ትችት
- Mulualem Getachew

- Aug 10
- 4 min read
የሰንበት ዕይታ - 7
አንድ ወዳጄ ስለትችት ወይም ሰዎችን ስለመተቸት እንድጽፍ ጠየቀኝ። በርግጥ የወዳጄ ትልቁ ጥያቄ ያለአቅም እና እውቀት ስለመተቸት ነው። እኔ እንደሚገባኝ ትችት ማለት አንድ ነገር ከምንጠብቀው ደረጃ በታች ሲሆን ወይም ትችት የሚቀርብበት ማየት ያለበትን ነገር ሳያይ ሲቀር ወይም የሆነውን ነገር በእውቀትም ሆነ ያለ እውቀት ሲያጣምመው የምናቀርበው ነቀፋ ወይም ስህተትን በጠንካራ ድምጸት ማሳየት ነው። ስለዚህ ለመተቸት እኔም ሆነ ተተቺው የተቀበልነው የጋራ ደረጃ (standard) ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ ይሄ አባት ተሳስተዋል ለማለት ፥ የሆኑትን ወይም የተናገሩትን ነገር ከእኔም ሆነ ከዛ አባት ውጪ ከሆነ ደረጃ (standard) ጋር በማዛመድ ነው ተሳስተዋል ማለት የምችለው። ያ ደረጃ ከሌለ ልል የምችለው ብቸኛ ነገር ያ አባት ተሳስተዋል ሳይሆን ለእኔ አልተመቹኝም ነው።
ምክንያቱም ደረጃው የጋራ ሳይሆን የእኔ ስሜት እና እውቀት ነው፤ ያ ስሜት እና እወቀት ከሌላው ጋር የምጋራው የጋራችን ካልሆነ ፥ እኛን አባት ስህተት ሊያስብል የሚችል ምንም ነገር የለም። በርግጥ ሌላ ክርክር ሊከፈት ይችላል። በራሳቸው ደረጃ (standard) ነው የመዘንኳቸው ሊል ይችላል። ያ ቢሆን ራሱ “የትኛው የራሳቸው ስታንዳርድ?” ትላንት የተናገሩት ወይስ ዛሬ ከተናገሩት ወይም ሆነው በተገኙት ስታንዳርድ? ትላንት ከተናገሩት ከሆነ ስህተቱ የሳቸው ሳይሆን የኛ ነው። ምክንያቱም እየተቸን ያለነው የትላንቱን ሰው ሳይሆን የዛሬውን ሰው ነው። በትላንት ንግግር መተቸት ያለበት የትላንቱ ሰው ነው እንጂ የዛሬው አይደለም። ስለዚህ ዛሬ ከተናገሩት ከሆነ ደግሞ ምንም የሚያስተች ነገር የለም ምክንያቱም ዛሬ የተናገሩት ነው የሳቸው ደረጃ።
ስለዚህ ትችት ትርጉም እንዲኖረው የጋራ የሆነ ሚዛን ያስፈልጋል። ሁለት ሲደመር ሁለት አምስት ነው የሚልን ሰው ልክ አይደለህም የምንለው የትም ቦታ ያ አራት መሆን አለበት ብለን ስለተስማማን ነው። ግን ያ የኛ ስምምነት ብቻ አይደለም፤ ይልቁስ የኛ ስምምነት በራሱ የጸናው በሆነው ነገር ነው። ሁላችን ብንስማማ እንኳ ሁለት ሲደመር ሁለትን አምስት ማድረግ አንችልም። በንድፈ ሀሳብ ተስማምተን ወደ ተግባር ስናወርደው ይከሽፋል። አራት ብርቱካንን ስለተስማማን አምስት ማድረግ ፈጽሞ አንችልም። አምስት ሰው አስቀምጠን አራቱን አንድ አንድ ለአምስቱም ማከፋፋል አንችልም። ስለዚህ ስምምነታችን ከኛ ስምምነት ውጪ ባለ እውነት፣ በራሱ መቆም በሚችል እውነት እስካልተደገፈ ድረስ ይፈርሳል። ማንም ማንንም ከመሬት ተነስቶ መጉዳት የለበትም የሚል ሰው ይሄን ለማለትኽ መሠረትኽ ምንድነው ብንለው፤ እንደዛ ይሰማኛል ብቻ ካለን ፥ ሌላውን ያለምንም ምክንያት የሚጎዳ ሰውም እንደዛ ይሰማኛል ብሎ ቢጎዳ ስህተቱ የቱ ጋር ነው? ነገር ግን ከዚህ የጠለቀ እውነት ሊኖረው ይገባል።
