top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10
  • 5 min read

የሰንበት ዕይታ - 15

ree

በከተማችን ከ50 በላይ የሕግ ባለሙያዎች በሥሩ የሚያስተዳድር “Law Firm” እና የተለያዩ የሬስቶራንት ቢዝነሶች ያሉት አንጋፋ የሕግ ባለሙያ በየወሩ በርሱ ሕይወት ያስተዋለውን መንፈሳዊ ዕድገት እና ውጊያ አስመልክቶ ከ49 ለማይበልጡ የቅርብ ወዳጆቹ በሁለት ገጽ ሪፍሌክሽኑን ጽፎ በኢሜል ያሰራጫል። ከሁለት ወር በፊት ለዚህ ሰው ቅርብ በሆነ ወዳጄ አማካኝነት በዚህ የኢሜል ቡድን ውስጥ ለመካተትና የግለሰቡን ወርሃዊ ሪፍሌክሽን ለማግኘት ቻልኩ። አሁን የዚህን ግለሰብ ወራዊ ሪፍሌክሽን ስቀበል ሦስተኛዬ ነው። የግለሰቡን ስም ፈቃድ ስላላገኘው መጥቀስ አልችልም።

ወደ ዋናው ሃሳብ ሳልገባ በዚህ መግቢያ ላይ ግን ለአንባቢዎች ማስታወስ የምፈልገው አንድ ነገር አለ። በመንፈሳዊውም ሆነ አካዳሚያዊ ስመጥር አዋቂ በሆኑ ግለሰቦች መኃል በሕይወት ስለገጠማቸው መንፈሳዊም ሆነ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ደብዳቤ መለዋወጥ በጣም የዳበረ ባህል መሆኑን። የስቶይክ ፍልስፍና ውስጥ ስመጥር ከሆኑት ኤፔክቲተስ፣ ሴኒካ፣ ማርከስ አሩሊየስ፣ ዳዮጄኒስ፤ እንዲሁም በክርስትና ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅዱስ አውግስጢን፣ ቅዱስ ባስሊዮስ፣ የኑሲሱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ከቅርብ ሰዎቻቸው ጋር በደብዳቤ መወያየት፣ መከራከር እና ተግዳሮቶቻቸውን ማካፈል እጅግ የተለመደ ነገር ነበር። ያለ ሃሳብ ፍጭትና መሞራረድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቅዱሳንን ወይም ሀሳቢያንን ማግኘት የሚቻል አይመስልም።



በዚህ ወር ያካፈለንን ሀሳብ ተርጉሜ ላቅርብ። የዚህ ወር ርዕሱ “Trust” በሚል ነው። አማርኛው Trustንም faithንም እምነት ብሎ ነው የሚተረጉመው። ያ ግን ልክ አይመስለኝም። ለዚህ ጹሁፍ Trustን መደገፍ ብዬዋለሁ፣ faithን ደግም እምነት ብዬዋለሁ። መደገፍ ከዚህ በፊት ያለን ልምድ፣ እውቀት፣ ማስረጃ ይመረኮዛል። እምነት ግን ከዚህ በፊት ያለን እውቀት፣ ማስረጃ፣ ልምድ አይጠይቅም። በዚህም መደገፋችን ወደ እምነት ይወስደናል። በጥቂቱ ነገር ተደግፈን ስላየነው፣ ባላየነው ጉዳይ እናምነዋለን። በዚህም ተስፋ የምናደርገው ነገር በእምነት እውነት እንደሆነ እንቀበላለን። ማንም Trust የሌለው (ጠንካራTrust ወይም መደገፍ የሌለው) እምነት ሊኖረው አይችልም። ከአብርሃም (ዘፍጥረት 15) እስከ ጌዲዮን የሚነግሩን ሀቅ እንዲያምኑ መጀመሪያ መደገፍ እንዳለባቸው ነው። ስለዚህም መደገፋቸውን በማስረጃ እና በልምድ ካደረጉ በኋላ ያላዩትን ነገር እንደሚሆን አምነው ተቀበሉ። በተቃራኒው ከእምነት የወጡ ሰዎችን ስናይ ይሄ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው መደገፍ ወደ እምነት ያልወሰዳቸው ሰዎች ሆነው እናገኛለን። ማለትም ምንም ዓይነት ግለሰባዊ የመደገፍ ልምምድ የሌለው ሰው የጸና እምነት ሊኖረው አይችልም።



