻለ የመረዳት አቅም አላቸው እና።
የተገናዘበ ሕይወት ማለት ውጪውን ከመረዳት በላይ ውጪውን የምንረዳበት እና የምናይበትን መንገድ በጥልቀት ማወቅ ነው። በሌሎች ላይ ለመፍረድ እና ለመጨከን የሚሮጥ ሰው ከፈረደባቸው ሰዎች ስብዕና በላይ ስለራሱ ማንነት ይነግረናል። የተገናዘበ ስብዕና ላይ የደረሰ ሰው በውስጡ የሚርመሰመሱ ስሜቶችን ሁሉ ያለ ማፈር እና መሸማቀቅ እውቅና ይሰጣቸዋል። የዚህ ዓለም ዕይታው እና ነገሮችን የመረዳት አቅሙ ከእነዚህ ከውስጡ ከሚመነጩ የስሜት ውጊያዎች ነጻ እንደማይሆን ይረዳል። ዓለሙን የመረዳት አቅሙ ራሱን በተረዳበት መጠን የተወሰነ እንደሆነ ስለሚያውቅ፤ ሪያሊትን የማወቅ ውስንነቱ ገደብ እንዳለበት ያለጥርጥር ይገባዋል። ለዚህ ነው የሕይወት የፍጽማና አቅጣጫ ለሰው ልጅ በባላንስ ብቻ የሚደረስበት የሚሆነው።
Comments