ከምናየው ውጪ የሚታይ ዓለም አለ
- Mulualem Getachew

- Sep 14
- 5 min read

በዚህ ሳምንት ትልቁ ዜና የቻርሊ ከርክ መገደል ነበር። ቻርሊ ከርክ በብዙ ነጭ አሜሪካዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው፣ ብዙ ወጣቶችን መሳብ እና መማረክ የቻለ ነበር። የሁለት ልጆች አባት እንዲሁም ባለትዳር ነበር። ቻርሊ መገለጫው በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች እየተጓዘ፣ ወንበር ዘርግቶ ጥያቄ እየተቀበለ ለእነዛ መልስ መስጠት ነበር። በጣም ውስብስብ የሆኑ የማህበረሰብ ጥያቄዎችን፣ የዘር ክፍፍል እና ልዩነት እንዲሁም የእኩልነት እና የጾታ ጉዳዮችን በድፍረት እና በአይዶሎጂ መስመሩ ይመልስ ነበር። ብዙ ነጭ ወላጆች ይወዱታል። ምክንያቱም ባህል፣ ሃይማኖት እና የቀደመው የቤተሰብ አወቃቀር ላይ ስለሚያተኩር እና ያን ለልጆቻቸው ስለሚሰብክ ወደውታል።
በተቃራኒው ቻርሊ ገና በሃያዎቹ ሆኖ ሳለ ሳይቀር ስለጥቁሮች፣ ስለ ስደተኞች እና በተመሳሳይ ጾታ ሰዎች ላይ የሚሰነዝረው ትችት እና የሚሰጠው መልስ ጠንከር ያለ እና ርህራሔ እና ጥልቀት የጎደላቸው ነበሩ። ለዚህም ይመስላል ከነጮች ውጪ ያለው አብዛኛው ማህበረሰብ በመገደሉ ያለው ስሜት እርሱን እንደ ጀግና በመቁጠር አይደለም። በርግጥ ከነጮችም ገዳዩን ጨምሮ የሚቃወመው እንዳለ ሁሉ፣ ከጥቁሮችም ሆነ ከስደተኞች የሚደግፉት አሉ።
አንድ በትልቁ የሚታይ ነገር ግን አለ። ገዳዩም ተገዳዩም ወጣቶች ነበሩ። አንድ የሚባል አባባል አለ። “በሃያዎቹ ዕድሜ አብዮታዊ ካልሆንክ ልብ የለህም፤ በአርባዎቹ ዕድሜ ደግሞ አብዮታዊ ከሆንክ ጭንቅላት የለህም።” ልብ እና ድፍረት ያላቸው ሁለት ወጣቶች ናቸው በዚህ ሳምንት ትኩረት የሆኑት። እኔን የሚገርመኝ ግን አሜሪካ ውስጥ ያሉ አዕምሮ ሊኖራቸው ዕድሜያቸው የሚያስገድዳቸው ሰዎች በእነዚህ ሁለት አብዮተኞች ጎራ ተሰልፈው የቃላት ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ነው። ማህበረሰብ እየወደመ ለመሆኑ ትልቁ ማሳያውአርባዎቹ እና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች አብዮተኞች ሲሆኑ ነው። በሃያዎቹ ያለ ሰው የሚታየው ነገር ውስን ነው። ለውጥ በነውጥ ጭምር ነው የሚታየው። ስለ ሕይወት ያለው ትርጉም በደረሰበት ዕድሜ የሚታየው ብቻ ነው። ያንን ትርጉም የማይጋሩት ሁሉ ደግሞ ጠላቱ እና ክፉዎች አድርጎ ያያል።
