top of page
Search

የሰንበት ዕይታ - 8

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10
  • 3 min read
ree

በዚህ ሰሞን ሁለት ታላላቅ አሜሪካውያን ሞተዋል። አንደኛው የአሜሪካ ቢዝነስ ላይ ኃያል ተጽዕኖ ያሳደረ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የ12 የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች የውጭ ጉዳይ እና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ አማካሪ የነበረ ነው። ቻርሊ መንገር በ99 ዓመቱ ሲሞት፣ ሄነሪ ኪሲንጀር በ100 ዓመቱ ሞቷል።


በኖሩበት ዘመን ልክ ተጽዕኖ የፈጠሩ፣ በተሰማሩበት መስክ አስገራሚ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ናቸው። ሕይወታቸው እስከሚያልፍ ድረስ ሰዎች የሚሰሟቸው ነበሩ። ሌላኛው አሜሪካዊ ሙሁር ናሲም ታሌብ ስለቻርሊ እና ኪሲንጀር ሲናገር “አንደኛው ወደ ገነት ሌላኛው ወደ ሲዖል እንደሄዱ የታወቀ ቢሆንም፣ ሁለቱም ግን በዚህ ዓለም ቆይታቸው በሚያዋዥቅ ሙሁራዊ እንቅስቃሴ (athletic activities) ጊዜያቸውን አላጠፉም” ይላል። ከሁለቱም የምንማረው ነገር ቢኖር፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ደረጀ የጎደለን ነገርን ነው። አንድን ነገር አድምቶ የመረዳት እና ከሥር መሰረቱ የማወቅ፣ ከዛ ሰው ወደደን ጠላን ለሚል ጊዜያዊ ሁካታ ሳይሆን ፥ በጽንአት በዛ አቋም መቆምን ነው። ማለትም ለጊዜያዊ ትክክለኝነት ስንል፣ ከጥልቀት ምርምር እና መረዳት በኋላ የያዝነውን አስተሳሰብ አለመለወጥ። ለዘላቂ ጥቅም ጠላት የሆነ አንድ ነገር አለ፣ ሕዝባዊነት ነው። ለጊዜው ሞኝ እና ስህተተኛ ሆኖ ለመቆጠር ያልደፈረ ሰው፣ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ግብን ማሳካት አይቻለውም። ቻርሊም ሆነ ኪሲንጀር በተሰማሩበት ሕይወት እንደዛ ነበሩ።



 ለዛሬ እ.ኤ.አ በሜይ 2023 ዓ.ም. ዋረን በፌት እና ቻርሊ መንገር ከበርክሸር ኢንቬስተሮች ጋር ባደረጉት የሁለት ቀን ስብሰባ ወቅት ከተናገሩት እና በጊዜው ለጥቂት ወዳጆቼ ያጋራውትን አጋራችኋለው። ከድንቁ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሳቢ ኪሲንጀር ደግሞ አንድ ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል የተናገረውን ነጥብ በቁጥር ዘጠኝ ላይ አክያለሁ። መልካም ንባብ።

ዋረን በፌት 92 ዓመቱ ሲሆን ፥ ቻርሊ መንገር ደግሞ 99 ዓመቱ ነው። ሁለቱም ከ20ዎቹ ዓመታቸው ጀምሮ ኢንቬስተሮች ሲሆኑ ፥ ከ50 ዓመት በላይ ቢሊየነር የሆኑ ጥቂት አሜሪካኖች ውስጥ በመጀመሪያው ረድፍ ስማቸው የሚቀመጥ ነው። ቻርሊ እና ዋረን በርክሽርን (ኮካ ኮላ እና አፕል ስልክን ጨምሮ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ የአንበሳው ድርሻ የያዘ ድርጅት ነው) በሚመሩበት ወቅት፣ ድርጅቱ 2,000,000% መነሻ ኢንቨስትመንቱ ላይ መመለስ ችለዋል። ትላንት ካነሱት ወሳኝ ነጥቦች ፥ በሕይወት እነዚህን ካደረጋቹ ስኬታማ ትሆናላችሁ ብለዋል፤


1) ወጪያቹ ከገቢያችሁ ማነስ አለበት። ቀሪውን ገንዘብ በጥንቃቄ ኢንቬስት አድርጉት፣


2) ከልጅነቴ ጀምሮ የተማርኩት ነገር በሕይወት የሚመጡልኝ ጠቃሚ ዕድሎች ጥቂት እንደሆኑ ነው፣ ጥበቡ እነዚህን ጥቂት ዕድሎች እንዳያመልጡን መዘጋጀት ላይ ነው። ይሄን የኢንቨስትመንት ካውንስል ላይ ሲናገሩ አትሰሟቸውም፣ እነሱ የሚመስላቸው ሚሊዮን ነገሮችን በማጥናት ሚሊዮን ነገሮችን ማግኘት የሚቻል ነው።


3) በየዕለቱ ከመተኛታችሁ በፊት የዛ ቀን ስትነሱ ከነበራችሁ እውቀት ትንሽ አዋቂ ሆናችሁ ለመተኛት ቁረጡ፣ ኃላፊነታችሁን በታማኝነት እና በጥሩ ሁኔታ ተወጡ።


