top of page
ree

የሰንበት ዕይታ - 10


የትኛውም ሰዎች ይሄን አድርጉ ሲባሉ ደስ አይላቸውም። ሰዎች በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ እና ሙሉ ነጻነት እንዳላቸው ማመን ይፈልጋሉ። ልጆች እንኳ እንደሚገረፉ እያወቁ አታድርጉ የሚባሉትን ነገር ነው የሚያደርጉት፤ ይሄም የሰው ልጅ በባህሪው ይሄን አድርግ ወይም አታድርግ ሲባል ስለማይወድ ነው። ለራሱ የሚጠቅም እንኳ ቢሆን ከሚታዘዝ ይልቅ ነጻነቱን ይመርጣል።

የማስታወቂያ ሰዎች ይሄን የሰው ልጅ ባህሪ ጠንቅቀው የተገነዘቡ ናቸው። ለዚህ ነው ጥሩ ማስታወቂያ የሚሰሩ ሰዎች ፥ ሰዎች ያን ዕቃን ግዙ ሳይሆን የሚሏቸው በመግዛት የሚገኘውን ደስታ፣ እርካታ እና ጥቅም ነው የሚያሳዩአቸሁ።


ኢትዮጵያ እያለው የተማረ ሰው ቢዝነስ እንደማይችል ይነገር ነበር። በከፊል እውነት ነው። አሜሪካ ስመጣ ግን ፥ በተለይ ቢዝነስ ስኩል ስገባ የአሜሪካ ኢንቬስተሮች አንዳች ነገር ያለዕውቀት እንደማያደርጉ አየሁ። ለምሳሌ በአሜሪካ ውስጥ ከአንድ እስከ ሦስት ያሉ ባለሀብቶች ሁሉም የIQ መጠናቸው መቶ ሀምሳ ወይም ከዛ በላይ ነው፣ በጣም ምጡቆች ናቸው። ይሄን ለምን አነሳው? ምንም ነገር በእውቀት ሲሰራ የተለየ እና ዘላቂ ውጤት እንዳለው ለማሳየት ነው። ለምሳሌ ቢዝነስ የሰውን ስነ-ልቦና በአግባቡ ማወቅ እና ራስን መግዛት ይጠይቃል። ዴቪድ ኦግሊቪ የተባለ ታዋቂ አሜሪካዊ ጸሐፊ ያሳየውን የቢዝነስ ጥበብ እሱም “አሳይ እንጂ አትንገር - Show but don’t tell” የሚለውን እንይ።



ዴቪድ ከቢሮው ሲወጣ አንድ ዓይነ ስውር ለማኝ ሰው በሚመላለስበት መንገድ ላይ “ዓይነ ስውር ነኝ እርዱኝ - I am blind please help” የሚል በካርቶኒ የተጻፈ ማስታወቂያ ይዞ ቁጭ ብሏል። አንድም ሰው ገንዘብ የሰጠው የለም። ለብዙ ሰዓት እንደተቀመጠ ግን ያስታውቃል። ዴቪድ ዓይነስውሩን ተጠጋው እና “ገንዘብ አልሰጥህም ፥ ይሄ ሁሉ ሰው ግን ገንዘብ እይሰጠ እንዲያልፍ ማድረግ እችላለሁ ፥ ከፈቀድክልኝ” አለው። ዓይነስውሩም የሚያጣው ምንም ነገር ስለሌለ “እሺ” አለ ፥ ዴቪዲም የዓይነስውሩን “ዓይነ ስውር ነኝ እርዱኝ” የሚለውን በራሱ ጹሁፍ ለውጦ ሄደ። በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ሰዎች ገንዘብ እና ሳንቲያቸውን ለዓይነስውሩ እየወረወሩ ፥ አንዳንዶቹም ከንፈራቸውን እየመጠጡ ያልፉ ጀመር።



ለማኙ በመደነቅ ፥ የሆነ ሰው ሲያልፍ “ወንድሜ እባክህ የተጻፈው ነገር ምን እንደሆነ ትነግረኛለህ?” አለው።



ሰውዬው ያነበበለትን ከመንገሬ በፊት፤ የመጀመሪያው ጹሁፍ ምን ስህተት እንዳለበት ላሳይ። “ዓይነ ስውር ነኝ እርዱኝ”። “ዓይነ ስውር ነኝ” የሚለው መረጃ ነው ፥ ሰዎች ዓይነ ስውር እንደሆነ እያዩ ነው ምንም የተለየ መረጃ አይሰጥም። ከሚያዩት በላይ የሚነግረው ምንም ነገር የለም። “እርዱኝ!” የሚለው ትዕዛዝ ወይም ማድረግ ያለባቸውን የሚነግር ነው። ሰዎች ደግሞ ይሄን አድርጉ ሲባሉ ደስ አይላቸውም። በራሳችን መወሰን እንችላለን ብለው ነው የሚያምኑት ፥ ሁሉም ሰው ለትዕዛዝ ያምጻል ፥ የእግዚአብሔር ትዕዛዝን የሚጥስ ሰው የሰውን ያከብራል ማለት ሞኝነት ነው።

ዴቪድ ኦግሊቪ ለዓይነ ስውር ለማኙ ምንድነው የጻፈው?