አንድ ጸሐፊ ስለ ዴማስ ጳውሎስን መክዳት ሲናገር፤ “ዴማስ ከቅዱስ ጳውሎስ ተሻግሮ ክርስቶስን ማየት ያልቻለ ተከታይ ነበር” ይላል። ቅዱስ ጳውሎስን ብቻ የሚያይ እና በዚያ የተወሰነ ሰው ክርስቲያን ሆኖ ለመጽናት ይቸገራል። ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ሲታሰር፣ ሲገረፍ፣ ሲጋዝ፣ ሲወገር፣ ሲሰደድ ነው የሚያየው እንጂ እነዚህ መከራዎች ኃያል የሆነ ውሳጣዊ ደስታ እና ክርስቶስን የመምሰል እርካታ እንዳላቸው መመልከት አይችልም። ምክንያቱም ያ ደስታ ያ ግለሰብ እርሱም ከፈጣሪው ጋር በሚኖረው ግለሰባዊ ሕብረት ብቻ የሚገኝ ስለሆነ። ፊሊጶስ ናትናኤልን ያለው ይሄን ነው። “መጥተህ እይ!”፤ ቶማስ መጠራጠሩን ለሐዋርያት ሲናገር ፥ ሐዋርያት ምንም አላሉም። ለርሱም እነሱ ያዩትን እና የቀመሱትን ጌታን እንዲያይ እና እንዲቀምሰው ከመመኘት እና ከመጸለይ በቀር። ጌታዬ አምላኬ ማለት የምንችለው ስንቀምሰው ብቻ ነው። ይሄ ማንም የሚሰጠን አይደለም። በእርሱ ቸርነት እርሱን ያገኘች ነፍስ ብቻ ወደ እምነት ታድጋለች። ከመደገፍ (Trust) ወደ እምነት ትሸጋገራለች። በዚህ ወደ የሕግ ባለሙያው የመደገፍ (Trust) ሪፍሌክሽን ልሻገር። በዚህ ጹሁፍ በቅንፍ ውስጥ የማስቀምጣቸው የኔ ማብራሪያዎችን ነው።



ላለፉት ዓመታት እግዚአብሔር ፈቅዶልኝ ይሄን መንፈሳዊ ሪፍሌክሽን ማድረግ ከጀመርኩ ጀምሮ በመደገፍ (Trust) ጉዳይ በሁለት ዓመት አንዴ፣ አንዳንዴ ደግሞ በዓመት አንዴ ጽፌያለሁ። በመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት ውስጥ መደገፍ (trust) በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው ጉዳይ ነው። በተለይ እንደ እኔ ላለ ሰው፣ ሁሉን ነገር መቆጣጠር ለሚፈልግ እና ራሴን እና በዙራዬ ያሉ ሰዎችን ለምሳሌ ሚስቴን፣ ልጆቼን ብቻ ለማምን ግለሰብ በእግዚአብሔር ላይ የመደገፍን (trust) ጉዳይ ዘወትር ራሴን ላስታውሰው ይገባል። በተለይ በከባድ ጊዜያት እግዚአብሔር ላይ መደገፍ በጣም ይከብደኛል፤ ነገሮችን በራሴ የምወጣ ይምስለኛል። “ለምንድነው በእግዚአብሔር የምደገፈው? ለምንድነው ችግሬን ለእግዚአብሔር አደራ ብዬ የምሰጠው?” የሚል ዓይነት ዝንባሌ ነው ያለኝ። እንደሚመስለኝ በዚህ ዓለም በእኔ ደረጃ ከፍተኛ ስኬት ላይ የደረሱ ሰዎች ፥ ልክ እንደኔው ችግራቸውን ለእግዚአብሔር የመተው እና በእርሱ የመደገፍ ከፍተኛ ተግዳሮት አለባቸው።



ስለ trust ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ እችላለሁ። እንደ አባት ቶሎ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ግን ልጆቼ ናቸው። ልጆቼን ማመን በጊዜ ሂደት ተምሬያለሁ። ልጆቼን ባምናቸውም የሆነ መከራ እና ችግር ውስጥ ራሳቸውን ይከታሉ የሚል ፍርሃት ስላለኝ ሁልጊዜ “check” አደርጋቸዋለሁ። ይሄን ፍጹም መታመን (trust) ትሉታላችሁ? በርግጥ ልጆቼን አምናቸዋለሁን? የፕሬዝዳንት ሬጋንን ታዋቂ ንግግር አስታውሳለሁ Trust but verify (እመን ግን አረጋግጥ)። የሚለውን። ይሄ የሚነግረኝ ጌታዬን እንደዛ በቅድመ ሁኔታ እንደማምነው ነው። አምነዋለሁ ግን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ሁልጊዜ ቼክ አደርገዋለሁ። አንዳንዴ የራሴን መንገድ እጠቀማለሁ።



