ውስንነትን እና ወሰን አልባነትን
- Mulualem Getachew

- 2 days ago
- 3 min read

በራሴ ላይም ሆነ በሌሎች ከምታዘበው አንዱ ነገር ድንበራችንን አለማወቅ እና ለማወቅም አለመፈለግ ነው። ዘወትር ዓለምን ለማየት የምንጥረው በፍላጎታችን መነጽር ስለሆነ፣ አዕምሮአችን በሚፈጥርልን ፊልሞች እንወሰዳለን። ከዚህም የተነሳ ምኞት ብዙ አቅማችንን ይወስደዋል።
በኛ ሕይወት ውስጥ ውስንነት አለ። የጊዜ፣ የጤና፣ የሪሶርስ፣ የስልጣን እና የእውቀት ውስንነቶች ሁልጊዜ አሉ። ወሰን አልባነትም አለ። የሰው ልጅ በማሰብ ወሰን አልባ ነው። ፈጽሞ አሁን ላይ የሌሉ ነገሮችን እና ፈጽሞ ያላያቸውን ነገሮች ያስባል። ደንበኛ ትርክት በነዛ ላይ ይፈጥራል። ሌሎችንም ያሳምናል። ከዛ በዛ ላይ ተመስርቶ ግዙፍ ሥራዎችን ይሰራል።
እነዚህን ውስንነቶችን እና ወሰን አልባነትን ያገናዘበ እና ሚዛን ያደረገ ሕይወት ምን አልባት ብዙዎች ስኬት የሚሉት ደረጃ ላይ ሊያስደርሰው ይችላል።
የመጀመሪያው የራስን ውስንነት፣ የሌሎችን ፍላጎት እና የአካባቢያችንን (ከኛ ውጪ ያለውን የተፈጥሮ) ሕግ ማወቅ እና መተዳደሪያቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከውስንነት ጋር መጣላት እና መጋጨት እምብዛም ጥቅም የለውም። ከእውነታ ጋር መከራከር አያሻም። ሁልጊዜ ያሸንፋልና። ይሄ ማለት ግን ሰው ውስንነቱን ዝም ብሎ መቀበል አለበት ማለት አይደለም።
ለምሳሌ የሰው ልጅ መብረር አልችልም ብሎ ቢቀመጥ ዛሬ ላይ በራሪ አውሮፕላኖችን ባልፈጠረ ነበር።
ለዚህ ነው ውስንነትን ከወሰን አልባነት ጋር ማጣጣም የሚያስፈልገው። ያም ምኞት እና ሀሳባችን ነው። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በፍጥነት መሄድ ምኞት ነው። ሌላ አህጉር ካሉት ጋር ፊት ለፊት አሁኑኑ ተገናኝቶ ማውራት ምኞት ነበር። ግን አካላዊ ውስንነት ነበር። ሁሉ ቦታ የምንገኝ አይደለንም። የተፈጥሮ ድንበሮች ይገድቡናል። በዚህ ገደብ ውስጥ ምኞት (ገደብ አልባው) ሲገባ በሁለቱ መኃል ያለ አስታራቂ ቁሶችን እና መላዎችን መፍጠር ተቻለ። ክንፍ ማውጣት ባንችል ክንፍ ካላቸው ተምረን ክንፍ ባለው ነገር መሄድ ጀመርን።
ሃይማኖት የተፈጥሮ ድንበርን ተሻግረን ከሌላው ዓለም ካለ ሰው ጋር የመገናኘትን ሕልም ሲያድለን፤ ስልክን፣ ፌስታይምን እና ተመሳሳይ ግኝቶችን አመጣን። ወሰን አልባ በሆነው የማሰብ አቅማችን የፈጠርናቸው ትርክቶች የውስንነታችንን ድንበር ለጠጡት። ማለትም ሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ሲላተሙ መኃከለኛው የተሻለ ዓለም ሆነ።
ለዚህ ነው ቻርልስ ዳርዊን የIQ መጠኑ ዝቅ ያለ እንደሆነ ቢያውቅም፤ አንድ ነገር ግን ግልጽ ሆነለት። ውስንነቱ እና ያን ውስንነት በወሰን አልባነት የማስፊያ መንገድ። ስለዚህ ስለአንድ ነገር እርግጠኛ እውቀት ሲኖረው፣ የሚያደርገው በፍጥነት ከርሱ በፍጹም ተቃራኒ እውቀት እና አስተሳሰብ ካለው ሰው ጋር መወያየት እና የእርሱን ንደፈ ሀሳብ (theory) ውድቅ እንዲያደርግበት መወያየት ነበር።
ብዙዎቻችን ለራሳችን ባለ ስሱ እና egoistic አመለካከት ምክንያት ከተቃራኒ እይታ ልናተርፍ የምንችለውን እጅግ ድንቅ ጥቅሞች እናጣለን። ስለዚህ የሚቃረንን ጠላት ማድረግ ወይም መሸሽ ነው ስራችን። እኛ ያከበርነውን ሃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ግለሰብ የሚያቀልብን ሁሉ ጠላታችን ነው። ለዳርዊን ግን እንደዚህ ዓይነቱ ሰዎች ነበሩ ወዳጆቹ። ምክንያቱም የሰው ልጅ የአቅም ውስንነት የሚሻሻለው በተቃራኒው ኃይል ስበት ነው። የኛን አመለካከት የሚደግፉ (ኮንፎርም ከሚያደርጉ) እምብዛም የምናገኘው ጥቅሞች የሉም፤ ስሱ ሆነን የራስ መተማመናችንን በእነዚህ ድጋፎች መገንባት ካልፈለግን በቀር።