“በጋ (spring) ነው፤ እኔ ግን እዚህ ነኝ - “It is spring but I am here”)፣ በአሜሪካ ውስጥ ስፕሪግ ሰዎች እረፍት የሚወጡበት እና የሚዝናኑበት ወቅት ነው፣ በዚህ ወቅት ውጪ እየወጡ መዝናናት የሁሉም ሰው ናፍቆት ነው ምክንያቱም የበረዶ ዘመን ያለቀበት እና ሀሩር ፀሐይ የሚመጣበት መኃከል ነው ስፕሪንግ ያለው። ሰው ሁሉ በዚህ ሰዓት ምኞቱ መዝናናት ነው። ዴቪዲ በስድስት ቃላት የገለጸው ስለዚህ የሰዎች ምኞት ነው። ሁሉም ሰው በስፕሪንግ ደሀ መሆን እና አለመዝናናት አለመቻል እንዴት እንደሚያም ያውቀዋል ፥ ሁሉም ሰው ግን ዓይነስውር ሆኖ አያውቅም። ስለዚህ ዓይነስውር መሆን ምን እንደሆነ አይረዳም። ስለዚህ ለሁሉም ሰው ቅርብ በሆነ ነገር ነው ዴቪድ የሰውዬውን ሕመም የገለጸው። ሁለተኛው ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አይገልጽም። ያን ውሳኔ ለሰዎ ትቷል። ማሳየት እንጂ የጥሩ አስተዋዋቂ ተግባር ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው መንገር አይደለም።



ስማርት ነጋዴ ልክ እንደ መርማሪ ፖሊስ ነው። የሞተ ሬሳ ጋር ቆሞ ፥ “ምን ቢፈጠር ነው ይሄ ሰውዬ የተገደለው?” ብሎ የሚጠይቅ ማለት ነው። ነጋዴም የመጨረሻውን መልስ ያውቃል። እሱም “እቃውን በሚፈልገው ትርፍ መሸጥ።” “ይሄን ዕቃ ለመሸጥ ምን መፍጠር አለብኝ ፥ ገዢዎቼ ውስጥ ምን ዓይነት ስሜት መቀስቀስ አለብኝ?” ብሎ የሚጠይቅ እና ለዛ ብዙ ነገሮችን የሚሞክር ማለት ነው።


ሰዎች እቃ የሚገዙት ወይም ሰርቪስ የሚጠቀሙት ለመደሰት ነው። ማንም ሰው ለማዘን ምንም ነገር አያደርግም። ደስታ ማለት በሆነ መጠን ከፍርሃት ነጻ መሆን ነው። ስለዚህ ሰዎች ምንድነው የሚፈሩት የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ሰዎች ተመሳሳይ ዕቃ ሆኖ ርካሹን ትተው ውዱን የሚገዙት ፥ ስለሚፈሩ ነው። ይሄ ርካሽ የሆነው እውነተኛ ስላልሆነ ነው ፥ ፌክ ስለሆነ ነው በሚል። ሰዎች ውድ እቃ ከመንገድ ላይ የማይገዙት ፥ በመንገድ ላይ የሚሸጠው ሰው ነገ እዛ ቦታ ላይ ስለማይገኝ ነው። የመንገድ ላይ ነጋዴ ደንበኛ መፍጠር የሚል ነገር አያስጨንቀውም። የሚያስጨንቀው እጁ ላይ ያለውን ዕቃ ሸጦ መገላገል ነው። ስለዚህ አጭበርብሮ ቢሆንም ይሸጣል። ሱቅ ያለው ሰው ግን (ቱሪስት ብቻ የሚሄዱበት ቦታ ካልሆነ) ስለነገ ስሙ ይጨነቃል። ደንበኞቹ ነገም ተመልሰው እሱ ጋር እንዲመጡ ይፈልጋል። ስለዚህ ትርፍና መታመንን አብሮ ነው የሚሸጠው። ስለዚህ የማስታወቂያ አንዱ ዓላማ መታመንን መፍጠር ነው።



ሌላኛው ሰዎች አንድን ነገር የሚያደርጉት በሁለት ነገሮች ግፊት ነው። የመጀመሪያው “በልምድ።” ሁለተኛው “ሌሎች ሰዎች ሲያደርጉ ስላየን።”

ሩዝ ሳይሆን እንጀራ በየቀኑ የምንበላው የእንጀራ ጥቅም ስለሚበልጥ አይደለም። በልምድ ከልጅነት ጀምሮ ስለምንበላ እንጂ። ስለዚህ ማስታወቂያ ሰዎች የምንሸጠውን ነገር እንዲለምዱ ማድረግ ፤ ለማስለመድ ደግሞ ከዚህ በፊት ከሚያደርጉት ነገር ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል። አንዱ ልምድ የምንፈጥረው የምንሸጠውን ነገር በተደጋጋሚ በማስተዋወቅ ነው። የዛኔ ሰዎች የኛን እቃ ይለምዱታል።