ክርስቲያኖች ግን እንዲህ አልተማርንም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን በፍጹም በርሱ ላይ እንድንደገፍ ነው። ይሄ የሚነገረኝ ሰው በእምነት ሲያድግ በእግዚአብሔር ላይ ያለው መደገፍም እየጨመረ እንደሚሄድ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብን አስታውሱት። እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው የሚያድን እምነት እንደሌለው ነው የነገረን (ያዕ 2፥14)። እምነት አለኝ ብሎ በእምነቱ ያልተደገፈ ሰው እምነቱ ከጌጥነት የተሻገረ ትርጉም የለውም።



ስለ መደገፍ (trust) ትክክለኛ ትርጉም ለማግኘት ብዙ ሞክሬያለሁ፣ ጥቂት የሚቀርብ ነገር ያገኘሁት “ጠንካራ መታመን፣ በዛ መታመን ላይ የተመሰረት ተግባር፣ መደገፍ” የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከ150 ጊዜ በላይ መደገፍ (trust) ስለሚለው ቃል ተናግሯል። ስለእስራኤላውያን ማን ይረሳል፣ በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፍ ብዙ የተቸገረ ሕዝብ ነበር፣ ትንቢተ ኢሳይያስ፣ ትንቢተ ዳንኤል፣ ምሳሌ እነዚህ ሁሉ መደገፍ (trust) በሚል ቃል የተሞሉ አይደሉምን? የዮናስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ ስለከበደው ነብይ አይደለምን? ነብዩ ነገሮችን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ እንደታዘዘው መተግበር ከእርሱ እውቀት ጋር አልገጥም ብሎት ሲቸገር ነው የምናነበው!

በአዲስ ኪዳን ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር መታመን ስለሚያስገኘው ተስፋ እና ደስታ ጽፎልናል። (ሮሜ 15፥13)። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14፥1 ደግሞ ጌታችን ስለመታመን የሁልጊዜ ምርጤ የሆነውን ቃል ነግሮናል። “ልባችሁ አይታወክ” አለን ጌታችን። “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።”



ታላቁ የመታመን ምሳሌ የትኛው እንደሆነ ታውቃላችሁ? የቃና ሠርግ ነው። የኢየሱስ እናት ማርያም “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው።”ድንግል ማርያም በኢየሱስ ላይ ምንም ጥርጣሬ የላትም። ምንም እንኳ ልጇን ያልተረዳችበት ጊዜ ቢኖርም። ታስታውሳላችሁ ጌታችን የ12 ዓመት ልጅ ሆኖ በመቅደስ ሲያስተምር፣ ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ እናቱ ድንግል ማርያም እና ዮሴፍ ሲያገኙት የተሰማቸው ስሜት፤ መገረም ነበር፤ ከዛ በፊት ደግሞ የት እንዳለ ስላላወቁ የመጨነቅ ስሜት ወርሷቸው ነበር።



ምንድነው የድንግል ማርያም መታመን በቃናው ሠርግ ያመጣው? ወይን ብቻ መሰላችሁ፤ ከወይን ሁሉ የሚልቅ ወይን፣ ከብዛቱ የተትረፈረፈ፣ ከጥራቱ አቻ የሌለው ወይን የድንግል ማርያም በኢየሱስ መታመን ያመጣው ነው። “የሚላችሁን ሁሉ ስሙት” ነው ያለችው። (ድንግል ማርያም በቅዱስ ገብርኤል የቀረበላት ሠላምታ ግራ አጋብቷት ነበር፤ አንድ ቃል ግን ተናገረች ፥ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም። በዚህ ዓለም የእግዚአብሔር ሥራ ግር ካላለን ገና ብዙ ነገር አልገባንም ማለት ነው። ማየት አልጀመርንም ማለት ነው። ብዙ፣ በጣም ብዙ የማንረዳው፣ ፈጽሞ የማይገባን ነገሮች አሉ። ግን ለእግዚአብሔር የሚሳነው፣ ለፍቅሩ የሚከብደው ነገር የለም። ይሄ ነው የእመቤታችን እምነት)። በእርሱ ስንደገፍ የምናገኘው ውጤት “ምንም አይልም “ይሁን” “0k” የሚያስብል ውጤት ሳይሆን ፥ እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን (የወይን ጠማቂውን) ጉድ የሚያስብል ነው። ባለሙያዎች ሳይቀር የሚደመሙበት ትሩፋት ነው የመደገፍ ውጤት።


(እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሰራ በምልአት ማናችንም አናውቅም፤ ብዙ ጊዜ ያንንም እርሱ አያብራራም። ለኢዮብ መጨረሻ ላይ ሲገለጥለት ለምን እንደተፈተነ፣ ሰይጣን ስለጠየቀው ጥያቄ እና ለምን ያንን እንደፈቀደ ምንም ማብራሪያ አልሰጠውም። ይልቁስ ለኢዮብ ያለው እርሱ አንድን ቁራን የሚመግብ፣ ሰጎን የረሳቻቸውን ልጆቿን የሚያሳድግ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ነው የነገረው። ማለትም ለቁራዎች አይደለም፣ በግል ደረጃ ለቁራ የሚጨነቅ አምላክ የፍጥረቱ ሁሉ መደምደሚያ እና የእጆቹ ውብ ሥራ የሆነውን የሰው ልጅ ያውም ኢዮብን እንደምን ሊተወው እንደማይችል ነበር የነገረው። “እምነኝ እኔ የምሰራው ሁሌ ልክ ነው፣ ፍጹም አስብልሃለሁ” ነበር ያለው። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር የሚሰራው ነገር አይገባን ይሆናል፣ በርግጠኝነት ግን የምናውቀው ነገር እርሱ ልክ እንደሆነ ነው። የሆነ ሰው መጥቶ ሕጻናት ሲሞቱ የት ነው የሚገቡት አለኝ፤ አላውቅም አልኩት። አንድ ነገር ግን አውቃለሁ፤ የትም ይግቡ የትም ፥ እግዚአብሔር ልክ ነው።)

ስለዚህ ወንድሞች ሆይ በየቀኑ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን መደገፍ ለመጨመር እና ለማሳደግ አንሰራምን? በእምነት ቀስ እያልን ግን በየቀኑ እንደግ።



እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች ራሳችሁን ጠይቁ፤


፩) ምንድን ናቸዉ በእግዚአብሔር እንዳልደገፍ እንቅፋት የሆኑኝ ምክንያቶች?

፪) በእግዚአብሔር ለመደገፍ ምን እርምጃዎችን (steps) ልውሰድ?

፫) በእግዚአብሔር ስደገፍ ከእርሱ ምን ልጠብቅ? ምንድነው ከእርሱ የምጠብቀው?

መልካሙን ሁሉ በክርስቶስ እመኝላችዋለሁ፤ አካባሪ ወዳጆ።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10
  • 4 min read

የሰንበት ዕይታ - 7


አንድ ወዳጄ ስለትችት ወይም ሰዎችን ስለመተቸት እንድጽፍ ጠየቀኝ። በርግጥ የወዳጄ ትልቁ ጥያቄ ያለአቅም እና እውቀት ስለመተቸት ነው። እኔ እንደሚገባኝ ትችት ማለት አንድ ነገር ከምንጠብቀው ደረጃ በታች ሲሆን ወይም ትችት የሚቀርብበት ማየት ያለበትን ነገር ሳያይ ሲቀር ወይም የሆነውን ነገር በእውቀትም ሆነ ያለ እውቀት ሲያጣምመው የምናቀርበው ነቀፋ ወይም ስህተትን በጠንካራ ድምጸት ማሳየት ነው። ስለዚህ ለመተቸት እኔም ሆነ ተተቺው የተቀበልነው የጋራ ደረጃ (standard) ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ ይሄ አባት ተሳስተዋል ለማለት ፥ የሆኑትን ወይም የተናገሩትን ነገር ከእኔም ሆነ ከዛ አባት ውጪ ከሆነ ደረጃ (standard) ጋር በማዛመድ ነው ተሳስተዋል ማለት የምችለው። ያ ደረጃ ከሌለ ልል የምችለው ብቸኛ ነገር ያ አባት ተሳስተዋል ሳይሆን ለእኔ አልተመቹኝም ነው።


