top of page
Search

የሰንበት ዕይታ - 5

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10
  • 6 min read
ree

የዶ/ር ተቀዳ የተፈጸሙት ትንቢቶች እና እንዳይፈጸም መጸለይ እና መሥራት ያለብን ቀሪው ትንቢት

መምርህ ብርሃኑ አድማስ ሰው በእውነተኛ እውቀት ሲያድግ ከእውነት (ከእግዚአብሔር ጋር) ይገናኛል ፥ ካዛ በፊት የማያውቀው ከሆነ ይላል። ዶ/ር ተቀዳ እንደ እኔ ያ የእውቀት ማማ ላይ የደረሰ ሰው። ዶ/ር ተቀዳ ሁላችን በዓብይ እና ተከትሎት በመጣው ለውጥ ስናብድ፣ ሀገርን ያለአስተዋይ የማይተዋት አለና፣ እምብዛም ለሕዝብ የሚውል ነገር የማይጽፈው እውነተኛው ሙሁር ብዕሩን አነሳ። ለጹሁፍ ርዕስ የከበደችው የዓብይ ኢትዮጵያ ሙሁሩንም አስጨነቀችው መሰለኝ ረዥም ርዕስ ሰጠው ለዚህ ረዥም ጹሁፍ። “የዛሬይቷ ኢትዮጵያ እንቆቅልሽ --- የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ --- ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና የሀገራዊ ደኅንነት ፍኖተ ካርት ፍለጋ --- የሚል ርዕስ ሰጠው ለዛ ረዥም ማስጠንቀቂያ ጹሁፍ።



በኢትዮጵያ ታሪክ እንደዚህ ዓይነት ከፍተኛ ቅቡልነትን ይዞ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ አስደማሚ ድጋፍ ይዞ የተነሳውን ሰውዬ ፥ “ድንቅ ነው ያገኘኸው ድጋፍ፣ ይሄ ልዩ ነው ግና ተጠንቀቅ፣ የሕዝብ ድጋፍ እንደሸንበቆ ነው ፥ ዘላለም አይቆይም፤ አረ ዘላለም አይደለም ብዙም አይዘልቅም” አለው። አንዳርጋቸው ጽጌ የለ፣ ሻለቃ ዳዊት የለ፣ ዮናስ ብሩ (ኮኪ አቤሴሎም) የለ፣ መስፍን ነጋሽ ወይም አብይ ተክለማርያም፣ ታደሰ ብሩ የለ ኮነሬል ጎሹ ወልዴ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የለ “ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ ፥ ከፈርዖን ቤት አሻጋሪሽን ሙሴሽን አገኘሽ” ሲሏት ፥ ዶ/ር ተቀዳ ግን ንጉሱ ራቆቱን ሊሆን ይችላል አለን።



ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማነባቸውን ነገሮች በጣም እየተጠነቀኩኝ ነው፤ ጊዜ ካልተረፈኝ በቀር ስለአሁን ሁኔታ የሚተነትኑ የፖለቲካ ጹሁፎችን እያሶገድኩኝ ነው። በተቻለ መጠን የአሁንን ሁኔታ ለመረዳት የዛሬ አስር እና ሃያ ዓመት ተጽፈው አሁን ድረስ መነጋገሪያ የሆኑ ጹሁፎችን እና መጽሐፎችን ነው አንስቼ የማነበው። የምጽፈውንም ነገር ስጽፍ ይሄን የምጽፈውን የዛሬ አስር እና ሃያ ዓመት አንድ ሰው ቢያነበው ምን ያህል ትርጉም ይሰጣል ብዬ በማሰብ ነው። የዶ/ር ተቀዳን ጹሁፍ እንደወጣ ነበር ያነበብኩት። የሙሴ ተከታይ ነበርኩና፣ ምንም እንኳ ምን ዓይነት ኢንቴሌክቿል ካሊበር እና ስብዕና ያለው ሰው መሆኑን ባውቅም ፥ ለውጡን ግን እንዲነካብኝ አልፈለኩም። ስለዚህ ከምር ሳልወስደው ቀረው።