ሁለተኛው ሌሎች ሰዎች ሲያደርጉት ስናይ ነው። ሰዎች ራሳችንን ምክንያታዊ አድርገን ማሰብ ደስ ይለናል። ያ ግን ውሸት ነው። ብዙ የምንሰራቸው ነገሮች ከምክንያት ጋር የሚጋጩ ናቸው። ብዙ ነገራችን “ሰዎችን ኮፒ” ማድረግ ነው። የምንቀናው ራሱ ከእኛ ከሚበልጠው ነገር ግን ከእኛ ብዙ ባልራቀ ሰው ነው፤ ከኛ በቅርብ ርቀት በሀብት በተለየው ሰው ነው። በቢልጌት አንቀናም። ምክንያቱም አንደርስበትም ብለን ስለምናስብ፤ ከእኛ በጣም ሩቅ ስለሆነ። ነገር ግን በጓደኛችን እንቀናለን። ምክንያቱም እሱ ከኛ ጋር አቻ ነው ብለን እናስባለን። ስማርት ነጋዴዎች ይሄን የሰው ባህሪ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህ የሚሸጡት ነገር በብዙ ሰዎች የተወደደ እንደሆነ ከማሳየት በተጨማሪ፣ የፉኩኩር መንፈሶችን በመቀስቀስ ስነ-ልቦና የተካኑ ናቸው። የሚሸጡት ነገር በብዙ ሰዎች የተወደደ እንደሆነ ያሳያሉ። ታዋቂ ሰዎች የነሱን ዕቃ ሲጠቀሙ ፥ የነሱን ዕቃ መጠቀም ፋሽን መሆኑን ለሰዎች በማሳየት ፥ ሌሎች ሰዎችም መከተለ እንዳለባቸው በጥበብ ያን ስሜት በሰው ልቡና ያሰርጻሉ።



በእንግሊዝ የማስታወቂያ ጂኒየስ የሚባለው ሮሪ ሰዘርላንድ እንዲህ ይላል “ሰዎችን ወደ ሬስቶራንት በማምጣት በሼፉ (ምግቡን በሚሰራው) እና ወለሉን በሚወለውለው ሰዎች መካከል ምንም ልዩነት የለም።” ወደ ሬስቶራንት ሰዎች የሚሄዱት በዋነኝነት ምግብ ለመብላት ቢሆንም ወለሉ ከቆሸሸ ግን ስለምግቡ ያላቸው ምልከታ ዜሮ ይገባል። እውነታው ግን በወለሉ እና በምግቡ መካከል ምንም ግንኙነት የለም። ወለሉ ሌላ ነገር ፥ ምግቡ ሌላ ነገር። የሰው አዕምሮ ግን እንደዚያ አያስብም። ወለሉ ከቆሸሸ ወዲያው ምግቡም ንጹህ አይደለም ብሎ ያስባል። ሊያስታውክ ሁሉ ይችላል።

ልክ እንደዛው ነጋዴዎች ሁሉ በሰዎች ዓዕምሮ ውስጥ ስለሚፈጥሩት ስዕል በጣም መጨነቅ አለባቸው። ለዚህም ሙያ ያላቸውን ሰዎች መጠየቅ፣ ዕይታ ላይ መስራት፣ ማስታወቂያ መስራት ብቻ ሳይሆን ፥ ያ ማስታወቂያ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ስለሚፈጥረው ምስል ማሰብ እና ጥሩ ምስል ከሳች ነገሮችን መጠቀም ወሳኝ የሚሆነው።



በዚህ ጹሁፍ በትንሹ ያሳየውት እንዴት ቢዝነስ የሰዎችን ስነ-ልቦና የማወቅ ጥበብ እና የአዕምሮ ውጤት መሆን እንዳለበት ነው። ይሄ ግን በቢዝነስ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የሕይወት ክፍላችን እና በተሰማራንበት መስክ መጠቀም ያለብን ብልሃት ነው። የሰዎችን ስነ-ልቦና ማጥናት እና ማወቅ በማንኛውም ተግባራችን ፊት-አውራሪ እንድንሆን የራሱ እገዛ ያደርጋል።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10
  • 4 min read
ree

የሰንበት ዕይታ - 17


የዛሬው ጹሁፍ በውሳኔ አሰጣጥ ጉዳይ እና በሕይወት ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን ስንወስን የሚገጥሙን የስነልቦና ዝንፈቶችን (cognitive dissonance) ይዳስሳል።


ስለውሳኔ ስናስብ ስለራሳችን ማሰብ ግድ ይለናል። ምክንያቱም ለራሳችን ያለን ግምት ነው በውሳኔ አሰጣጥ ሂደታችን ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድረው። ስለራሳችን ያለን በጎ አመለካከት ለአዕምሮም ሆነ አካላዊ ጤናችን እና በሕይወት ላለን ደስታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ለዚህም ነው ስለራሳችን በጎ እና የማይለዋወጥ ምስል (consistent self-image) እንዲኖረን ብዙ ነገሮችን ስንሰራ የምንታየው።