ምክንያቱም ደረጃው የጋራ ሳይሆን የእኔ ስሜት እና እውቀት ነው፤ ያ ስሜት እና እወቀት ከሌላው ጋር የምጋራው የጋራችን ካልሆነ ፥ እኛን አባት ስህተት ሊያስብል የሚችል ምንም ነገር የለም። በርግጥ ሌላ ክርክር ሊከፈት ይችላል። በራሳቸው ደረጃ (standard) ነው የመዘንኳቸው ሊል ይችላል። ያ ቢሆን ራሱ “የትኛው የራሳቸው ስታንዳርድ?” ትላንት የተናገሩት ወይስ ዛሬ ከተናገሩት ወይም ሆነው በተገኙት ስታንዳርድ? ትላንት ከተናገሩት ከሆነ ስህተቱ የሳቸው ሳይሆን የኛ ነው። ምክንያቱም እየተቸን ያለነው የትላንቱን ሰው ሳይሆን የዛሬውን ሰው ነው። በትላንት ንግግር መተቸት ያለበት የትላንቱ ሰው ነው እንጂ የዛሬው አይደለም። ስለዚህ ዛሬ ከተናገሩት ከሆነ ደግሞ ምንም የሚያስተች ነገር የለም ምክንያቱም ዛሬ የተናገሩት ነው የሳቸው ደረጃ።



ስለዚህ ትችት ትርጉም እንዲኖረው የጋራ የሆነ ሚዛን ያስፈልጋል። ሁለት ሲደመር ሁለት አምስት ነው የሚልን ሰው ልክ አይደለህም የምንለው የትም ቦታ ያ አራት መሆን አለበት ብለን ስለተስማማን ነው። ግን ያ የኛ ስምምነት ብቻ አይደለም፤ ይልቁስ የኛ ስምምነት በራሱ የጸናው በሆነው ነገር ነው። ሁላችን ብንስማማ እንኳ ሁለት ሲደመር ሁለትን አምስት ማድረግ አንችልም። በንድፈ ሀሳብ ተስማምተን ወደ ተግባር ስናወርደው ይከሽፋል። አራት ብርቱካንን ስለተስማማን አምስት ማድረግ ፈጽሞ አንችልም። አምስት ሰው አስቀምጠን አራቱን አንድ አንድ ለአምስቱም ማከፋፋል አንችልም። ስለዚህ ስምምነታችን ከኛ ስምምነት ውጪ ባለ እውነት፣ በራሱ መቆም በሚችል እውነት እስካልተደገፈ ድረስ ይፈርሳል። ማንም ማንንም ከመሬት ተነስቶ መጉዳት የለበትም የሚል ሰው ይሄን ለማለትኽ መሠረትኽ ምንድነው ብንለው፤ እንደዛ ይሰማኛል ብቻ ካለን ፥ ሌላውን ያለምንም ምክንያት የሚጎዳ ሰውም እንደዛ ይሰማኛል ብሎ ቢጎዳ ስህተቱ የቱ ጋር ነው? ነገር ግን ከዚህ የጠለቀ እውነት ሊኖረው ይገባል።



ለምሳሌ በልጅነቱ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የሰው ጓሮ ገብቶ ፍራፍሬ የሰረቀው አውግስጢኖስ ፥ ሌብነት መጥፎ መሆኑን ማንም አስተማሪ ሳይኖር እናውቃለን ይላል። ይሄን ሲመልስ ሌባ እንኳን ሌላ ሰው መጥቶ የእሱን እቃ እንዲሰርቅበት አይፈቅድም። ሌባ ሆኖ ሳለ እንዲሰረቅ አለመፈለጉ የድርጊቱን ሁሉንአቀፋዊ መጥፎነት (universal evilness) ይናገራል። በጎ ነገር ስናደርግ ያን በጎ ነገር ሰዎች ለእኛ እንዲያደርጉልን እንፈልጋለን። ቢያንስ ተመሳሳይ ነገር እንዲመልሱልን ባንፈልግ እንኳ ያ የበጎነት ስሜት ግን ስለእኛም እንዲያድርባቸው እንሻለን። ማናችንም ግን ክፉ ነገር ስናደርግ እነዛ ሰዎች ያን ክፉ ነገር በእኛ ላይ እንዲያደርጉብን አንሻም።



