የምናውቀው ግን እንደምናውቅ ለማወቅ የማንወደው
- Mulualem Getachew

- Sep 7
- 3 min read

የንጉሱን ልብስ ታሪክ ብዙዎቻችን (the emperor cloth) እናውቀዋለን። ታሪኩ ረዘም ቢልም በጥቅሉ ግን የንጉሱ ልብስ ሰፊዎች ለንጉሱ ታይቶ የማይታወቅ ልብስ እንሰፋለን ብለው ተነሱ። ያን ልብስ ማየት የማይችል ሰው በፈጣሪ ርጉም የሆነ እና ኃጢያተኛ ነው አሉ። ንጉሱ ልብሱን ለማየት ቸኮለ። ሕዝቡ ንጉሱ ያን ልብስ ለብሶ ለማየት ቋመጠ። ንጉሱን ልብስ ሰፊዎቹ ለኩት። በወሩ ተመልሰው ልብሱን ይዘን መጣን አሉ። ንጉሱ የለበሰውን ልብስ ሁሉ አሶለቁት። ከያዙት ሳጥን ልብስ እንደሚያወጡ መስለው፤ ከፈቱት። ማንም በዛ ያለ ልብስ አልታየውም። ግን ማን ደፍሮ ይናገራል። ልብሱን ማየት የማይችል ሰው የኃጢያት እና የርግማን ግርዶት ነው ተብሏል። ንጉሱም ልብሱን ማየት አልቻለም። ግን በልቡ ኃጢያተኛ እና በፈጣሪ የተረገምኩኝ መሆን አለብኝ አለ። ንጉሱን ያለበሱት መስለው ተሸከረከሩት። አለበስነው ብለው እልል አሉ። ሁሉም የልብሱን ማማር በአድናቆት ዋው እያለ ገለጸ። የአድናቆት ማዕበል እና ዶፍ ወረደ። ንጉሱ በቤተሰቡ እና በአጃቢዎቹ ተከቦ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሕዝቦቹ ከዚህ አስገራሚ ልብስ ጋር ወደ ሰገነቱ ወጣ። ያን አስገራሚ ልብስ ያየ አንድም የለም። የንጉሱን ሁሉ መላ ከነመላመሉ ግን ሁሉም እያዩ ነው። ግን ሁሉም አስደናቂ ይሆናል ብለው ለተመኘቱ እና ማየት ግን ላልቻሉት ልብስ ከመጀመሪያ ጫፍ እስከ እስከመጨረሻ ጫፍ የአድናቆት ናዳ አወረዱ። በዚህ መኃል በአባቱ ትከሻ ላይ ያን አስደናቂ ልብስ ለማየት እሽኮኮ የወጣ ልጅ ፥ እየሳቀ “ንጉሱ ራቆቱን ነው” አለ። ከዛ ከላይ እስከ ታች ያለው ሕዝብ “ሕጻኑ እኮ ንጉሱ ራቆቱን ነው አለ!” እያሉ ሁሉም ያዩትን፣ የሚያውቁትን እውቀት ለሁሉም ማሰራጨት ጀመሩ። ከላይ እስከ ታች በሕጻኑ አይን ያዩትን የተገለጠ እውነት ማስተጋባት ጀመሩ።
እውቀት ብዙ ዓይነት ነው። አንዱ ግን መጀመሪያ ያወቅነውን ያን እውቀት እንደ ምናውቅ በድፍረት መግለጽ ነው። የታወቀ እውቀት ግን መግለጽ የተፈራ ነገራ ካልታወቀ እውቀት ወይም እውነት ጋር እምብዛም ልዩነት የለውም። ለባለፉት አራት ዓመታት የአሜሪካ ማህበረሰብ ጆይ ባይደን እንዳረጀ፣ የማሰብ እና የማገናዘብ አቅሙ ለሀገር መሪነት ብቁ እንደማያደርገው ያውቅ ነበር። ግን ያን መናገር ለዲሞክራቶች ፓርቲያቸውን መክዳት ነበር የሆነው። ስለዚህ የታወቀውን እውነት ካልታወቀ እውቀት ጋር አቻ አደረጉት። መደበቅ የማይቻልበት ደረጃ ሲደርስ ግን ሁሉም ነገር ከእጃቸው አምልጦ ነበር። በቲቪ ለዓለም በሚታይ መልኩ ከፕሬዝዳንት ትረምፕ ጋር ሲከራከር ትረምፕ “የሚናገረውን ራሱ እንኳ የሚያውቅ አይመስለኝም” ብሎ አሾፈበት። ከዛ ያን የተገለጠ እውነት በሕጻኑ ዓይን አሁን ሁሉም ተቀባበለው። የደረሰውን ውድቀት ግን መቀነስ አልተቻለም።