ቻርሊ ከርክን የገደለው ሮቢንሰን የሳለ አዕምሮ ያለው እና በትምህርቱ ምጡቅ ነው። ያ ግን አንድ እውቀት እና መረዳት ብቻ ነው። ገና በሕይወት ጉዞ ያልተደላደለ፣ በውጣ ውረድ ያልሰከነ እና ከሌሎች እይታዎች ጋር ያልተፋጨ ነው። ሁላችን ወጣቶች ነበርን። ሁላችን በሃያዎቹ ዕድሜ ነበርን። አሁን ላይ ደግሞ ወደ ኋላ ስንመለከት ምን ያህል ውስን መረዳት እና ደካማ የሆነ እይታ እንደነበረን፣ ጽንፈኝነት እስከ አፍንጫችን እንደነበረ አስተውሉ። ቻርሊ ከርክ ደግሞ ልክ እንደ ጀዋር መሐመድ ያለ ሰው ነው። የነጭ ጀዋር መሐመድ ማለት ነው። አንደበት አለው። የእኔ የሚላቸው ሰዎች በቁጥር ብዙ ናቸው። ለብዙ ማህበረሰብ የተወሳሰበውን ችግር በራሱ መነጽር ብቻ አይቶ የማህበረሰብን አድሎአዊ እይታ በማጽደቅ ይመልሳል። ከፍተኛ ኃይል አለው። አይደክምም። ልክ ጀዋር መሐመድ በአፍላ ዕድሜው ብዙዎች የእርሱ ያልሆኑት እንዲገደል ጭምር ሲመኙለት እንደነበረው፣ ቻርሊንም የሚቃወሙት ሰዎች ያን ነበር የሚመኙለት የነበረው። እርሱም መጀመሪያውኑ የተዋቀረው የአሜሪካ ሥርዓት ያጎሰቆላቸው እና ያዳከማቸው ማህበረሰቦች ላይ በንግግሩ ያቆስላቸዋል። ጥቁሮች ሰነፎች ናቸው፣ እንደውም በሆነ መለኪያ በባርነት ዘመን የተሻለ ሕይወት ውስጥ ነበሩ፣ ባርነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭምር ነው በሚሉ እና ዳታዎችን (ስታስቲኮችን) ልክ እንደ ጀዋር መሐመድ ለራሱ ጥቅም ያለምንም መጠንቀቅ ነበር የሚጠቀማቸው።
እኔ እነዚህ ዕድሜያቸው ከዚህ በላይ እንዲያስቡ ባልፈቀደላቸው ሰዎች እምብዛም አላዝንም። በሁለቱ ጎራ ሆነው ግን ይሄን ሀገር ወደ ተሻለ መምራት የሚችሉ አዕምሮ ሊኖራቸው የሚገቡ ሰዎች የሚያሳዩት ባህሪ ነው የሚደንቀኝ። አንድ ጓደኛዬ የቻርሊ ከርክ ገዳይ ኢሚግራንት ቢሆን ኖሮ፣ አንድ ሳምንት ከቤት አልወጣም አለኝ። ምክንያቱም የተፈጠረው ስሜት የቡድን ነው።
ድንቅ አሳቢው ቶልስቶይ በ”War and Peace” መጽሐፉ ላይ አንድ ጀግና አለው። ጀግናው ወጣቱ ፒየር ነው። ፒየር ፈረንሳይ ሀገር ሄዶ የተማረ እና በዘመናዊ ትምህርት ዳብሮ የሩሲያን የከበርቴውን እና ፊውዳል አስተዳደር መመንገል አለበት ብሎ የሚያምን ነበር። ለንብረትም ሆነ ለሀብት ብዙ ግድ የለውም። እጦትን አይቶ ስለማያውቅ። ፒየር ለናፖሊዮ ቦና ፓርቴ ያለው አብዮታዊ ፍቅር ልዩ ነበር። ሰዎችን አይቶ በባህሪያቸው ወዲያው ይበይናቸው ነበር። ግን ፍጹም ቅን ሰው ነበር። ከችኩልነቱ እና ፈጣን ለውጥ ከመፈለጉ በቀር ውስጡ መልካም ነበር። ቶልስቶይ እንደዚህ ዓይነት የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ያውቃል። ፒየርን ወደ ተደላደለ እውቀት ነበር ማምጣት የፈለገው። ከሚያየው ውጪ ሌላ ዓለም እንዳለ እንዲያስተውል ነበር የፈለገው። ቶልስቶይ በተለይ ይሄን ያሳየው አንድ በፒየር እና መሰሎቹ ዱሪያ ከሚባለው ዶሎኮቭ ጋር ፒየር የሽጉጥ ፍልሚያ ውስጥ በመክተት ነበር።