ለምሳሌ በልጅነቱ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የሰው ጓሮ ገብቶ ፍራፍሬ የሰረቀው አውግስጢኖስ ፥ ሌብነት መጥፎ መሆኑን ማንም አስተማሪ ሳይኖር እናውቃለን ይላል። ይሄን ሲመልስ ሌባ እንኳን ሌላ ሰው መጥቶ የእሱን እቃ እንዲሰርቅበት አይፈቅድም። ሌባ ሆኖ ሳለ እንዲሰረቅ አለመፈለጉ የድርጊቱን ሁሉንአቀፋዊ መጥፎነት (universal evilness) ይናገራል። በጎ ነገር ስናደርግ ያን በጎ ነገር ሰዎች ለእኛ እንዲያደርጉልን እንፈልጋለን። ቢያንስ ተመሳሳይ ነገር እንዲመልሱልን ባንፈልግ እንኳ ያ የበጎነት ስሜት ግን ስለእኛም እንዲያድርባቸው እንሻለን። ማናችንም ግን ክፉ ነገር ስናደርግ እነዛ ሰዎች ያን ክፉ ነገር በእኛ ላይ እንዲያደርጉብን አንሻም።
ይሄን ሁሉ ያልኩት ለመተቸት የጋራ የሆነ ደረጃ (standard) ሊኖረን እንደሚገባ ለማሳየት ነው። ድልድይን በሙስና ያለጥራት የሚሰራ መሐንዲስ፤ ሌሎች መሐንዲሶች ግን ድልድዮችን በጥራት እንዲሰሩ ይሻል። ያ ግን የሱ ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከሱ ውጪ ያለ ፍላጎት ነው። የሱ ፍላጎትማ በሙስና ለጥራት ባለመጨነቅ መስራት ነው። ግን ከተግባሩ በተቃራኒ ይፈልጋል። ምክንያቱም ያ ፍላጎቱ ተራ ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከሱ እና ከሌሎች ውጪ ባለ እውነት ላይ የቆመ እንጂ። ያ እውነት ደግሞ ጥራት ያለው ድልድይ ነው፤ እሱንም ሆነ ቤተሰቦቹን ያለስጋት በዛ ድልድይ የሚያሻግረው። እውነት የምንለው ነገር ከኛ የማድረግ እና ያለማድረግ ተጽዕኖ ውጪ ሕልውና ሲኖረው ነው። ለዚህ ነው እውነት የሆነው። በእኔ ማድረግ እና አለማድረግ ስላልተወሰነ። እኔ በሙስና የምሰራ እንኳ ቢሆን ፥ የእኔ ድርጊት ተግባሩን ጥሩ እንደማያደርገው ከሌሎች በጠበኩት ደረጃ ገለጥኩኝ። ደረጃው የእኔ ቢሆን ኖሮ ፥ ሌሎች እንዲህ ማድረግ አለባቸው ባላልኩኝ ነበር። ያን ብል እንኳ የሚሰማኝ የለም፣ ሰዎች ችላ ለማለትም ስጋት አይገባቸውም። ደረጃው ግን ሁሉን አቀፍ ስለሆነ ካልተሸሸግን በቀር በይፋ አናደርገውም።
ስለዚህ ትችት ሁልጊዜ ከእኛ እና ከዛ ሰውዬ ተራ ፍላጎት ነጻ ሲሆን ነው ትርጉም የሚኖረው። ካሮት ወዳለው የሚልን ሰው እና ካሮት ስላልወደድን ብቻ አንተቸውም። የእኛ ካሮት አለመውደድ የእኛ ወይም የጥቂቶች ብቻ ስለሆነ ግን አይደለም። ካሮትን መብላት ከምግብነት አንጻርም ጥቅም እንዳለው ስለምንገነዘብ እንጂ። ጥቅሙ ደግሞ በሌሎች ተጓዳኝ የፍትሕ እና የመልካም ሕይወት አኗኗር ላይ ጉዳት ስለሌለውም ጭምር ነው። ማለትም ለምግብነት ጥሩ ሆኖ ሌሎች የመልካም ሕይወት ጉዞዎችን የሚያደፈርስ ቢሆን አንቀበለውም። ይሄ የሚያሳየን እኛ ባናረገው ራሱ የማያሳነቅፍ ነገሮችን ስንዳኝ ምን ያህል ከኛ ውጪ ባለ መለኪያ እንደምንመዝን ነው።