ከጠንካራ ንባብ ዘወር ማለት ስፈልግ ወደትዊተር መንደር ስሄድ በመሐመድ ኡመር የተጻፈውን እና በፎሬን ፖሊሲ ድረገጽ ላይ የወጣውን ጹሁፍ አገኘውት በዚህ ሰሞን። “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት እየሄዱ ነውን?” ይላል መሐመድ፤ አካባቢውን በጥልቀት የሚያውቀው እና የኤርትራ ነጻነት ግንባር የቀድሞ አባል የነበረው መሐመድ፤ ይሄ ጹሁፍ አዲስ መረጃ ባይሰጠኝም፤ ተቀዳን ግን አስታወሰኝ። ዶ/ር ተቀዳ የኖቤል ፕራዝ ኮሚቴ አብይ ከኤርትራ ጋር ለፈጠረው ሰላም በሚል እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2019 ሽልማት ሳይሰጠው በፊት ፥ “ሁለቱ ሀገሮች ድጋሚ ወደ ጦርነት ወይም ወደነበሩበት የቁርሾ ሁኔታ የሚገቡበት መንገድ ዝግ አይደለም!” ብሎ ነበር የመከረው።


ሁለተኛ ትንቢት መሆኑ ነው። የመጀመሪያው “ይሄ የሕዝብ ድጋፋ ይከስማል” አለው፤ “አረ እንደውም ብዙም አይቆይም” አለ። በኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ ደረጃ ተደግፎ የማያውቀው ሰውዬ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደሱ ተጠልቶ ወደማያውቅ ደረጃ በፍጥነት እየደረሰ ነው (እስካሁንም ካልደረሰ)። ዶ/ር ተቀዳ ሁለተኛ ያለው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ትላንት የተነሳው በአንድ እና አንድ ምክንያት ብቻ ነበር። ግንኙነቱ የሁለት ሀገሮች ግንኙነት ሳይሆን የሁለት መሪዎች፣በዛ ቢባል የሁለት ፓርቲዎች ስለሆነ ነበር። ሰዎች ደግሞ ተቋሞች አይደሉም፤ ለራሳቸው በማይገነዘቡት ሁኔታ ጠዋት ከተፋቀሩት ጋር ማታ ተጣልተው ያድራሉ፤ ስለዚህ ከትላንት ካልተማርን ታሪክን እንደግማለን አለን። ደገምን። መድገም የማይሰለቸን እኛ። ዳንኤል ክብረት 70 ዓመት ይብቃችሁ ብሎ ዲያስፖራዎችን በሚገርም እውነት ተችቷል በዚህ ሰሞን። ዳንኤል ምን አልባትም ዓብይ ከመጣ በኋላ የጻፈው ምርጥ እና ትክክለኛ ጹሁፍ ይሄ ብቻ ይመስለኛል። ዳንኤል ግን እንደዛች ዝንጀሮ በመስታወት ውስጥ ያየው የዲያስፖራን የ70 ዓመት ውድቀት እንጂ ለእኛ የደብተራዎች የ2000 ዓመት ውድቀት እንዴት ኩልል ብሎ እየታየን መሆኑን ዘንግቶታል። ሀገሬ ለሺ ዘመናት እየደጋገመች ከትላንት ስህተት መማር ተስኗት እንድትወድቅ ያደረጋት የዳንኤል ክብረት ዓይነት ሰው የሀገሪቷ መሪ መቀመጫ ሥር ገብቶ፥ ለክርስቶስ መስቀል እና ለቤተክርስቲያን ያለንን እምነት ለቤተመንግስት እንድንሰጥ የበዘበዙን ደብተራዎች በመብዛታቸው እንጂ 70 ዓመት ያስቆጠረው ዲያስፖራ አይደለም።