ዳርዊን ከታች ማንነት ተነስቶ ዌስት ሚኒስቴር ፍጻሜው የሆነው ውስን ስላልሆነ ሳይሆን፤ ናፍቆቱ እውነትን ማግኘት ስለነበረ ነበር። እውነትን ለማግኘት የሚጥር ሰው ስህተቱ በቶሎ እንዲገለጥ ነው የሚሻው። የአስተሳሰብም ሆነ የእምነት ስህተቱን ለፀሐይ (ለትችት) በማጋለጥ ፈውስን ያገኛል። የፀሐይ ብርሃን ትልቁ ኢንፌክሽን ማከሚያ ነው ይባላል። (sunshine is the best disinfectant)።
ለዚህ ነው መቀየር የማትችሉትን ነገር መቀበል ሲባል፤ መቀየረ የማንችለውን ነገር አሁን ባለው ውስንነታችን ማየት እና ወሰን አልባነታችንን ተጠቅመን ግን ድንበሮችን መግፋት ያሻል ማለት ነው።
ለምሳሌ ሰው ከሞተ በኋላ ለምን ሞተ ብሎ ማማረር ደካማነት ነው። የሞተን ሰው ምንም ማድረግ አንችልም። ያ ሕይወት ቢያንስ ከኛ ጋር ባለው ሕብረት አብቅቶለታል። ያን ሞት ወደ ሕይወት ማምጣት አንችልም። ግን አንድ ነገር ግን እንችላለን። ስለ ሞቱ ምክንያት ማጥናት፣ ያ የሞት ምክንያት ሌሎቹ ላይ ወደፊት እንዳይደገም እና ሕይወትን በቶሎ እንዳይቀጭ ማድረግ እንችላለን። በዚህም ከውስንነታችን በመማር የሌሎችን ሕይወት (ወሰን) ግድቡን ከፍ እናደርጋለን። ሞትን ባናስቀር እንኳ እናዘገየዋለን። ሞትን ዝም ብለን ብንቀበል ግን የማዘግየትን ዕድል እናጣለን።
በአዕምሮአችን ውስጥ ሁለት ትግሎች አሉ። ሕይወታችን በጊዜ የተገደበ መሆኑ። ሌላኛው ዘላለማዊ የመሆን ምኞት። (ምኞት ወሰን አልባ ነው)። ስለዚህ ሰው በሞት ሲቀጭ ከምኞታችን ጋር ይላተማል። በሞት እንዳይቀጭ እና ዘላለማዊ የመሆን ፍላጎት ጋር ማለት ነው። ስለዚህ ምኞታችን ስለሞት ያጠናል፣ ያን የሰው ሕይወት ለዘላለም ቅርብ ለማድረግ ይታገላል። በዚህም ምኞታችን ዘላለማዊ ጋር መድረስ ባንችል እንኳ የዕድሜን ገደብ ከፍ እናደርጋለን። ለዚህ ምኞታችን ሃይማኖት ጥሩ ትርክት ሆኖ አገልግሎናል። የሰው ልጅ ፈጽሞ አይቶት ስለማያውቀው ግን ተችሎ ነበር ስለሚለው የዘጠኝ መቶ ዓመቱ ማቱሳላ በእምነት እንድናይ ያደርገናል። ያ እምነታችን ወሰናችንን ያሰፋዋል።
ለዚህ ነው ስለምንቃወመው ነገር መጠንቀቅ ያለብን። ብዙ ሰዎች ሃይማኖት እርባና ቢስ እና ተራ የስሜት ምቾት ሰጪ ብቻ ያደርጉታል። ሃይማኖት ግን የማይቻለው ነገር ድንበር ሰባሪ ነው። ይሄ ማለት ሃይማኖት ሁልጊዜ ጥሩ ነው እያልኩ አይደለም። ብዙ ጎታች ሃይማኖቶች አሉ። እያልኩኝ ያለውት እንደ ጄ ኬ ቼስተርተን ነው። የሆነ አጥር ካየ ያ አጥር የቆመበት ምክንያት አለው። ጥራዝ ነጠቅ አዋቂዎች አጥሩን ሲያዩ፤ ምንድነው ይሄ አጥር ፥ ኑ እናፍርሰው ይላሉ። የበሰሉ አዋቂዎች ግን “ያለፈው ማህበረሰብ ዝም ብሎ አጥር አያስቀምጥም። ከማፍረሳችን በፊት ይሄ አጥር የቆመበትን ምክንያት ሁሉ ጠንቅቀን እንወቅ። ሲገባን ብቻ፣ ስናውቅ ብቻ የዛኔ ማፍረስ ካለብንም እናፈርሳለን።” ይላሉ።
ይሄ ጹሁፍ የሚነግረን አንድ ነገር የሆነ ሃሳብ ሲመጣልን ሌላ ሀሳብ በተቃራኒው እስከምናደምጥ እና የራሳችንንም ሆነ የተቃራኒውን ሀሳብ በደንብ እስከምናውቅ ድረስ አቋም ላለመያዝ እንጠንቀቅ እያለን ነው። አቋም በቀላሉ ይያዛል። የመማር እና የማወቅ ክፍተት ግን ከተደፈነ በኋላ መክፈት ከባድ ነው። የሰው ውስንነት በቶሎ የመርካት ዝንባሌ አለው። የማይታወቅ ነገር ስለሚያስፈራን በውሸት እውቀት ፍርሃትን ማሸነፍ እንመርጣለን።






Comments