የሰንበት ዕይታ - 4
- Mulualem Getachew

- Aug 10
- 2 min read

ኖሕ መርከብን ለመገንባት 20 ዓመት ነበር የፈጀበት። 20 ዓመት መሉ ያን ግዙፍ መርከብ ሲገነባ ሰዎች ያሾፉበት ነበር ምክንያቱም ሰማዩ የጠራ ነበር ፥ አንዳች ዝናብ የሌለበት፣ ፀሐይ በሰዓቷ ትወጣለች በሰዓቷ ትገባለች፣ ቀኑ በሰዓቱ ነግቶ በሰዓቱ ይመሻል፣ ዓየሩ የመለወጥ ምልክት አያሳይም፤ ሁሉም ዑደቱን ጠብቆ ነበር የሚጓዘው። የማያቋርጠው ዝናብ መዝነብ እስከሚጀምር ኖሕ ነበር ሞኙ። ኖሕ ነበር ጊዜ አባካኙ፣ ኖሕ ነበር ያልገባው፣ ኖሕ ነበር ያለፈበት፣ ኖሕ ነበር ነቄ ያልነበረው፣ ኖሕ ነበር የሚሾፍበት፥ ያ ዝናብ እስኪጀምር።
በሕይወትም እንደዛ ነው ፥ ፈተና እስከሚደርስ የማያጠኑ፣ ችግር እስከሚመጣ ገንዘብ የማጠራቀም ጥቅሙ የማይታያቸው፣ ብቸኛ እስከሚሆኑ ዝምድና የማይገነቡ፣ እድሜያቸው ጨምሮ በሽተኛ እስከሚሆኑ ስለሚበሉት ምግብ የማይጨነቁ፣ በዶክተር እስከሚነገራቸው ስፖርት የማይሰሩ ፥ የመከራ ዝናብ እስከሚዘንብ መርከብ የማይገነቡ ሰዎች ብዙ ነን። ዝናቡ አንዴ መዝነብ ከጀመረ ግን ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ነው ፥ ፋይዳ የሌለው ሩጫ ፥ ትርጉም የሌለው ጭንቀት፣ ሰሚ የሌለው ዋይታ ብቻ ነው።
ከዓመታት በፊት ከአንድ ኢአማኒ ወዳጄ ጋር እንደቀልድ ስንወያይ በዚህ ምድር እንዴት በፍቃዳችን መከራ መቀበል እንዳለብን እና ያ ደግሞ ለሚመጣው ዓለም ዋስትናችን እንደሆነ ስነግረው ፥ “አንተ እኮ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን እንደጣለችው እየሆንክ ነው፤ ገና ለገና ያን አገኝ ብለህ እጅህ ላይ ያለውን ደስታ አሳልፈ ትሰጣለህ” አለኝ። ፈተነኝ። ከባድ ምት ነበር። ነገር ግን በሕይወታችን ይሄን ወዳጄ ጨምሮ በየቀኑ የምናደርገው በፍቃዳችን የብብታችንን እየጣልን ተስፋ የምናደርገውን ለመያዝ አይደለም የምንዘረጋው?
ቀኑን መሉ እየተራገጠ እና እየቦረቀ ከሚውል (እጁ ላይ ያለውን የዛሬ ደስታ) ይልቅ ነገ መኖሩን እርግጠኛ ላሎነለት ዓለም አይደል እንዴ ተማሪ ዛሬ የሚጨነቀው? ስንቶቻችንስ ዛሬ እጃችን ላይ ያለው ገንዘብ ሊሰጠን የሚችለውን ደስታ ገታ አድርገን (ብብታችን ውስጥ ያለውን ትተን) ነገ ተጠራቅሞ አንድ ቁም ነገር ላይ ለማዋል ገንዘባችንን እናጠራቅም የለ። ይሄስ ተስፋ የምናደርገውን ነገር በዛሬ ስቃይ ለመያዝ መዘርጋት አይደለምን? ስንቶቻችን አይደለን ምራቃችንን እየዋጥን ለነገ ጤናችን ስንል ስንት አሁን ላይ የሚጥመንን ምግብ የምናሳልፈው። እነዚህስ ሁሉ ከተስፋ ውጪ ምን ዋስትና አላቸው? ብዙ ሰዎች ተጠንቅቀው የዛሬን ደስታ አሳልፈው ለነገ ያቆዩትን ሳይጠቀሙ ከመካከላችን እንደተለዩን እያየን እንኳ ፥ መቼ በነገ ተስፋ ቆርጠን እናውቃለን? መቼ የዛሬን ሕይወት በጥቂት ስቃይ ለነገ ከማስተላለፍ ተቆጥበን እናውቃለን? አባካኝ የሚባለው ሰው ሳይቀር በሆነ መጠን ለነገ የዛሬን ደስታ የሚገብርበት ንቃተ ሕሊና ቀርቶለታል።
በመኃል ይሄን የኑሮ እውነት ወደ መግለጽ የገባውት፤ የሰው ልጅ ለዚህ ዓለም የተፈጠረ እንዳልሆነ ተፈጥሮው ራሱ እንዴት እንደሚመሰክርበት ለማሳየት ነው። ሰው ከሃይማኖት የሚፈልገው የዕለት ሕይወቱን ከሚመራበት የምክንያት ሚዛን በላይ ስለሆነ እንጂ፤ የሰው ተፈጥሮ ራሱ ተስፋ ለምናደርገው ነገር ስቃይን ዛሬ በፈቃድ መቀበል ላይ የተመሰረተ ነው።
ወደ ቀደመው ነገር ልመለስ፤ ኖሕ እንዴት በጉብዝናው ወራት የመከራውን ወራት መርከብ እንደሰራ እና በጉብዝናቸው ሰዓት ያሾፉበትን ሰዎች እናያለን። ጠቢቡ ሰሎሞን እንዳለው የጭንቀት ቀን ሳይመጣ፣ ያ መጥፎ የምንለው ወራት ሳይደርስ፣ ሁሉም አልቃሽ፣ ሁሉም ራሱን የማዳን ሩጫ፣ ሁሉም የኩራዝ ጋዛቸው አልቆ ሊገዙ ወደ አደባባይ የመሮጣቸው ወራት ሳይመጣ ፥ የሕይወት መርከባችንን እንስራ። ትላንት መርከብ የሰሩ ሰዎች የዛሬ የመዓት መከራ ላይ ሲንሳፈፉ እያያችሁ ነው። ትላንት ዘረኝነትን የዘሩ፣ ሕዝብን የጨፈጨፉ፣ ሁሉን ማስተንፈስ ስለቻሉ ዘለዓለም የሚገዙ መስሏቸው ሁሉን ፈሪ ብለው ተዘልለው የተቀመጡ እንዴት እንደወደቁ እንዳያችሁ አትዘነጉትንም።
ከአሁኑ የሕይወት መርከባችንን እንስራ ፥ የመከራ ዝናብ ሳይዘንብ የጥበብ እና የአስተዋዮች ኑሮ እንኑር። ዛሬ አስረስ ምቺው ካሉት ጋር ስላላልን ሞኝ ነን ፥ ነገ ግን እኛን ዛሬ ሞኝ ያሉን ሲጠፉ እኛ በመከራ ዝናብ ላይ እንሳፈፋለን። ዛሬን ሞኝ ለመባል የደፈረ ብቻ የነገ ብልሕ ይሆናል። ዝናቡ እስኪጀምር ሞኝ ሆነን መርከባችንን እንስራ።






Comments