ፍትሐዊ ትችት ሚዛኑ ሁልጊዜ ከተቺው ጊዜያዊ ጥቅም እና መሻት የሚሻገር ነው። ይሄ ማለት አንድን ነገር ተቺው ስለወደደው እና ስለጠላው ሳይሆን ከሱ ውጪ ያለ የፍትሕ እና የእውነት ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው የሚዳኘው። ከኛ ውጪ ያለን ነገር ደግሞ የምንረዳው ባለን የእውነት እና የፍትሕ ዓይኖች የአድማስ ስፋት እና የሕይወት ልምድ ነው። ልጆችን ብዙ ነገር እንዳያደርጉ የምንከለክለው ያ ነገር በራሱ መጥፎ ስለሆነ ብቻ ላይሆን ይችላል፤ የከለከልናቸው ነገር ያለአግባብ ከተጠቀሙበት የሚያመጣውን ጉዳት በማሰብ እንጂ። ለምሳሌ የሦስት እና አራት ዓመት ልጅ ውጪ ወጥቶ መንገድ እንዳያቋርጥ የምንፈልገው፣ መንገድ ማቋረጥ በራሱ መጥፎ ሆኖ አይደለም። ነገር ግን ዕድሜው ግራ ቀኙን የማየት አቅም ስለማይሰጠው፣ ልሻገር ሲል አደጋ ሊደርስበት እንደሚችል ስለምናውቅ እንጂ።
ያ እውቀታችን ደግሞ ከወላጅነት ከሚመጣ ለኛ ግለሰባዊ ከሆነ መሳሳት ብቻ አይደለም። አደጋ ደርሶ ስላየን እና ራሳቸውን ከአደጋ መከላከል የማይችሉትን ልጆቻችንን አለመጠበቅ መጥፎ ወላጅነትም እንደሆነ ስለምንገነዘብ ነው። ይሄ የሚነግረን ከኛ የሕይወት ልምድ፣ እውቀት፣ የሥራ እና የዕድሜ አድማስ ውጪ የሆኑ ነገሮችን መተቸት ምን ያህል ልክ እንዳልሆነ ነው። ምክንያቱም ትችት ከኛ ውጪ ባለ መስፈርት ሲመዘን ብቻ ነው ፍትሐዊ እና ትክክለኛ ትችት የሚሆነው፤ ያ እንዲሆን ደግሞ ፥ ያ ከኛ ውጪ ስላለ ሚዛን እና ደረጃ ከምንተቸው ሰው የማይተናነስ እውቀት ሊኖረን ይገባል። ካለዛ ግን እያልን ያለነው “ለእኔ አልጣመኝም፣ እኔ ካሮትን አልወድም ስለዚህ ካሮትን የሚወድ ሁሉ መጥፎ ነው” ነው። ያ ደግሞ ትችታችንን ኢፍትሐዊ ያደርገዋል። ስለእኛም ግልብነት ይናገራል። በጠባብ የራስ ፍላጎት ላይ የቆመ ስለሆነ ፍጻሜው እፍረት ነው።
ልጅ በሆንባቸው ዘርፎች ወላጅ የሆኑ ሰዎችን መተቸት ትርጉም አይኖረውም። በእነዚህ ጉዳይ ከትችት ይልቅ መጠየቅ እና ያልገቡንን ለመረዳት መጣር ነው ተገቢው እርምጃ። ከአንድ እውነት ጋር ግን መጋፈጥ አለብን። ያለእውቀት እና ያለምንም ልምድ የሚተቹ ደፋሮች በየትኛውም ጊዜ እንደሚኖሩ። ያ ብቻ አይደለም የእነሱን ስሜት እና ከእነሱ ውጪ ያለን ደረጃ (standard) ለይተው ማየት የማይችሉ ሰዎችም አሉ። ይሄ ማለት ለእነሱ ጆሮ ያልጣማቸውን ሙዚቃ መጥፎ መዚቃ የሚሉ፤ እንዲሁም እነሱ የወደዱትን ሙዚቃ ሰዎች ካልወደዱ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የደረጃ (standard) ጉዳይ አድርገው የሚደባልቁ ሰዎችም በስፋት አሉ። ገበያ ውስጥ እየገቡ ዝምታን መሻት ቅዠት እንደሆነ ሁሉ፤ የአዕምሮ እና የችሎታ ውጤቶቻችንን ለማህበረሰብ ገበያ እያቀረብን ጉራማይሌ ግብረ መልስ አለመጠበቅ የዋህነት ነው። እያደናገሩ ለሚኖሩ እንጂ የማህበረሰብን የምቾት ሀጢያት እና ያለአዋቂነት ስንፍና እየገለጡ ለመኖር ለቆረጡ ክብር እና አድናቆትን ወዲያው መሻት ከረዥሙ የሰው ልጆች የታሪክ እውነት ጋር መጋጨት ነው። ታሪክ ያሳየን ከሚሰክሩ ጋር አብረው ለሰከሩት ብቻ ነው በጋርዮሽ ሀሳብ የሚሄዱ ስብስቦች ቦታ የሚሰጡት። ባልገባቸው ሰዎች የተሳሳታችሁ ተብለው ለመወቀስ እና እንደ ሞኝ እና ጅል ለጊዜው ለመቆጠር የፈቀዱ ናቸው የዘመናት የማሕበረሰብን ዓይነ ጥላ የሚገፉት። እኛ ግን ለማስተዋል የፈጠንን፤ ለመፍረድ እና ለመናገር የዘገየን እንሁን። ታሪክ ያስተማረን ከዛሬ ደስታ ይልቅ የጸጸት ዕድሜ ረጅም መሆኑን ነው። ቸኩሎ መፈረድ እና መተቸት ለረዥሙ ጸጸት ነው የሚዳርገን።






Comments