ይሄን የማንነት ምስል ለመጠበቅ ስኬትን ለራሳችን የመውሰድ ጠንካራ ዝንባሌ ሲኖረን ውድቀትን ደግሞ ለሌሎች እንሰጣለን። ገና ልጅ እያለን በቋንቋችን ሳይቀር የሚዋሃደን ይሄ አስተሳሰብ ነው። ጥሩ ውጤት በትምህርት ስናገኝ “አገኘው!” እንላለን። መጥፎ ውጤት “ሲ” ወይም “ዲ” ስናገኝ “አስተማሪው ሰጠኝ” ነው የምንለው። ይሄ ውድቀትን ለራስ ባለመስጠት ስነልቦናዊ ማንነታችንን እየጠብቅን ነው። በዚህም ራሳችንን ከተራ ሰዎች የተሻልን እንደሆን እናምናለን፣ በእውቀት፣ በውበት፣ በባህሪ፣ በጥረት እና በችሎታ ከብዙ ሰዎች እኛ የተሻልን እንደሆን እናምናለን ወይም ማመን እንፈልጋለን።



ይሄ ስለራስ ያለ የተጋነነ በጎ አመለካከት በጥቂት ሰዎች ላይ የሚስተዋል ሳይሆን ብዙ ሰዎች ያላቸው ማንነት ነው። አንዳንዴ ግን ሕይወት ይሄን ስለራስ ያለንን ግምት ይቀደዋል (smash it)። ከሥራ እንባረራለን፣ ሰዎች ይተውናል፣ ማግኘት ተስፋ ያደረግነውን ነገር እናጣለን ወይም በሰዎች ፊት ከፍተኛ ነቀፋ ይደርስብናል ፥ እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ደግሞ ለራሳችን ከሰጠነው ግምት ተቃራኒ የሆኑ ውሳኔዎችን እንወስናለን።


ይሄ ስለራስ ባለ ልዩ እና ከእውነታው የተለየ ምስል ምክንያት ፊት ለፊት ያለን ሀቅ ለመቀበል እንቸገራለን። በዚህም ቀላል እና ጊዜያዊ የነበሩ ችግሮቻችን ሥር ይሰዳሉ። ይሄን ስሱ (fragile) የሆነ ስለራስ ያለን ግምት ለመጠበቅ ጊዜያችንን ባልሆኑ ነገሮች እናባክናለን፣ አላስፈላጊ እና ጊዜ አባካኝ ክርክሮች ውስጥ እንጠመዳለን፣ አንዳንድ ሰዎች ወደ ሱስ ወይም ለእነሱ የማይመጥን ግንኙነቶች ውስጥ ይነከራሉ።


ከዚህ ጋር በተያያዘ የቶልስቶይ ወንጀለኞች ለዚህ አመለካከት ገላጭ ምሳሌዎች ናቸው። ቶልስቶይ በልቦለዶቹ ወንጀለኞቹ ሁለት ዓይነት ስነልቦና እንዳላቸው ያሳየናል።

የመጀመሪያው እውነትን ይሸሹታል ፥ በመካድ፤ መካድ የሚከሰተው ስለሕይወት ኃያል እውነት ፊትለፊት ሲገጥመን እና ያን ከመቀበል ይልቅ መካድን ስንመርጥ ነው። ለምሳሌ ልጆቿቸው ከመስመር እየወጡ እና ያልሆነ ሕይወት ውስጥ እየገቡ የሚመለከቱ ወላጆች ይሄን ወዳጆቻቸው ሲነግሯቸው የመጀመሪያው ግብረ መልሳቸው መካድ ነው። እነዛ ያሳደጓቸው ልጆች፣ ከምንም ነገር በላይ የሚወዷቸው ልጆቻቸው በመጥፎ ሕይወት ውስጥ ተገኝተዋለ ብለው ማሰብ አይፈልጉም። ስለዚህ ወሬውን ያመጡላቸውን ሰዎች መንቀፍ ወይም መቀየም ይቀላቸዋል እውነታን ከመጋፈጥ ይልቅ።



በተመሳሳይ ቆዳችን ላይ የሆነ ጥቁር ነጥብ ቢወጣ፣ መጀመሪያ ሊያስደነግጠን ይችላል። ከዛ ግን እንረሳዋለን። ከሳምንታት በኋላ ስናየው የበለጠ ጠቆረ እንጂ የተለወጠ ነገር የለም። ምንአልባት ከዚህ ከሳምንታት መካድ በኋላ የበለጠ መጥቆሩ ከመካድ ሊያወጣን ይችላል። የመጀመሪያው ግብረ መልሳችን ግን መካድ ነው። እንዲሁ እንደወጣ እንዲሁ እንዲጠፋ መመኘት ነው።