ይሄን ሁሉ ያልኩት ለመተቸት የጋራ የሆነ ደረጃ (standard) ሊኖረን እንደሚገባ ለማሳየት ነው። ድልድይን በሙስና ያለጥራት የሚሰራ መሐንዲስ፤ ሌሎች መሐንዲሶች ግን ድልድዮችን በጥራት እንዲሰሩ ይሻል። ያ ግን የሱ ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከሱ ውጪ ያለ ፍላጎት ነው። የሱ ፍላጎትማ በሙስና ለጥራት ባለመጨነቅ መስራት ነው። ግን ከተግባሩ በተቃራኒ ይፈልጋል። ምክንያቱም ያ ፍላጎቱ ተራ ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከሱ እና ከሌሎች ውጪ ባለ እውነት ላይ የቆመ እንጂ። ያ እውነት ደግሞ ጥራት ያለው ድልድይ ነው፤ እሱንም ሆነ ቤተሰቦቹን ያለስጋት በዛ ድልድይ የሚያሻግረው። እውነት የምንለው ነገር ከኛ የማድረግ እና ያለማድረግ ተጽዕኖ ውጪ ሕልውና ሲኖረው ነው። ለዚህ ነው እውነት የሆነው። በእኔ ማድረግ እና አለማድረግ ስላልተወሰነ። እኔ በሙስና የምሰራ እንኳ ቢሆን ፥ የእኔ ድርጊት ተግባሩን ጥሩ እንደማያደርገው ከሌሎች በጠበኩት ደረጃ ገለጥኩኝ። ደረጃው የእኔ ቢሆን ኖሮ ፥ ሌሎች እንዲህ ማድረግ አለባቸው ባላልኩኝ ነበር። ያን ብል እንኳ የሚሰማኝ የለም፣ ሰዎች ችላ ለማለትም ስጋት አይገባቸውም። ደረጃው ግን ሁሉን አቀፍ ስለሆነ ካልተሸሸግን በቀር በይፋ አናደርገውም።



ስለዚህ ትችት ሁልጊዜ ከእኛ እና ከዛ ሰውዬ ተራ ፍላጎት ነጻ ሲሆን ነው ትርጉም የሚኖረው። ካሮት ወዳለው የሚልን ሰው እና ካሮት ስላልወደድን ብቻ አንተቸውም። የእኛ ካሮት አለመውደድ የእኛ ወይም የጥቂቶች ብቻ ስለሆነ ግን አይደለም። ካሮትን መብላት ከምግብነት አንጻርም ጥቅም እንዳለው ስለምንገነዘብ እንጂ። ጥቅሙ ደግሞ በሌሎች ተጓዳኝ የፍትሕ እና የመልካም ሕይወት አኗኗር ላይ ጉዳት ስለሌለውም ጭምር ነው። ማለትም ለምግብነት ጥሩ ሆኖ ሌሎች የመልካም ሕይወት ጉዞዎችን የሚያደፈርስ ቢሆን አንቀበለውም። ይሄ የሚያሳየን እኛ ባናረገው ራሱ የማያሳነቅፍ ነገሮችን ስንዳኝ ምን ያህል ከኛ ውጪ ባለ መለኪያ እንደምንመዝን ነው።



ፍትሐዊ ትችት ሚዛኑ ሁልጊዜ ከተቺው ጊዜያዊ ጥቅም እና መሻት የሚሻገር ነው። ይሄ ማለት አንድን ነገር ተቺው ስለወደደው እና ስለጠላው ሳይሆን ከሱ ውጪ ያለ የፍትሕ እና የእውነት ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው የሚዳኘው። ከኛ ውጪ ያለን ነገር ደግሞ የምንረዳው ባለን የእውነት እና የፍትሕ ዓይኖች የአድማስ ስፋት እና የሕይወት ልምድ ነው። ልጆችን ብዙ ነገር እንዳያደርጉ የምንከለክለው ያ ነገር በራሱ መጥፎ ስለሆነ ብቻ ላይሆን ይችላል፤ የከለከልናቸው ነገር ያለአግባብ ከተጠቀሙበት የሚያመጣውን ጉዳት በማሰብ እንጂ። ለምሳሌ የሦስት እና አራት ዓመት ልጅ ውጪ ወጥቶ መንገድ እንዳያቋርጥ የምንፈልገው፣ መንገድ ማቋረጥ በራሱ መጥፎ ሆኖ አይደለም። ነገር ግን ዕድሜው ግራ ቀኙን የማየት አቅም ስለማይሰጠው፣ ልሻገር ሲል አደጋ ሊደርስበት እንደሚችል ስለምናውቅ እንጂ።