ዲያስፖራው ስህተት የለበትም እያልኩኝ አይደለም፣ በዛማ ከዳንኤል ክብረት ጋር 100% በተጠጋ መጠን እስማማለሁ፤ ግን ለሺ ዓመት ውድቀት የአክሱም ላሊበላ ስልጣኔ ዕምብርት የነበረችውን ሀገሬን የ፸ ዓመት ዕድሜ ብቻ ያለውን መክሰስ የደብተራነት የንጉሱን ፊት እያዩ የመጻፍ አባዜ ነው። ያ ነው የሀገሬ ገዳይ፤ ያ ነው ኢትዮጵያችንን ደጋግሞ የጣላት። የደብተራነት አድርባይነት። ንጉሱ ራቆቱን ሳለ ለመስቀሉ የሰጠነውን እምነት ራቆቱን ለቆመው ንጉስ እንድንሰጥም እምነታችንን የበዘበዙት የደብተራዎች ሴራ ነው የሀገሬ አንዱ የመክሸፍ ምስጢር። (ብዙ ሰዎች ደብተራዎች ሲባል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነው የሚመስላቸው። እውነት ለመናገር ቤተክርስቲያኒቷ ነች ሀገራችን እስካሁን ሳትጠፋ እንድትቀጥል የረዳቻት። በዚህ ጹሁፍ ድብተራዎች የምላቸው የቤተክርስቲያንን እውቀት እና ያገኙትን ትምህርት እውነትን ለማገልገል ሳይሆን የገዢዎች ፍላጎትን ለማርካት ያዋሉትን ነው። ደብተራዎች በቀደመው ጊዜ ከቤተክርስቲያን ነበር የሚወጡት ብቸኛዋ የትምህርት ማዕከል ስለነበረች፤ አሁን ግን እነዚህን intellectual prostitutes እንላቸዋለን።)



ቢያውቀው ዶ/ር ተቀዳ ነበር የዓብይ እውነተኛ ወዳጅ። ይሄ የሕዝብ ድጋፍ ራስህን ልዩ አድርገህ እንድትቆጥር ይፈትንሃል፤ በአግባቡ ከተጠቀምክበት ግን ማለትም በግልጽነት እና በጥበብ ተቋሞችን ለመገንባት ከተጠቀምክበት ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲ፣ ወደ ተረጋጋ ሰላም እና ዘላቂ ልማት መውሰድ ትችላለህ አለው (“If this asset is used properly, transparently and wisely—which, among other things, requires prioritizing institution building and eschewal of the temptations of self-aggrandizement”)። ይሄን ምክር በነጻ ሊለግስህ የሚችለው ውለታ የዋልክለት ሰው ብቻ ነው። ዶ/ር ተቀዳ ግን “በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተቋማዊ ሥርዓትን እና የነገ የኢትዮጵያን ታአማኒነት በማይጎዳ መልኩ ብቻ ነው ማስነሳት ያለብን እንጂ እንደ የሕጻን ልጅ ጨዋታ በብዙ ልፋት የተጣለውን ማዕቀብ በደብዳቤ ብቻ ማንሳት ተገቢ አይደለም” ባለ ፥ በሁለት መስመር ደብዳቤ ከኒውዮርክ አዋራጅ እና ሥርዓትን ባልጠበቀ መልኩ በዓብይ የተነሳ ነበር። መልሶ ጭንቅ ውስጥ ሲገባ ገዱ አንዳርጋቸውን አስልኮበት (በሽማግሌ) ድጋሚ እንዲረዳው ሊጠይቀው ነገር። ዘመኑንን ሁሉ ኢትዮጵያን ያገለገለው ዶ/ር ተቀዳ ግን በዛ ማበድ እና ሳይገባን መከተል ፋሽን በሆነበት ዘመን ነው ፥ “ግድ የለህም ይሄን ነገር ፈር አሲዘው። ተቋማዊ አድርገው። ትላንት ስህተትን ከሰሩ ሰዎች አንተ በምንም አትለይም፣ በእነሱ መንገድ ከሄድክ በመንገዳቸው መጨረሻ እነሱ የገጣማቸውን ነገር ብቻ ነው የምታገኘው” ይለዋል። “ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም የሚለው የሎርድ ፓልመርስቶን ንግግር ምንም እንኳ አናዳጅ እና ኢሞራላዊ ቢመስልም እውነት መሆኑን ግን መካድ የለብንም” ይላል ዶ/ር ተቀዳ፤ “የኤርትራ ፍላጎት ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ሳይሆን የኢሳያስ የኤርትራ ሕወኃትን የመበቀል ጥማት ነው” ሲለን። እኛ ግን ዜጎቹን ሁሉ አባሮ ሽማግሌ እና አሮጊት ታቅፎ፣ ሲንጋፖር ትሆናለች የተባለችን ሀገር ኦስማን ሳሌ እና የማነ ገብርመስቀል የሚባሉ ሁለት ሰዎች ብቻ አስከትሎ የሚመራን መሪ ለኢትዮጵያ ብርሃን ይሆናል ብለን ተቀበልን።