ልጃቸው ወደጦርነት የሄደ እና ከዛ ያልተመለሰ ቤተሰብ አውቃለሁ። ጦርነቱ ካለቀ ረጅም ጊዜ ቢሆንም የልጃቸው አለመመለስን ሞቶ ነው ብሎ መቀበል አይፈልጉም፤ ሰው ሁሉ ያን ቢያምንም። ይሄ እውነታ የሚነግረኝ በጣም የምንወደው ነገር ሲሆን በዛ ነገር ላይ የደረሰ ክፍ ነገርን መቀበል ይከብደናል። በጣም የምንጠላው ነገርም ሲሆን ያ ነገር በጎ ነገር እንዳለው መቀበል እንቸገራለን። ስለዚህ ጠንካራ ስሜቶች ሁልጊዜ መካድ ይከተላቸዋል። ለምሳሌ ሂትለር ሕጻናትን የሚወድ እና ለሕጻናት ስሱ ልብ እንዳለው መቀበለ ይከብደናል። ምክንያቱም ሂትለር በብዙ ነገር ክፉ እና አረመኔ ስለሆነ። አንድ የሚሊተሪ ስትራቴጂስት “ጠላቴን አልጠላውም፣ ምክንያቱም ጥላቻ ጠላቴን እንዳላይ ይከልለኛል” ይላል። ጥላቻ የወረረው አዕምሮ ፈጽሞ ስትራቴጂክ ውሳኔዎችን መወሰን አይችልም። ፍቅርም የወረሰው አዕምሮ እውነታን የመጋፈጥ አቅም የለውም።



ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሱስ (addiction) ነው። የሰው ልዩ ባህሪው ራሱን ፍጹም መውደዱ ነው። በዚህም ማናችንም ደደብ እንደሆንን እና የሆኑ ነገሮችን ማድረግ እንደማንችል መቀበል ይቸግረናል። ለዚህ ነው በሌሎች ላይ ውበት ስናይ የሚቀናን መተቸት ወይም የሚነቀፍ ነገር መፈለግ የሚሆነው። ምክንያቱም ያ ሰው ከኛ የሚያንስበትን ነገር ነው የምንፈልገው። ሱስ ከዚህ የሚመነጭ ነው። ሱሰኛ ሰዎችን ተመልከቱ። (በርግጥ በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ማን ሱሰኛ ያልሆነ አለ?) ሁሉም በማንኛውም ሰዓት ያን ሱስ ማቆም እንደሚችሉ ነው የሚያምኑት። ምክንያቱም አልችልም የሚለው ስሜት በከፍተኛ ደረጃ ለራሳቸው የሰጡትን በጎ ስሜት (self-iamge) ይጎዳዋል። ስለዚህ ሰው ሁሉ የሚያውቀውን እውነት ይክዱታል። ከሱ መውጣት እንደከበዳቸው።



ሾፐናወር ለሰው ልጅ መቀበል ከሚከብደው አሉታዊ ስሜት ከሆኑት ትልቁ “ደደብ ነኝ የሚለው ስሜት ነው” ይላል። ይሄ ያለመቻል ስሜት ለራሳችን የሰጠነውን የተጋነነ ስሜት፣ ራስን ከመውደድ እና ስሱ (frgile) የሆነውን ማንነታችን እንዳይጎዳ ከመጠበቅ የመጣ ፍላጎት ስለሆነ ፊት ለፊት ያለውን ሀቅ እንሸሻለን፣ እንክደዋለን። ይሄ የጥሩ ውሳኔዎች ሁሉ የመጀመሪያው እንቅፋት ነው።

ሁለተኛው የቶልስቶይ ወንጀለኞች ባህሪ ምክንያት መስጠት (self-justification) ነው፤

የቶልስቶይ ወንጀለኞች ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ ያን ወንጀል በዛ ሁኔታ (context) ውስጥ ወይም በእነርሱ ላይ ከደረሰባቸው አንጻር ተገቢ እንደሆነ ምክንያት ይሰጣሉ። ጉቦ የሚሰጥ ሰው ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ጉቦ ከሚቀበለው ልዩነት የለውም። ሁለቱም ካለጉቦ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ነው የሚናገሩት። ጉቦ ተቀባዩ ያለጉቦ የኑሮ ውጣ ውረድን ማሸነፍ እንደማይችል ሲናገር ፥ ጉቦ ሰጪውም የቢሮክራሲውን ውጣ ውረድ ያለጉቦ ማለፍ እንደማይችል ነው የሚገልጸው።



ሁለቱም ወንጀል እየሰሩ እና በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቃቸውን አስነዋሪ ተግባር እየሰሩ መሆናቸውን ማመን አይፈልጉም። ይልቁስ ከመሠረታዊ እምነታቸው ጋር እንዳይጋጭ ለዛ ምክንያት ይሰጣሉ።