ያ እውቀታችን ደግሞ ከወላጅነት ከሚመጣ ለኛ ግለሰባዊ ከሆነ መሳሳት ብቻ አይደለም። አደጋ ደርሶ ስላየን እና ራሳቸውን ከአደጋ መከላከል የማይችሉትን ልጆቻችንን አለመጠበቅ መጥፎ ወላጅነትም እንደሆነ ስለምንገነዘብ ነው። ይሄ የሚነግረን ከኛ የሕይወት ልምድ፣ እውቀት፣ የሥራ እና የዕድሜ አድማስ ውጪ የሆኑ ነገሮችን መተቸት ምን ያህል ልክ እንዳልሆነ ነው። ምክንያቱም ትችት ከኛ ውጪ ባለ መስፈርት ሲመዘን ብቻ ነው ፍትሐዊ እና ትክክለኛ ትችት የሚሆነው፤ ያ እንዲሆን ደግሞ ፥ ያ ከኛ ውጪ ስላለ ሚዛን እና ደረጃ ከምንተቸው ሰው የማይተናነስ እውቀት ሊኖረን ይገባል። ካለዛ ግን እያልን ያለነው “ለእኔ አልጣመኝም፣ እኔ ካሮትን አልወድም ስለዚህ ካሮትን የሚወድ ሁሉ መጥፎ ነው” ነው። ያ ደግሞ ትችታችንን ኢፍትሐዊ ያደርገዋል። ስለእኛም ግልብነት ይናገራል። በጠባብ የራስ ፍላጎት ላይ የቆመ ስለሆነ ፍጻሜው እፍረት ነው።



ልጅ በሆንባቸው ዘርፎች ወላጅ የሆኑ ሰዎችን መተቸት ትርጉም አይኖረውም። በእነዚህ ጉዳይ ከትችት ይልቅ መጠየቅ እና ያልገቡንን ለመረዳት መጣር ነው ተገቢው እርምጃ። ከአንድ እውነት ጋር ግን መጋፈጥ አለብን። ያለእውቀት እና ያለምንም ልምድ የሚተቹ ደፋሮች በየትኛውም ጊዜ እንደሚኖሩ። ያ ብቻ አይደለም የእነሱን ስሜት እና ከእነሱ ውጪ ያለን ደረጃ (standard) ለይተው ማየት የማይችሉ ሰዎችም አሉ። ይሄ ማለት ለእነሱ ጆሮ ያልጣማቸውን ሙዚቃ መጥፎ መዚቃ የሚሉ፤ እንዲሁም እነሱ የወደዱትን ሙዚቃ ሰዎች ካልወደዱ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የደረጃ (standard) ጉዳይ አድርገው የሚደባልቁ ሰዎችም በስፋት አሉ። ገበያ ውስጥ እየገቡ ዝምታን መሻት ቅዠት እንደሆነ ሁሉ፤ የአዕምሮ እና የችሎታ ውጤቶቻችንን ለማህበረሰብ ገበያ እያቀረብን ጉራማይሌ ግብረ መልስ አለመጠበቅ የዋህነት ነው። እያደናገሩ ለሚኖሩ እንጂ የማህበረሰብን የምቾት ሀጢያት እና ያለአዋቂነት ስንፍና እየገለጡ ለመኖር ለቆረጡ ክብር እና አድናቆትን ወዲያው መሻት ከረዥሙ የሰው ልጆች የታሪክ እውነት ጋር መጋጨት ነው። ታሪክ ያሳየን ከሚሰክሩ ጋር አብረው ለሰከሩት ብቻ ነው በጋርዮሽ ሀሳብ የሚሄዱ ስብስቦች ቦታ የሚሰጡት። ባልገባቸው ሰዎች የተሳሳታችሁ ተብለው ለመወቀስ እና እንደ ሞኝ እና ጅል ለጊዜው ለመቆጠር የፈቀዱ ናቸው የዘመናት የማሕበረሰብን ዓይነ ጥላ የሚገፉት። እኛ ግን ለማስተዋል የፈጠንን፤ ለመፍረድ እና ለመናገር የዘገየን እንሁን። ታሪክ ያስተማረን ከዛሬ ደስታ ይልቅ የጸጸት ዕድሜ ረጅም መሆኑን ነው። ቸኩሎ መፈረድ እና መተቸት ለረዥሙ ጸጸት ነው የሚዳርገን።

 
 
 