በዚህም ሲስተማቲካሊ ወደፊት ትጓዛላችሁ፤ የግድ በፍጥነት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ይሄን በማድረጋችሁ ጠንካራ ሥነስርዓት (discipline) ስለምትገነቡ ወደፊት በፍጥነት መስፈንጠር ትችላላችሁ። በየቀኑ አንድ እርምጃ ወደፊት ተጓዙ፣ ቀን በቀን ለማደግ ሞክሩ፤ በመጨረሻ ረዥም ዕድሜ ከኖራችሁ በሕይወት የሚገባችሁን ነገር አታጡም። (ቻርሊ ከፈጣን ዕድገት ይልቅ ሰውን ወደ ግቡ የሚያደርሰው ዝግ ያለ ግን የማይቆም ዕድገት ነው የሚል ፍልስፍና አለው። ሲ ኤስ ሉዊስ ስለሰይጣን ስትራቴጂ ሲናገር “የሰውን ልጅ በርግጠኝነት ሲዖል ማስገባት የሚቻለው በፈጣኑ የክህደት ሃዲድ ሳይሆን፣ ዝግ ብሎ በሚሄደው የክህደት መስመር ነው” ይላል። በርግጥስ ከጥንቸል ይልቅ የአሸነፈችው ያለማቋረጥ ግን ደረጃ በደረጃ የተጓዘችው ኤሊ አይደለች። ዊንስተን ቸርችል ስለአሜሪካ ሲናገር “ቶሎ ለውጥን አይቀበሉም ነገር ግን ሁልጊዜ ትክክለኛው ነገር ላይ ይደርሳሉ” ይላል)።


4) ሰዎችን በፍጹም አትውቀሱ ፥ ሰውን ሳትወቅሱ ጥፋታቸውን ማሳየት ትችላላችሁ፣(የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በሚለው መጽሐፋቸው ሊቁ እጓለ ገብረዮሐንስ፤ “አንድን አሮጌ ቤት አሮጌ ሳትሉ ማርጀቱን መግለጽ ትችላላችሁ” ይላሉ። “ይሄም አጠገቡ አዲስ ቤት በመገንባት ነው። የዛኔ ያንተን አዲስነት፣ የዛን ቤት አሮጌነትም ይናገራል” ይላሉ። “ነቢይ እና ሕጻን ነው በቀጥታ ሰውን የሚወቅሱት። እኔ ደግሞ ሁለቱንም አይደለውም” ይላሉ ሊቁ። ቻርሊ እና ዋረን የሚሉንም ተመሳሳይ ነው)።


5) በሕይወታችሁ መርዛማ ሰዎችን በፍጥነት አሶግዱአቸው (ተንኮልን እወቁ ግን ተንኮል አትስሩ ፥ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማችሁ አድርገው ሊበዘብዟችሁ ያሉ ሰዎችን በተቻለ መጠን ከሕይወታችሁ በቶሎ ቆርጦ መጣል ወሳኝ ነው።)


6) በሞታችሁ ጊዜ እንዲነበብላችሁ የምትፈልጉትን ከአሁኑ ጻፉ (obitury) እና በዛ መሰረት ኑሩ። ያኔ በየቀኑ በጥበብ ታድጋላችሁ።


7) ዕዳ ውስጥ ፈጽሞ አትግቡ ፥ አንዴ ከገባችሁ መውጫ የለውም ምን አልባት ቤት መግዛት ላይ በዕዳ ልታደርጉት ትችላላቹሁ ከዛ ውጪ ግን ፈጽሞ።


8. የምታደርጉትን ሁሉ ይሄን ነገር በየቀኑ እያደረኩኝ ብቀጥል የዛሬ አስር ዓመት የት ያደርሰኛል ብላችሁ ጠይቁ። ያኔ ነው ዛሬ ላይ ደደብ የሆነ ነገር ከመስራት የምትቆጠቡት። በሁሉም ነገር የረዥም ጊዜ እይታ ይኑራችሁ።


9) ኪሲንጀር ከጎቴ (Goithe) አዘውትሮ የሚጠቅሰው አባባል አለው፣ “በፍትሕ እና በሥርዓት (order) መካከል ምርጫ ቢሰጠኝ፣ ሥርዓትን ነው የምመርጠው። ምክንያቱም አንዴ ሥርዓት አልበኝነት ከነገሰ ለፍትሕ ቦታ የለውም። (ኪሲንጀር በዚህ ሳምንት ቢሞትም ይሄ አባባሉ ግን በዓብይ ኢትዮጵያ ዛሬ እየኖርነው ነው። ሰው “ምን ነው ሁሉ ነገር ቀርቶብኝ በሰላም ወጥቼ በሰላም በገባው” እያለ ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሞቱ ብቻ አይደለም ዛሬ ያማረረው። ገዳዩ መብዛቱ እንጂ። አንድ ገዳይ ቢቻ ቢኖር ያን መንግስት ብሎ ይታዘዝለት እና የሚፈልገውን ያህል ይገብርለት ነበር። ሥርዓት አልበኝነት ባለበት ፍትሕ ሆነ ዲሞክራሲ ቅንጦት ናቸው። ሥርዓት ባለበት ግን ቢያንስ ቢያንስ የተገደበ ፍትሕ በርግጠኝነት አለ)።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page