ዶሎኮቭ የተበላ ቁማርተኛ፣ የሽጉጥ ፍልሚያን የሚያዘወትር፣ ቢጠጣ ቢጠጣ የማይጠረቃ እና ቤተሰብ እንዳላሳደገው የሚኖር ሰው ነበር። ከፒየር ጋር ዶሎኮቭ ይጣላል። የሽጉጥ ፍልሚያ የጥሉ መቋጫ እንዲሆን ይስማማሉ። ሁሉም ዶሎኮቭ ካለው ፍጹም የልምድ ብልጫ በመነሳት ፒየርን እንደሚገለው ገመቱ። ከፍልሚያው በፊት ዶሎኮቭ ለወዳጁ ሮስቶቭ "ይኸውልህ ወደ እንደዚህ ዓይነት ግጥሚያ ስትሄድ እንደምትሞት አስበክ ኑዛዜ ጽፈክ፣ የመጨረሻ ቃል በሚያምር ቃላት ከትበክ መጓዝ የለብህም፡ ግን እንደምትገድል ቅንጣቢ ጥርጣሬ ሳይኖርክ ከገባህበት ሁሉም ነገር ይሰምራል። ልክ እንደ ድብ አዳኝ ፥ ፍርሃቱን ከገለጠ ድቡ ያንን በማሽተት እንደሚያከሽፍበት ሁሉ ፣ ፍርሃት ከተሰማክ ሁሉ ነገር እዛው ያከትማክ።" ሲያቀብጠው እዚህ ጉድ ውስጥ እንደገባ የገባው ፒየር ግን አንዴ ለግጥሚያው እሺ ብያለው እንግዲህ የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ በሚል ፍልሚያው ሜዳ ላይ ቆመ። ፒየር ዶሎኮቭን ክፉኛ አቆሰለው። ዶሎኮቭ ፒየርን ሳተው። ሮስቶቭ ጓደኛውን አቃቅፎ ወደ እርዳታ ከነፈ። በመኃል ዶሎኮቭ እያቃሰተ እነዚህን ቃላት ይተፋል "ይሄን ከሰማች ትሞታለች፣ አትተርፍም፣ ለእኔስ ግድ የለኝም እሷ ግን ... እሷ ግን ቆማ መሄዷን እንጃ። ወይኔ ... ይሄን ጉድ ...ማየት የለባትም ... በሕይወት አትኖርም ..." ሮስቶቭ ግራ ገባው! "ስለ ማን ነው የምታወራው?" አለው። "ስለ ... እናቴ! .... ስለ እህቴ!" ከዚህ በኋላ ሮስቶቭ አዕምሮ ውስጥ የተመላለሰው ቃላቶች ናቸው ዘወትር የሚገርመኝ። "ዶሎኮቭ ወንበዴው፣ ዶሎኮቭ ቁማርተኛው፣ ዶሎኮቭ ነዋጩ ...አፍቃሪ ልጅ እና ወንድምም ነበር!"
ቻርሊ ከርክን የገደለው ወጣት የሚያውቀው አንድ የዓለምን ገጽታ ብቻ ነው። እርሱ ልክ ነው ብሎ ያመነውን ዕይታ ብቻ። ከዛ ያን ዕያት የሚቃወመውን ቻርሊንን። ቻርሊ ግን ሁለት ልጆች አሉት። ለእነዛ ልጆች ቻርሊ አባት ነው። ቻርሊ ባልም ነው። ቤተሰብ ያለው እና አሜሪካ ለልጆቹ የተሻለች ሀገር እንድትሆን የሚጨነቅም ነው። ያን ዕይታ ሮቢንሰን ማየት አልቻለም። የሚገድለው ሰው ፥ ሰውነት እንዳለው ማሰብ አልፈቀደም። ወጣት እና ምንአልባትም አንድ ቀን ሊሰክን እና የዕይታ አድማሱን የሚያሰፋ ሰው ሊሆን እንደሚችል ማየትም አልፈቀደም። ምክንያቱም የእኔ ብሎ የሚወደውን ቻርሊ ተችቶበታል እና። ቶልስቶይ ፒየርን ያስተማረው ሊገለው የተኮሰበት ግለሰብ ቁማርተኛ ብቻ ሳይሆን እናት ያለው ልጅ፣ እህት ያለው