የሰው ልጅ ከታወረ እና እውነትን ለማየት ካልፈለገ ፤ ሲ ኤስ ሉዊስ እንዳለው ዓለም በፊቱ እንደ ወረቀት እየተጠቀለለች እንኳ እውነትን አይቶ ከማመን ይልቅ አይ ይሄ ሃሉስኔሽን (hallucination) ነው ይላል። የራሱን ሀገር ሰው አልባ ያደረገ መሪ በምን ተዓምር ነው 30 ዓመት መሉ የተዋጋትን ኢትዮጵያ ከሀገሩ በላይ የሚያዝንላት? የኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ዲሞክራሲያዊ መሆን እና የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቁ አደጋ ለኢሳይያስ መሆኑን ለመዘንጋት እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ መታወር ያስፈልጋል።

ዶ/ር ተቀዳ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የሚጠነሰስበት “the Council on Foreign Relations” ፕሬዝዳንት የሆነው ሪቻርድ ሀስ “ፎሬን ፖሊሲ የሚጀምረው ከቤት ነው” ብሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መጀመር ያለበት የውስጥን ቤት ሥርዓት በማስያዝ ነው በሚል በ2013 ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አስተሳሰብ አስተዋኩኝ ብሎ ከመነሳቱ 9 ዓመት በፊት፤ መለስ ዜናዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን እና ስትራቴጂያችን መነሳት ያለበት የውስጥ ቤትን በማቃናት እና ሥርዓት በማስያዝ ነው ብሎን ነበር ይለናል።(እንደአንዳንዶች ዶ/ር ተቀዳ ነበር የጻፈው ያን ድንቅ ፖሊሲ፤ ይሄ ባይሆን እንኳ ትልቅ ግብአት እንደነበረው አልጠራጠርም። ይሄን የምለው መለስ ዜናዊ ያን የማፍለቅ የአዕምሮ አቅም የለውም እያልኩኝ አይደለም። ከዛም በላይ መስራት እንደሚችል ያሳየን ይመስለኛል።)። ዶ/ር ተቀዳ ፖሊሲውን ቢያደንቅም ፥ ያን ፖሊሲ መሬት ለማውረድ የሰነፈውን ኢህአዴግን ግን አልራራለትም። ይሄም ይመስለኛ የዚህ ጹሁፍ ውበት ፥ እውነትን ለራስም ሲሆን አለመሰወር። ለራስም ቢሆን አለመራራት።


በርግጥ ይሄ ጸሐፊ ዓብይ አህመድ ያመጣው የለውጥ ማዕበል ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቀጣጠል፤ የሕወኃት አባል ከነበረ አለቃዬ ጋር ዶ/ር ተቀዳን በኒውዮርክ በምሳ ግብዣ ላይ ለማውራት ዕድሉን አግኝተን ነበር። ስለኤርትራ አለቃዬ ሲጠይቀው፤ ዶ/ር ተቀዳ “ችግራችን በዋነኛነት ኤርትራ አይደለችም፤ ወደውጭ መመልከት ተው፤ አሁን ያለውን ነውጥ ራስን በማቃናት እና በመታረም ፈር ማስያዝ ካልቻላቹ ከኤርትራ በላይ ለሀገሪቱ አደጋው ኢህአዴግ ነው” ነበር ያለው። የሚዲያ ሰው ግን ስላልነበረ፣ ይሄን አይነት የእውነት ስብዕናውን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው። ይሄ ማለት ስህተት የለበትም ወይም ንጹሁ ነው ለማለት አይደለም፤ በዲፕሎማቲክ አገልግሎቱ ኢትዮጵያን ከማስቀደም ጎድሎ አያውቅም ለማለት እንጂ።



