ለምን እናካብዳለን?
- Mulualem Getachew
- Aug 10
- 4 min read

በውጭ ጉዳይ በቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ስሠራ፣ አንድ የጀርመን ኩባንያ ከሀገር ነቅሎ ሲወጣ ለመ/ቤታችን የጻፈው ደብዳቤ ሁልጊዜ ትዝ ይለኛል። “የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ሁሉም ኋላ ቀር ሀገራት በሕግ ብዛት ችግሮችን መፍታት የሚቻል የሚመስለው ነው፤ ችግሮች ሲገጥሙ በውይይት እና መፍትሔ ለመፈለግ በሚሆን አዕምሮ ከመሥራት ይልቅ በሕግ ላይ ሕግን ማውጣት ባህሪው ስላደረገ እና በዚህ ሁኔታም ኩባንያችን በዚህ ሀገር ውስጥ ለመሥራት ስለሚቸገር ለቀን ወጥተናል” የሚል ጠንካራ ደብዳቤ ጽፈው ነበር የኩባንያው ኋላፊዎች ከሀገር የወጡት። አንድ የጀርመኖች አባባል አለ “The more laws, the less justice” የሚል።
ይሄን ያነሳውበት ምክንያት ብዙ ጊዜ የተወሳሰቡ ነገሮች፣ መዋቅሮች፣ ብዛት ያላቸው ሥርዓቶች፣ ትንታኔዎች ይመስለናል ትክክለኛው መልስ ወይም ለችግሮቻችን መፍትሔ። ለዚህም በሁሉም የሕይወታችን ክፍል ውስጥ ማቅለልን ሳይሆን ማክበደን እና ማስጨነቅን፣ ማወሳሰብን የጥራት፣የአዋቂነት መለኪያ አድርገን እንወስደዋለን።
የ14ኛው ክፍለዘመን ቲዎሎጂያን እና የሎጂክ ሰው ዊሊያም ኦክሃም የፈጠረው እና ኦካም ራዛር ተብሎ የተሰየመ የችግሮች መፍቻ ሂደት አለ። ሁልጊዜ ቀላሉ መፍትሔ በጣም ውስብስብ ሆኖ ከቀረበው በላይ ምርጡ መፍትሔ ነው ይላል። (The simplest solution is almost always the best. ... simplicity is better than complexity)።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእስራኤል መኃል የተጠየቀውም ይሄን ነበር። በፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን የሕግ እና የሥርዓት ቀንበሮች እና ውስብስብ የአምልኮ ማስመሰሎች መኃል ጌታችን በአንድ የሕግ አዋቂ “ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ተብሎ ተጠየቀ። (ማቴ 22፥36)። ከ613 ሕግጋት መካከል የትኛውን እንደሚያስበልጥ ሲጠይቀው ጌታችን እንዴት ባለ መልኩ የሕግጋትን ሁሉ መስፈሪያ ለዚህ ሰው እንደነገረው ተመልከቱ።
613 ሕግጋት መኃል ሁለቱን ምሰሶዎች፣ በጫካው የተሸፈኑ ሁለቱ የሕይወት ዛፎችን አሳየው። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስም በፍጹም አሳብህም ውደድ።” እና “ባልጀራህን እንደራስህ ውደድ” የሚለውን።
እነዚህን ሁለቱን ሕግጋት ሳይፈጽም ቀሪዎቹን ሕግጋት ሁሉ ቢፈጽም፤ ለሰው ምንም አይጠቅመውም። እነዚህን ሁለቱን ሕግጋት ብቻ የሚፈጽም ደግሞ ሁሉንም ሕግጋት ይፈጽማል። ለዚህ ነው ቅዱስ አውግስጢኖስ “እግዚአብሔርን ውደዱት ከዛ ሁሉን ማድረግ ትችላላችሁ ያለው።” (Love God and you are allowed to do everything)። ምክንያቱም ፍቅር የተፈቃሪውን ደስታ ከራሱ በላይ የሚሻ እና ተፈቃራዊን ለማስደሰት የሚሰራ ስለሆነ ነው።
ሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲሁ ሌላ የሕግ አዋቂ የጌታን እውቀት ሊፈትን መጣ። የሕግ አዋቂዎች ማወቃቸውን የሚያሳዩት የረቀቀ ነገር በመናገር፣ ግልጽ የሆነውን ነገር ሳይቀር በማወሳሰብ፣ ሰው ሁሉ በሚገባው ቋንቋ ሳይሆን ፥ ሁሉ የሚያውቀውን ቋንቋ የውጭ ሀገር ቋንቋ እስኪመስል ድረስ በማራቀቅ ነበርና፣ ታላቅ የሆነን ሰማያዊ እውቀት በቀለለ ቋንቋ፣ ሁሉም በሚረዳው መልኩ የሚያቀርበውን መምህር አልወደደውም። ለሕግ አዋቂዎች ብቻ ተወስኖ የነበረውን፣ ተራው ሕዝብም እንዳይገባው በሚመስል መልኩ የቀረበውን እውቀት፣ ይዘቱ ሳይጓደል ለተራው እስራኤላዊ የሚያስተምረው የዚህ መምህር ዘይቤ ለተኮፈሰው ማንነታቸው አደጋ ነበርና ፥ ይሄ የሕግ አዋቂ ጌታችንን “ባልጀራዬ ማነው?” ብሎ ጠየቀው።
በሉቃስ ወንጌል 10፥30 ላይ “ባልጀራ ማነው?” የሚለውን በደጉ ሳምራዊ ታሪክ ገለጠለት። ባልጀራ ማነው የሚለውን ለማስረዳት አዲስ ሕግ አላወጣም። ረቂቅ ትንታኔ አልሰጠም። በወንበዴዎች ተደብድቦ የወደቀውን አይሁዳዊ እና ሌሎች ሳይረዱት ያለፉትን፤ የእርዳታ እጁን የዘረጋለትን እውነተኛ ባልጀራ ደጉ ሳምራዊን በትረካ አሳየው እንጂ። (በሰዓቱ አይሁድ እና ሳምራዊያን እንደ ጠላቶች ነበሩ)። ጠላቶቻችን ሳይቀሩ የኛ ፍቅር እንደሚገባቸው በማስረዳት ፥ ባልጀራ ማነው የሚለውን በሚደንቅ ቅለት ነገረው።
እውነት ለመናገር አንድ ነገር እንደገባን ማወቅ የሚቻለው ለ6 እና ለ7 ዓመት ሕጻን ልጅ ወይም ለአሮጊት አያታችን ማስረዳት ስንችል ነው። እስከዛ ድረስ እኛም ገና አልገባንም።
አንድን ነገር አቅልሎ የሚያሳይ ሰው የዛ ነገር “essence” ወይም ዋናው አንኳር የገባው ሰው ነው። በተቃራኒው የሚያወሳስቡ ሰዎች አልገባቸውም ወይም ብዙ ጊዜ አጭበርባሪዎች ናቸው።
ከ90 ዓመት በፊት የአሜሪካ ኃያል ባለሀብት የነበረው ጆን ሮክፌለር (ከሀብቱ ብዛት የአሜሪካ መንግስት አስገድዶት ገንዘቡን ተበድሮታል) በጣም የሚታወቅበት ነገር ያልገባውን ነገር በልምድ ወይም ሰዎች ሲያደርጉት ስላየ ፈጽሞ አለማድረጉ ነው። በነዳጅ ማጣሪያው ስፍራ ቆሞ ሲመለከት ሠራተኛው ስምንት ጊዜ ማጣሪያውን ይጫነዋል፣ ይሄ ሂደት ሠራተኞች እይተቀያየሩ የሚከውኑት ነበር። ሮክፌለር አንዱን ኃላፊ “ለምንድነው ስምንት ጊዜ የምታደርጉት፣ ለምን አንድ ጊዜ ብቻ አታደርጉም?” ብሎ ጠየቀው። እሱም “ከዚህ በፊት ስምንት ጊዜ ነበር የምናደርገው” አለው። “ምክንያቱን ግን አላውቅም” ብሎ መለሰለት። “በሚቀጥለው ቀን ምክንያቱን አጥንተ አቅርብልኝ” ብሎት ሄደ። ሰውዬው በጥናቱ የደረሰበት ስምንት ጊዜ የሪፋይነሪ ፓምፑን መጫን እንደማያስፈልግ እና ይሄ በሆነ አጋጣሚ የተከሰተ፣ አሁን ግን ፈጽሞ የማያስፈልግ መሆኑን አጥንቶ አቀረበ። “ለምን” ብሎ በመጠየቁ ብቻ ሮክፌለር ሠራተኞቹ የሚያጠፉትን ሰዓት አዳነ፣ የሪሶርስም ብክነት ቀነሰ።
በየቀን ሕይወታችን የምናደርጋቸው ቀላል የማይባሉ ሥራዎች ያለምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ሥርዓት ስለሆነ ብቻ፣ ከዚህ በፊት ሌሎች ስላደረጉት ወይም ያን አለመከተል ከሌሎች ሊነጥለን እና ጥፋት ብናጠፋ አደጋ ውስጥ ሊጥለን ይችላል ብለን ስለምናስብ የምናደርጋቸው ነገሮች ብዙ ናቸው።
ይሄ የማይነካው የሕይወት ክፍል የለም። ብዙ ግራ የሚገቡን እና ዓላማውን የሳቱ ወይም ከዓላማው በላይ ሥርዓቱን ዓላማ ያደረጉ ነገሮች በሃይማኖት ስፍራ እናያለን፣ በሥራ ቦታዎቻችን እነዚህ ውስብስብ ሥራዓቶች እና ቢሮክራሲዎች የደካሞች መደበቂያ ሆነው እናገኛለን።