አሁን ደግሞ ፕሬዝዳንት ትረምፕን ተመልከቱ። ካቢኔው ሲሰባሰብ ሰውዬውን ልክ የአብይ አህመድ ካቢኔ ይመስል አስደናቂ መሪ፣ ባለራዕይ መሪ፣ በአሜሪካ ታሪክ ተፈጥሮ የማያውቅ መሪ፣ ስኬት በስኬት የሆነ መሪ በሚል ነው የሚጀምሩት። በቀደም ለት የቴክ መሪዎችን ሰብስቦ የአፕል ሲኢኦ የሆነው ቲም ኩክ በሦስት ደቂቃ ንግግሩ ትረምፕን ስምንት ጊዜ አስደናቂ መሪ እያለ አመሰገነው። እውነታው ግን የሌበር ዲፓርትመንቱ እንደጠቀሰው ከ2001 ዓ.ም. በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥራ አጥ ቁጥር ሪከርድ ደረጃ ዝቅ ብሏል። የአሜሪካ ወዳጅ የነበረችው ሕንድ ከቻይና ጋር ገጥማለች ወይም እየሸሸች ነው። የአሜሪካ ወዳጆች አሜሪካንን እየራቋት ነው። ትረምፕ ሲመጣ ቃል ከገባው የፓናማ፣ የካናዳ እና የግሪን ካርድ ጥቅለላ አንዱም የተሳካ ውጥን የለም። ሀገሪቷ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተከፋፍላለች። የኑሮ ውድነት ከባይደን ዘመን በላይ የማይቻል ሆኗል። እውነት ነው ድንበሩ ተዘግቷል። በሕገ ወጥ መልኩ የሚገቡ ኢሚግራንቶች የሉም። ግን ደግሞ የዲፖርቴሽን ሂደቱ ጽንፍ ሄዶ ወንጀል ያለባቸውን ብቻ ሳይሆን ንጹሀንን እና ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ሁሉ እያጠቃ ነው። በዚህ ውስጥ ሆነን ነው የንጉሱ ልብስ አስደናቂ ነው የሚሉ የካቢኔ አባላትን የምንሰማው።
በሕይወት እውነትን ግቡ ያላደረገ ሰው የሚያጠፋቸው ጥፋቶች የትየለሌ ነው። ንጉሱ ራቆቱን መሆኑን ሁሉም አይቷል። ያን መናገር ግን ኃጢያተኛ የሚያስብል ከሆነ ወይም ቅጣት ካለው ያን ሪስክ ለመውሰድ ብዙ ሰው አይፈቅድም። መወደድ የመጀመሪያ ግባችን ሲሆን፥ ከሰዎች ጋራ ላለመስማማት እንጥራለን። ሪስክ ከመውሰድ እንሸሻለን። ድንበር ላለመግፋት እንጥራለን። የሌሎች ሰዎች ጥበቃ እስረኛ እንሆናለን።
እውነት ግቡ የሆነ ሰው ከሌሎች ጋር ለመለያየት ብዙ አይፈራም። ሪስክ ከመውሰድ አይሸሽም። ያለ ሪስክ እውነትን መግለጥ አይቻልም እና። ከሁሉም በላይ የሌሎች ሰዎች ፍላጎት እስረኛ አይሆንም።
ይሄ በኛም ግለሰባዊ ሕይወት ውስጥ ያለ ነገር ነው። የምናውቀው፣ ብዙ ዳታዎች ያሉን እውነቶች አሉ። ግን ያን ማወቅ እና መግለጥ አንፈቅድም። ለምን? ከምኞታችን ተቃራኒ ስለሆነ። የምንመኘው እና የምናውቀው ለየቅል ሲሆን፤ ለምኞታችን እንሸነፋለን። ምኞታችን እውቀትን እና እውነትን መግለጥ ከሚፈልገው ክፍላችን በላይ ጠንካራ ነው። ስለዚህ እውነትን በድፍረት የሚነግሩን ሰዎችን በዙሪያችን መክበብ አለብን።
ዛሬ አሜሪካ ውስጥ ስለ ቻይና ያለው አመለካከት ተመሳሳይ ነው። ቻይና በብዙ መንገድ ተመንድጋለች። በብዙ የቴክኖሎጂ ብቃት ከአሜሪካ በልጣለች። ይሄን ማመን ግን የፖለቲካ ሱሳይድ ነው። ስለዚህ ቻይና ሰርቃ ነው፣ አጭበርብራ ነው ወይም ብዙ ደሃ ቻይናዎች አሉ በሚሉ ፕሮፖጋንዳዎች ተጠምደዋል። እውነታውን ማመን ግን ችግሩን ለመቅረፍ የመጀመሪያ መንገድ ነበር። የሰው ልጅ እውነትን መቀበል ዋጋ የሚያስከፍለው ሆኖ ካገኘው፤ ማስደሰትን ይመርጣል።
በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች እንገምግማቸው። እውነታን በምንም ዋጋ የሚነግሩን ናቸው ወይስ እኛን ለማስደሰት የሚጥሩ ናቸው። በሚያስደስቱን ሰዎች ራሳችንን ከከበብን የቀን ጉዳይ ነው፤ ከኛ ጋር መሆን አስፈሪ እና የማያስደስት በሆነበት ቀን ጥለውን የሚሄዱ የመጀመሪያ ሰዎች እነርሱ ናቸው። ለዚህ ነው በጆራችን ላይ ሙገሳን ዲቴክት የሚያደርግ ሳይረን ሊኖር የሚገባው። እውነታን ቢመረንም ለሚነግሩን ቀና መንፈስ እና ምቹ ሁኔታን እንፍጠርላቸው። እነርሱ ያድኑናል።






Comments