ምክንያት የመስጠት (justification) ትልቁ መገለጫ ማቆም ነው። ለምሳሌ ሲጋራ ለማቆም ጥሮ ያልቻለ ግለሰብ የሚያደርገው ሲጋራ መጥፎ ነው ብሎ ማመን ያቆማል። ይልቁስ ሲጋራ እያጨሱ እስከ 90 እና 80 ዓመት የኖሩ ጥቂት ሰዎችን መጥቀስ ይጀምራል ወይም “ሕይወት ማለት ካላጨስክ እና ካልጠጣክ ምኑን ሕይወት ሆነ?” ማለት ይጀምራል። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአገቱኒ መጽሐፉ የነገረን የዚህ ባህሪ ተጠቂ መሆኑን ነበር። አቆመ። ቤተክርስቲያን መሄድ እና ማስቀደስ አቆመ። ንጉሱ “ለምን አቆምክ?” ብለው ሲጠይቁት የመለሰው “መጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላኛውን አዙርለት ይላል፤ እኔ ግን መልሼ ነው የምመታው። ለነገ አትጨነቁ ይላል፣ እኔ ደግሞ ልጆች አሉኝ አለመጨነቅ አልችልም። ስለዚህ አቆምኩኝ” አለ። አለመጨነቅ ጥሩ መሆኑን ሳይሆን ፥ ለመጨነቁ ምክንያት መስጠት ተያያዘ። መታገሰን ገንዘብ ከማድረግ ይልቅ ፥ ታገሱ የሚለውን ስብከት መስማት ማቆም የቶልስቶይ ወንጀለኞች ባህሪ ነው።



በሕይወታችሁ ጥሩ ውሳኔ ለመወሰን ትፈልጋላችሁ? በተቻለ መጠን እውነታን ተጋፈጡ። ሲ ኤስ ሉዊስ ለኦክስፎርድ ተማሪዎቹ የሚላቸው ይሄን ነበር “እውነታን በጥቂቱ ካሳየናችሁ ፥ እውነትን የማየት ድፍረት በጥቂት ከሰጠናችሁ፤ ያን ጊዜ ስኬታማ ፕሮፌሰሮች እንባላለን። የኛ ዓላማ እውነትን የሚያዩ እና ያዩትን እውነት የመናገር ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራት ነው።”

እውነታው ከምናስበው በላይ ደደቦች ነን። እውነታው ብዙ ነገሮችን ማቆም አንችልም። እውነታው ስሜታዊ ነን። እውነታው ፈሪዎች ነን። እውነታው ከመጠን በላይ በሰዎች መወደድ እንፈልጋለን። እውነታው እንደምናስበው ጥሩዎች አይደለንም። እውነታው ሰንፎች ነን። እውነታው አድሎአዊ እና ዘረኞች ነን። ይሄን ስለራስ መቀበል ያማል፣ ግን ይሄን በጊዜ እንደመቀበል ምንም ፈጣን የመፍትሔ እና የለውጥ መንገድ የለም። አዎ ለዚህ ብዙ ምክንያቶችን መስጠት እንችላለን፤ ግን እውነታውን አይቀይሩትም።



ቻርሊ መንገር ስለወዳጁ ልጅ እና አባቱ ስላለው ነገር እዚህ ጋር ማንሳቱ በጣም ጠቃሚ ነው። ልጁ ከአባቱ የሳንቲም ማጠራቀሚያ “በኋላ እተካለሁ” እያለ ሁልጊዜ ይወስዳል። ይሄን ባህሪ ያስተዋለ አባት “ልጄ! ግድ የለህም ስትወስድ በኋላ እተከዋለሁ እያልክ ተደብቀህ ከምትወስድ ፥ በወሰድክ ቁጥር ሁሉ ራስህን ሌባ እያልክ ጥራ” አለው። ያ ልጅ ዛሬ አድጎ እና ተለውጦ የካሊፎርኒያ ቢዝነስ ስኩል ዲን ሆነ። መጥፎ ነገር ስናደርግ ራሳችንን በዛ ስም እንጥራው። አዎ፣ “ዝሙት እየሰራው ነው። እየሰርኩኝ ነው። ወንጀል እየሰራው ነው።” እንበል። በውሸት ምክንያት የተገነባን የራስ ምስል (self-iamge) ከመጠበቅ ይልቅ፤ ራሳችንን ለዛ ባህሪ ተገቢ በሆነ ስም እንጥራው። ከዛ ባህሪ ለመላቀቀ ትልቅ እርዳታ ይኖረዋል። ከአስርቱ ትዕዛዛት ሁለተኛው “የተቀረጸ ምስል ለራስህ አታኑር” የሚል ነው። ይሄ የተቀረጸ ምስል አንዱ የራስ ምስል (self-iamge) ነው። በምክንያት የምንጠብቀው፣ እውነትን በመካድ ያቆምነው፣ ይሄ ስሱ ምስል (fragile self-image)፣ የሰዎችን መጥፎ ንግግር እና ነቀፋ መቋቋም የማይችለው ፣ በተግሳጽ እና በአሉታዊ ኮሜንት የሚፈርሰው ፣ ላይክ እና አስመሳይ የማሽሞንሞን ቃሎች የሚያለመልሙት የተቀረጸው የራስ-ምስል (carved self-image) ለጥሩ የሕይወት ውሳኔ ሁለተኛው እንቅፋት ነው።