ከወራት በፊት የወዳጄ ቤት ስሄድ፣ በቤቱ ውስጥ አንድ ጉዙፍ ውሻ አለ። ውሻው በአንገቱ ላይ ገመድ አለው። ዓላማው በቀን አንዴ ውጪ ይዞት ሲወጣ፣ እዛ የአንገት ገመድ ላይ ረዥም ሌላ ገመድ አስሮ ለመውጣት ነው። በዚህ ሀገር ውሻን ያለማሰሪያ (leash) መንገድ ላይ ይዞ መወጣት በሕግ ስለሚከለከል ነው። ውሻው ቤት ውስጥ ስለነበረ ይሄን የአንገት ገመት አወለኩለት። ውሻው ግን መታሰሪያውን መልሰ ካላጠለክልኝ ብሎ አበደ። በጣም ገረመኝ። ምንአልባት እንግዳ ስለሆንኩኝ እና እኔ ስላወለኩለት ይሆናል ብዬ፤ እነሱ እንዲያወልቁለት እና እንዴት እንደሚሆን ለማየት ጠየኳቸው። ውሻው ግን ማንም ያን የአንገት ገመድ ከአንገቱ እንዲወስድበት አልፈቀደም። ምክንያቱም ከልጅነቱ ጀምሮ ይሄ ገመድ ዘወትር አንገቱ ላይ ስለነበረ፤ ከዛ ማሰሪያው ገመድ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ፈጥሯል። ነጻ እንዲሆን እና እንዲቀለው የተመኘነውን ሁሉ ሊፈቅድልን አልቻለም።
ይሄ የውሻ ታሪክ ብቻ ከመሰለን በጣም ተሳስተናል። እውነት ለመናገር ያ ውሻ ራሴን እንድፈትሽ ነበር የጋበዘኝ። “በእኔ ሕይወት ውስጥ ምክንያቱን የማላውቃቸው ከልምድ አንጻር፣ ከማህበረሰብ ላለመለየት ስል ብቻ ወይም ሳይገባኝ ሌሎች ስላደረጉት ብቻ የማደርገው ነገር ምንድነው?” ብዬ መጠየቅ ነው የጀመርኩት።
ታላቁ ሳይኮሎጂስት ካርል ዩንግ በዚህ ዓለም ላይ በጣም ከባዱ ነገር አንድን ነገር ማቅለል ነው፤ ራስንም አቅሎ ለማቅረብ ታላቅ ጥበብ ይፈልጋል ይላል። (But simple things are always the most difficult. In actual life, it requires the greatest art to be simple.)።
የትኛውንም ነገር ጠንቅቃችሁ ለማወቅ ትፈልጋላችሁ፣ ያን ነገር አቅልሉት። ውስብስብ ነገሮችን በቀላል ነገር ተኳቸው፣ ሥርዓት የበዛበት ነገር ስታዩ ቆም ብላችሁ ጠይቁ፤ “ምንድነው የዚህ ሥርዓት ዓላማ? ማነው ይሄን የደነገገው? ምን ለማሳካት ታልሞ ይሄ ሥርዓት ወጣ? ዓላማውን ለማሳካት ዛሬ ላይ ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም?” ለእነዚህ ጥያቄዎች ውስብስብ መልስ የሚሰጣችሁ ሰው ወይ ራሱ አልገባውም ወይም እያጭበረበረ ነው።
ነገር ግን ያለዕውቀት ለማቅለል የሚሞክር ሰው ሕጻን ነው። ሕጻን ብቻ ነው አንድን ነገር የሚያስከትለውን የተለያዩ መዘዞች በአግባቡ ሳያጤን ለማፍረስ የሚሯሯጠው። ያ ቀላል የሕጻን አዕምሮ ነው።
ማካበድ ደግሞ የጀማሪ አዋቂ ወይም ትንሽ እውቀት ያለው ሰው ባህሪ ነው። ይሄ ሰው በውስብስብ ሕጎች፣ ቢሮክራሲዎች፣ ሥርዓቶች፣ በረቀቁ ትንታኔዎች፣ በከባድ ቋንቋዎች (ቃላቶች) ብቻ ነው ከፍ ማለት የሚችለው፣ መኖር እና አዋቂ ተብሎ መከበር የሚችለው። እነዚህ ዓይነት ሰዎች “ሰንበት ለሰው እንጂ ሰው ለሰንበት የተፈጠረ” አስመስለው ሥርዓት እንደዘረጉት ፈሪሳውያን ናቸው። በማወሳሰብ ብዛት አዋቂ ተብለው ለመኖር የሚቋምጡ።
በእውቀት ላይ ተመስርቶ ቀንበርን ማቅለል ግን የጥበበኛ እና የፍጹም አዋቂ ሰው ባህሪ ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የማንኛውንም ነገር essence ወይም ኮር ዓላማ ወይም ዋነኛ ግብ ለማወቅ የሚጥሩ ሰዎች ናቸው። ያን ጠንቅቀው ካወቁ በኋላ፣ ዓላማውን በተሻለ መንገድ፣ ከድሮው በቀለለ ሂደት ለማሳካት የሚጥሩ ናቸው።
በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ጹሁፎቼን በቴሌግራም ገጼ ማግኘት ትችላላችሁ።
Comments