ዶ/ር ተቀዳ በመጨረሻ ፥ ስለኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል በማሰብ እንቅልፍ አልባ ማታዋችን እንደሚያሳልፍ ገልጾ ፥ በመጨረሻ ትንቢት ጹሁፉን ይዘጋዋል። “ይሄን የለውጥ ዕድል ከበቀል በጸዳ መንፈስ ካልተጠቀምንበት፣ ተቋሞችን ለመገንባት ካላዋልነው፣ ሕወኃት እንዳደረገው ስለተዋጋቸው ብቻ ታላቅ የነበረውን የመከላከያ ሠራዊት እንዳፈረሰው፣ አሁንም ያለው የለውጥ ኃይል ያን ዓይነት ስህተት ከደገመ ‘ኢትዮጵያችን ሁለተኛ ይሄን የመሰለ ዕድል ላታገኝ ትችላለች!’” አለን።



ሀገሬ ዘላለማዊ እንዳልሆነች አውቃለሁ፤ ለእኔም ድንኳኔ እንጂ ዘላቂ ሀገሪ እንዳልሆነች አልዘነጋም፤ ነገር ግን ይሄ የተቀዳ ትንቢት ግን እንዳይሰምር የትላንት ትንቢቱ እንዳይሰምር ከተመኘውበት እጥፍ እመኛለሁ። ኢትዮጵያኖች የገጠመን ነገር የኛም ክፋት ውጤት ነው። ከዚህ መከራ ሊያወጣን እግዚአብሔር የታመነ ነው። ፍቅሩ እና ማዳኑ ግን ያለቅድመ ሁኔታ አይደለም። ሀብታሞች (ነጋዴዎች) በዚህ ደረጃ ጨካኝ ሆነው ፍጹም ለሆነ ስግብግብ ትርፍ የሚራወጡባት፣ የክርስቶስን መስቀል የተሸከሙ አባቶች በዘር እና ጎጥ ተለያይተው እንደ ድንጋይ መግለጫ በሚወራወሩበት ሁኔታ፣ የሀሰት ሌባ ነብዮች በዚህ ደረጃ ሀገሪቷ ላይ ሲፈነጩ እና ትውልድ ሲያከስሙ፤ እኛም የሚናገሩት ለጆሮአችን ደስ ስላለን እየተከተልናቸው፣ የመንግስት ባለስልጣናት የወጣላቸው ዘራፊ ሆነው፣ ወንድማማችነት ጠፍቶ ዘረኝነት የነገሰበት ሀገርን የሚታደግ አምላክ የለንም። ዶ/ር ተቀዳ እንዳለን እሴቶቻችንን እንፈትሽ ፥ “የትኛውም የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ የደህንነት ፖሊሲ የጥንካሬው ደረጃ በቆመባቸው እሴቶቹ (values) ጥንካሬ የሚለካ ነው” ነው ያለን ዶ/ር ተቀዳ።



የሀገራችንን ዘላቂ ጥቅም ማስቀደም ካልቻልን፣ ስለእውነት ለመናገር ካልደፈርን፣ ወገናችንን ለመውደድ ካልፈቀድን ኢትዮጵያን ነገ አናያትም ብቻ አይደለም ሶማሌ እና የመንን ገነት እናስመስላቸዋለን። ለእኔ ዓብይ አህመድ የክፋታችን እና የእውቀት አልባነታችን ውጤት እንጂ ምንጭ አይደለም። ዓብይ አህመድን ለዚህ ውድቀት ማውገዝ ሰውዬው የሌለውን አቅም እና ችሎታ መስጠት ነው። ለመገንባት ብቻ አይደለም ለማፍረስም ችሎታ ይጠይቃል። እሱ ሁሉቱም የሌለው ነው። ላለንበት ሁኔታ ኃላፊነት ወስደን ሀገራችንን እንታደጋት።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page