 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10
  • 3 min read
ree

የሰው ልጆች በሁሉም ወቅት የሚሰራ መመዘኛ የለንም። መመዘኛችን እና የሞራል እይታችን በደረስንበት የእይታ ጥራት እና አድማስ የሚወሰን ነው። ይሄ ማለት ዘመን እና ድንበር ተሻጋሪ የሞራል ልኬቶች (universal values) የሉንም አይደለም። ለምሳሌ ደግነትን የትኛውም ማህበረሰብ በየትኛውም ስፍራ እንደ ጥሩ እሴት ያከብረዋል። ጥያቄው በአንድ ወቅት ደግነት ተብሎ የሚወሰድ ጉዳይ በሌላ ጊዜ ክፋት ሊሆን ይችላል። ይሄ ተቀያያሪ የሆነ የይዘት ሁኔታዎች የሰው ልጅን የመመዘኛ ድክመት ነው የሚያሳየው። ይሄ ማለት ግን ጽንፎችን የሰው ልጅ አያውቃቸውም ማለት ላይሆን ይችላል። ለአንዱ ሙቀት የሆነ ለሌላው ኖርማል የዓየር ጸባይ ሊሆን ይችላል። ግን የትኛውም የሰው ልጅ ላይኖርበት የሚችል የሙቀት መጠን አለ። በሚዛን ደረጃ ጽንፎችን የማወቅ አቅም አለን ማለት ነው። ፍጹም ምቾትን እና ፍጹም የሆነ ስቃይን የማወቅ አቅምም እንደዚሁ። በፍጽምና መኃል ስላሉት ጉዳዮች ግን በትክክል የሚመዝን አዕምሮ የለንም።



ይሄን በሕመም እንየው። ከእግር በታች ሰውነታችን ሕመም ቢደርስበት፤ በዛ ቦታ ያለው የነርቭ ሥርዓታችን ለአዕምሮአችን መልዕክት ያስተላልፋል። መልዕቱን ተከትሎ አዕምሮአችን ያ ቦታ አደጋ ውስጥ እንዳለ በመግለጽ፤ እዛ ቦታ ላይ እብጭ፣ መቅላት እና ሕመም እንዲኖር ያደርጋል። አዕምሮአችን ያን የሚያስተላልፈው ያን ስፍራ ከመጠበቅ አንጻር ነው። ያ ሕመም ያለበትን አካል በመጠቀም የበለጠ እንዳንጎዳው ያሳብጠዋል ወይም ሕመም ያኖራል። የአዕምሮ ተቀዳሚ ሥራ እኛን ከአደጋ መከላከል ነው። ልክ ነኝ ወይም ልክ አይደለውም የሚለው የአዕምሮ ተቀዳሚ ተልዕኮ አይደለም። ተቀዳሚው ተልዕኮ መጠበቅ (protect) ወይም መከላከል ነው።



አንዳንድ ጊዜ ግን አዕምሮ የተሳሳተ ሲግናል ይልካል። ለምሳሌ Complex Regional Pain Syndrome (CRPS) የሚነግረን ምንም እንኳ የታመመው የሰውነት አካል ቢድንም አዕምሮ ግን እስካሁን እንዳልዳነ ሊቆጥረው ይችላል። ስለዚህ እነዛ የሕመም ምልክቶችን በመላክ እብጠት እና መቅላት፣ ሕመም እንዲቀጥል ሊያደርገው ይችላል። ይሄ መጀመሪያ ከደረሰው የሕመም ከባድነት የተነሳ፤ ሰውነታችን ቢድን እንኳ፤ አዕምሮአችን ግን ሕመሙ ላይ ቀርቷል። ከሰውነታችን ጋር አብሮ ራሱን አላሻሻለም። በዚህም የሕመም ሲግናል (ምልክት) በተከታታይ ይልካል።



ለዚህ አንዱ የሚደረገው አዕምሮ እነዛን የሕመም ሲግናሎች መላክ እንዲያቆም ማሰልጠን ነው። አዕምሮአችን በየዕለት ሕይወታችን የሚያደርገው ይሄንን ነው። እኛን የመጠበቅ ተልዕኮ ስላለው፤ ከዚህ በፊት ውሻ የነከሰው ሰው ፥ ለውሻ የሚኖረው ፍርሃት ወደር አይኖረውም። ሁሉም ሰው ውሻውን እየዳሰሰ እርሱ ግን ከዛ ውሻ ይሸሻል። አዕምሮ ይሄን ሰው በማንኛውም ሁኔታ መጠበቅ ስላለበት፤ ከዚህ በፊት በውሻ የደረሰበትን እንዳይረሳ በማድረግ ይጠብቀዋል። ምንአልባት ሰውዬው ለራሱ ማጽናኛ ቃሎችን ሁሉ ሊጠቀም ይችላል። “ውሻ አይወደኝም ወይም የውሻ መወደድ የለኝም” እና የመሳሰሉት እምነቶችን።