የሰንበት ዕይታ - 13

ree

መሪ እኛን ካልመሰለ መሪዬ ብሎ መቀበል ከባድ ነው፣ መሪ እኛን ከመሰለ ደግሞ ለምን መሪያችን ይሆናል? ከኛ ከልወጣ እኛን እንዴት ያውቀናል፣ ከኛ ከወጣ ደግሞ እኛን ከዚህ እንዴት ያወጣናል? አብሮን ካልበላ፣ አብሮን ካልጠጣ፣ አብሮን ካልተቸገረ፣ አብሮን ካልዘመረ፣ አብሮን ካልጸለየ የኛ ነገር እንዴት ይገባዋል ብለን እንመን? በሁሉ ነገር ከኛ ካልተለየ ከምንም ነገር እኛን ሊለየን አይችልም! የምናውቀው ነገር ብቻ ነው የሚስበን ፥ ልዩ የሆነ ነገር ብቻ ነው የሚማርከን። የምናውቀው ልዩ ካልሆነ፣ ልዩ የሆነው የምናውቀው ካልሆነ ዓይናችንን አይስበውም፣ አዕምሮአችንን አይማርከውም። ራሱን ድኋ ካደረገ ሀብታም ነው ማለት ነው፣ እረኞች ከሰገዱለት የበጎቹ ጌታ እርሱ ነው ማለት ነው፣ ጥበበኞች ከተንበረከኩለት ጥበብ እርሱ ነው ማለት ነው፣ ካህናት ካልሄዱ ራሱ ካህን ነው ማለት ነው፣ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ከሌለው እርሱ እንግዳ አይደለም ማለት ነው። ስላላወቅነው እርሱ እንደሆነ አወቅነው፣ ስላሳደድነው እውነት እንደሆነ ገባን፣ ወደ ግብጽ በመውረዱ የአባቶቻችን ዘመድ እንደሆነ ተገለጠልን። ወደ ግብጽ ስላልጠራን፣ በግብጽ ስላላገኘነው ከአባቶቻችን የተለየ እንደሆነ አወቅን። በመመሳሰሉ ሳበን፣ ልዩ በመሆኑ ማረከን።



ሕጻን ተወልዶልና ግን የዘላለም አባት ነው፣ የሰላም አለቃ ነው ግን የኛን ሰላም ያናጋዋል፣ ንጉስ ነው ግን እግራችንን ነው የሚያጥበው፣ አምላክ ነው ግን አምላኬ ለምን ተውከኝ ይላል። ወንድ ልጆች ሲገደሉ አባታችን ሙሴ ወደ ገዳዩ ቤት ገባ፣ ወንድ ልጆች ሲገደሉ ወንዱን ልጅ በመጠቅለያ ይዛ ወደ ግብጽ ወረደች።



አካላዊ ቃል ፥ ቃል አልባ ሕጻን ሆነ፤ ቤት ያልተገኘለት ልደት በሁሉ ቤት የሚከበር ልደት ሆነ። ያለእናት የተወለደው ልጅ፣ ያለ አባት ደግሞ ተወለደ። የሰውን ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት ከገነት ያሳደደው አምላክ፣ በሰው ልጅ በንጽህናው ምክንያት ከቤተልሄም ተሳደደ። ለካህናት እና ለጠቢባን ረቂቅ የሆነው ልደት ለእረኞች እና ለበጎቹ ግልጽ ሆነላቸው። ቅርብ ለነበሩት የራቀው ልደቱ ለሩቅ ምስራቆቹ ቅርብ ሆነላቸው። ምድራውያን ከልደቱ ሲሸሹ ሰማያዊያን በቤተልሄም ቆሙ። የሚሰግዱት በሄሮድስ ሲያልፉ የሰገዱት ከሄሮድስ ራቁ። አዋቂዎች ሊሰይፉት ሲነሱ ሕጻናት ስለእሱ ተሰየፉ። ምኞታችንን ሕይወት እንድንነሳው ፥ ሕይወት ያለምኞት ተወለደ።



መንግስቱ የማይታየው ንጉስ፣ አሳዳጃችንን ያሳደደልንን ተሳዳጅ፣ ልብስ አልባው አልባሽ፣ በቤት ያኖረን ቤት ያልተገኘለት። ያን ነው ታናሿ ቤተልሄም የሰጠችኝ ታላቁ ጌታ። ከሁሉ አንሶ የተገለጠውን ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም የተባለችው ከተማ ሰጠችን። ከሁሉ ለመብለጥ ከሁሉ ታናሽ ሁኑ፣ ለመቅለል ቀንበሬን ተሸከሙ ፣ ዓለምን ለመውረስ ዓለምን ካዱ ፣ ራሳችሁን ለማዳን ራሳችሁን እጡ፣ ፊተኞች ለመሆን ኋለኞች ሁኑ፣ አለቃ ለመሆን ሠራተኞች ሁኑ የሚለን ሕጻኑ አባት፣ ማረፊያ አልባው አሳራፊ፣ ሰላም የነሳነው የሰላም አለቃ፣ ሄሮድስን የሚሸሽ የዘላለም ንጉስ፣ የራሱ የሆኑት ያላወቁት ከርሱ ያልሆኑት ያወቁት በዳዊት ከተማ ተወለደ።



መልካም ገና!!!

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page