ወንድም እንደሆነ በማሳየትም ነበር። ዶሎኮቭ ከቁሱሉ በላይ የሌሎች በእርሱ ቁስል መጎዳት ነበር ያመመው። ዶሎኮቭ ግን እስከዛ ደቂቃ ድረስ ያን ስብዕና ለሌሎች ገልጦ አያውቅም ነበር። ሌላ ዓለምም ዶሎኮቭ እንዳለው ለማየት መታገስ እና ዶሎኮቭን በቁሱሉ ሰዓት መስማት ያስፈልግ ነበር። ቻርሊ ከርክም የሚፈርድባቸው ጥቁሮችም ሆነ ስደተኞች ልብን የሚሰብር ታሪክ እና አሜሪካንን ታላቅ የሚያደርግ ብቃት እንዳላቸው ማየት የፈቀደ ሰው አልነበረም። ሁሉንም በአንድ ሳጥን ውስጥ ከቶ አንዳች እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚሰብክ እንጂ። እንደሱ ቤተሰብ፣ ልጆች ያሏቸው እንዲሁም ለሰው እና ለመጡበት ሀገር በጎ ነገር ለማድረግ የሚጥሩ እንዳሉ ሊረዳ ፈቅዶ አያውቅም።
ብዙ ኢትዮጵያውያንም እንደ ፒየር ነን። ጥቁሮች ሰነፎች ናቸው። ጥቁሮች እንደዚህ ናቸው በማለት ለመፍረድ እምብዛም ማሰብ አንፈልግም። ግን ማህበረሰብ ከማንነቱ ተነቅሎ፣ ለዘመናት በባርነት ውስጥ ካለፈ በኋላ የሚፈጥረው ትውልድ ምን ሊመስል እንደሚችል ምንም እውቀቱ የለንም። እኛ ሲከፋን ሳይቀር ሀገሬ ብለን የምንጠራት እና የምንተክዝበት የስሜት ምርኩዝ አለን። ቀና ብለን እንድንሄድ በሚያደርጉ ትርክቶች ነው ያደግነው። ከዛ ደግሞ ከሀገራችን የመጡ እና የአሸነፉ ሰዎች ምሳሌዎች እንደ ጉም ከቦናል። ቅዱስ ጵውሎስ እነዛን ሁሉ በመከራ ውስጥ ያለፉ የቀደሙ የእምነት አባቶችን የጠራው እኮ የሰው ስነልቦና ስለገባው ነው። ሰው ፊትለፊቱ ያለውን መከራ የሚያልፈው በቀደሙ አባቶቹ ታሪክ እና ጀግንነት ነው። ይሄ የሌለው ማህበረሰብ እንዴት ነው የሚያሸንፈው? በምን አቅሙ ነው እንደ ጉም የከበበውን መከራ የሚሻገረው? ለዛውም በሲስተም ታፍኖ እያለ! እኔ ሰበብ ሰበብ ማብዛትን እየደገፍኩ አይደለም። ግን መፍረድም በተመሳሳይ ስህተት ነው ለማለት ነው። በተለይ ፈጽሞ የማንረዳውን እና ውስብስብ የሆነን የማህብረሰብ ውድቀት እና ስኬት ቀላል በሚመስሉ ንድፈ ሃሳቦች ብቻ መልስ ለመስጠት መሞከር አብዮተኛ እንጂ አስተዋይ አያደርግም። ያፈርስ ይሆናል እንጂ ይሄ ዓይነት አስተሳሰብ አይገነባም። የሰው ልጅ እና ማህበረሰብ ፊትለፊት ከምናየው ውጪ ብዙ ውስብስብ ታሪኮች እና እውነቶች አሉት። መግደል ተቃዋሚን በፍጥነት ያሶግድ ይሆናል። የምንፈልገውን ለውጥ ግን በብዙ ነው የሚያዘገየው። አምባገነን ስርዓት አንድን ጉዳይ በፍጥነት ያሳካ ይሆናል፤ የብዙ ዘመናትን ድልድዮች ግን አይገነባም። ተቃዋሚን ማሶገድ እና አንድ ወጥ የሆነ ማህበረሰብ ብቻ ለመፍጠር መጣር ለጊዜው could be effective but not efficient.






Comments