ይሄ ግን በግለሰብ ደረጃ ብቻ እንዳይመስላችሁ። በማህበረሰብ ደረጃም በወል አዕምሮ ውስጥም ተመሳሳይ እሳቤዎች አሉ። በፖሊሲም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ይገዛ የነበረን ብሔር ሌሎች የማህበረሰብ አካላት ሊፈሩት እና “ከመጣብን የቀደመውን ይደግማል” በሚል ፍርሃት ሊያሳዱት ይችላሉ። ለምሳሌ በሴፕቴምበር አስራ አንድ የደረሰው የሽብር ጥቃት እንዴት በዓለም ላይ ያሉ ሙስሊም ያልሆኑ ማህበረሰቦችን እይታ እንደቀየረ ተመልከቱ። የጥቂት ሰዎች አውሬነት የብዙ ሰዎች ተደርጎ በፖሊሲ ደረጃ ምንም በዚህ ጉዳይ ላይ የሌሉ የእምነቱ ተከታዮች ለአሰቃቂ ጥቃት ተጋልጠዋል።



አሁን በአሜሪካ ውስጥ የምናየው የኢሚግሬሽን ፖሊሲም የዚህ ስሁት ሪያክሽን ውጤት ነው። ጥቂት ከሌሎች ሀገራት የመጡ ሰዎች በፈጸሙት ወንጀሎች ብዙ መልካም ማንነት ያላቸው ሰዎች በጅምላ ይፈረድባቸዋል። ለሁሉም ጥላቻ ይኖራቸዋል። “ለምን እንደዚህ ታደርጋላችሁ?” ሲባሉ፤ አንድ ሰነድ አልባ ስደተኛ የሆነ ቦታ እና ጊዜ ያደረገውን ወንጀል እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ። ይሄ የሲግናል ግራ መጋባት ነው። ብዙ ጊዜ ለዚህ የሚዳረጉ ሰዎች የተጋላጭነት መጠናቸው በጣም ጠባብ የሆኑ ናቸው።



በቅርብ አንዱ ከኢትዮጵያ ስለ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለክርስትና መስፋፋት እንቅፋት እንደሆነች ጻፈ። ይሄ ሰው ምን አልባት ከአዲስ አበባ የዘለለ የሕይወት ተጋላጭነት የለው። ስለ ካቶሊክም የሰማው ከኢትዮጵያ ወጥተው በማያውቁ ሰዎች ከተጻፉ መጽሐፎች ይሆናል። አውሮፓ በየሀምሳ ሜትሩ ቤተክርስቲያንን የተከለች፣ በቢሊዮን የሚቆጠር አማኝ ያላት ቤተ እምነት እንደሆነች ምንም እውቀቱ የለውም።



አንድ ወዳጄ ስለነጮች ያለው አመለካከት በጣም ጠባብ ነው። የእኔ ጥያቄ የነበረው “ምን ያህል ነጭ የቅርብ ወዳጅ አሉህ? ወይም በበዓል ቀናቸው የምትሄድበት ነጮች አሉ? ወይም የሴት ጓደኛ ከነጮች ይዘህ ታውቃለህ? የሚል ነበር። መልሱም የሉኝም። አላውቅም ነበር።



ለComplex Regional Pain Syndrome (CRPS) የሚመከረው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የተጎዳውን የሰውነት ክፍል ለተለያዩ ቴምፕሬቸሮች፣ ንክኪ እና እንቅስቃሴ ማጋለጥ ነው። በዚህም አዕምሮ ቀስ እያለ ያ ቦታ መዳኑን ይማራል። ስለዚህ ቀስ እያለ የስህተት የሕመም ሲግናሎችን መላክ ያቆማል ማለት ነው።



ትግሬን ወይም አማራን ወይም ኦሮሞን የሚጠላ ሰው የምመክረው፣ ወጥቶ ከእነዚህ ብሔሮች ብዙ ወዳጆች እንዲያፈራ ነው። ቀስ እያለ ያለው አስተሳሰብ ፍጹም ከእውነት የተቃረነ እንደሆነ ይማራል። ለምሳሌ በወንድ የተደፈረች ሴት ሁሉም ወንዶች መጥፎ እንደሆኑ ልታስብ ትችላለች። ከዚህ ስሁት አስተሳሰብ ብቸኛ የሚያወጣት ራሷን ለሌሎች ወንዶች ስታጋልጥ ነው። ፍርሃትህን በመጋፈጥ ብቻ ነው የምታሸንፈው። ይሄም የአዕምሮ ካርታን (GPS/Map) ማደስ ይባላል። አዕምሮአችን የሆነ ቦታ ለመድረስ የሚያውቀው GPS (Map) አለው። ያ GPS (map) አሁን ላይ አይሰራም። ዓለም ተቀያይሯል። ቁስሎች ድነዋል። ግን አዕምሮአችን ያው የጥንቱ GPS (map) ላይ ነው። ያንን እንዲቀይር ማድረግ የሚቻለው ቦታዎቹ ላይ በመሄድ (exposing the brain) የተለወጠውን ነገር በግድ በማሳየት ነው። አለበለዚያ ግን ከእውነት የራቁ እና ለሕይወት እንቅፋት የሆኑ ውሳኔዎችን እየወሰንን እንቀጥላለን።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page