
ከማኬቬሌ እስከ ሀገራችን ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ድረስ የሚነግሩን ሕዝብ እና ሰው የተለያዩ መሆናቸውን ነው። ሁለቱም ስለሰው ባህሪ ብዙ የጻፉ ናቸው። ግን ሕዝብ ሰው አይደለም ብለውናል። ከበደ ሚካኤል ጎርፍ ሲለው ማኬቬሌ የሚወደውን የሚያጠቃ ፍጥረት ነው ይለዋል። በርግጥ ከሩቅ ሲታይ ሕዝብ የነጠላ ሰዎች ጥርቅም ይመስላል።የሰዎችን ባህሪ ካወቅን ደግሞ ሕዝብ እንዴት መልስ እንደሚሰጥ ማወቅ አይከብደንም ልንል እንችላለን። ግን ሕዝብ የሰዎች ስብስብ ቢሆንም እንደሰዎች አያስብም። ለግለሰቦች የረፈደው ሰዓት ለሕዝብ ገና ልጅ ነው። ለግለሰቦች ጥሬ የሆነው ለሕዝብ በስሎ ጎርምቷል። ሕዝብ የማይታወቅ የማሰቢያ ቅል አለው። የሚመቆው እና የሚበርደው፣የሚገነፍለው እና የሚረጋው በምክንያት አይደለም። ምክንያት ከሕዝብ ጋር አይስማማም። ሕዝብ ከፍ ለማለት መሰላል ሊሆን ይችላል ፥ ከፍ ብሎ ጸንቶ ለመቆም ግን መሠረት አይሆንም። ሕዝብ ከላይ አውርዶ የሚጥል ንፋስ ሊሆን ይችላል ፥ቀብሮ የሚያስቀር የመቃብር ድንጋይ ግን አይደለም።
ሕዝብ ማለት ራቆቱን ያየውን ንጉስ እንደ ለበሰ እና ከመልበስም በላይ በውብ አቻ በማይገኝለት መከናነቢያ እንደተጎናጸፈ ለማመን ምንም ሰቀቀን የለበትም። ፈቅዶ ለመታወር ሕዝብ አያመነታም። እጅግ ምክንያታዊ እና አስተዋይ ሰው ፥ ሕዝብ ሲሆን ጠባዩ ይቀየራል። ምክንያትም፣ ማስተዋልም መለያዎቹ መሆናቸው ይቀራሉ። ሕዝብ የራሱ መልክ እና ጠባይ አለው። የአመለከውን ለመስቀል፣ የሰቀለውን ለማምለክ ለሕዝብ ምንም አይቸግረውም።
ከሃምሳ ዓመት በላይ ሕዝብ ሲወርድ ሲውጣ እርሱ ግን ከቢዝነስ ስኬት ወርዶ የማያውቀው ዋረን በፌት እንዲህ ይላል፤ “ሌሎች ስስታም ሲሆኑ አንተ እጅህ ይፈታ ፥ ሌሎች እጃቸው ሲፈታ ደግሞ አንተ ስስታም ሁን።” በዚህ ዓለም ላይ ከባዱየቤት ሥራ እውነትን ማወቅ ነው፤ አንድ ግን እውነት የማይገኝበትን ቦታ ልንገራችሁ ፥ ከሕዝብ ዘንድ። እውነት ወዴት እንደሆነች ማወቅ ቢሳናችሁ፤ ፈጽሞ መሆን የማትችልበትን ቦታ ግን እናውቃለን። ከሕዝብ ዘንድ። እውነትን የሚፈልግ ሁሉ ከሕዝብ ውጪ መፈለግ ይኖርበታል። ሕዝብ ሰፊ መንገድ ይፈልጋል፤ ምክንያቱም ጠባብ አይበቃውም።
የአይሁድ ሸንጎ ያደረገው እኛ በየቀኑ የምንለውን ነው። “ይሄ ሁሉ ሰው እንዲህ እያመነ አንተ እንዴት ትለያለህ” ብለን ብዙ ጊዜ እናውቃለን። “አረ ሰው ምን ይልሃል!” የሁልጊዜ ቋንቋችን ነው። ይሄ የአይሁድ ሸንጎ ፍርድ ነው። ግን የኛም ፍርድ ነው። የቀያፋ ፍርድ ነው ይሄ። ብዙ ነገራችን በየዕለት ሕይወታችን በሕዝብ ውሳኔ የተመራ ነው። ምክንያቱም ሕዝብ ማሰብን አይወድም መመሳሰልን (conformity) እንጂ። እውነት ግን በተቃርኖ ወይም ኢደመነፍሳዊ ውስጥ ነው ያለችው።
የተቃርኖ ጌታ ራሱ የእውነት ጌታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “ማንም ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።” “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ መጨረሻ ይሁን።” “ጌታም መሆን የሚሻ ባሪያ ይሁን” አለን። “ሸክም የከበዳችሁ ኑ ወደ እኔ የእኔን ቀንበር በትከሻችሁ ተሸከሙ የዛኔ ታርፋላችሁ”አለን ማረፍ ቀንበር በመሸከም መሆኑን ሲነግረን። “የሚሰጥ ከሚቀበል በላይ ይበለጽጋልም” አለን። እነዚህ ሁሉከሕዝብ የተለዩ እውቀቶች ናቸው። እውነቶች ናቸው ከሕዝብ ጋር ግን የማይሄዱ። የሞቀ ውሃ ከቀዝቃዛ ውሃ ቀድሞ በረዶ እንደሚሰራ በሳይንስ እናውቃለን። የሚጨው ውሻ እምብዛም እንደማይናከስ ከልምዳችን ደርሰንበታል።በተመሳሳይ ፥ ሪያሊቲ ያለው ለስሜታችን በቀረበው እና በሚመስለው ውስጥ አይደለም። ከደመነፍሳችን ተቃራኒ ስንሄድ ነው፤ ከሕዝብ ውጪ ለመቆም ስንደፍር ነው ሪያሊቲን ማየት የምንችለው።
እና ምን ለማለት ፈልገህ ነው ጃዌ ህዝብ አይደለም ነው እኔ ግን እላለሁ ጃዌ ብቻውን ህዝብ ነው