ራስን የማዳን ስሁት
- Mulualem Getachew

- Aug 3
- 3 min read

የስነልቦና ሐኪሞች እንዲህ ይላሉ “ለማዳን በጣም ከባዱ በሽተኛ ራሱን ለማዳን የሚጥርን የማዳን ጥረቱን ማስቆም ነው።” ያሉን አስገራሚ ባህሪዎች ራሳችንን ለማከም የወሰድናቸው መድኋኒቶች እንደሆኑ ቢነገረን ምን የምንል ይመስላችኋል?
ማርክ ትዌን ስለዚህ ሲናገር በድመት ነው። ብረትምጣድ ላይ ለመቀመጥ የምትፈራ ድመት ካያችሁ፤ ከዚህ በፊት የጋለ ብረትምጣድ ላይ ተቀምጣለች ማለት ነው። የጋለ ብረትምጣድ ብቻ አይደለም የምታሶግደው ሁሉንም ብረትምጣዶች እንጂ። ሁለት ሦስቴ በሰዎች የተከዳ ሰው የሚክዱ ሰዎችን ብቻ አይደለም የሚያሶግደው፤ ለደስተኛ እና ጤናማ ሕይወት መሠረት የሆነውን ሰውን ማመን ሁሉ እንጂ። በየዓመቱ ከሀገር ወደ ሀገር ከቤተሰቦቹ ጋር እየተዘዋወረ ያደገ ልጅ ፥ ዘላቂ ጓደኝነትን እና ትውስታን መመስረት ይሳነዋል። ሁሉም ነገር ጊዜያዊ ነው የሚመስለው። በጣም በችግር ያደገ ሰው ፤ በጣም ገንዘብ ቢያገኝም ሁልጊዜ ወደ ዛ ችግር የሚመለስ ስለሚመስለው የድህነት ስነልቦና ላይለቀው ይችላል።
ቅናት እና ምቀኝነት እንስሳዊ ማንነታችን ለገጠመን በሽታዎች የለገሰን መድኋኒቶች ናቸው። እንስሳዊ ባህሪያችን በዙሪያችን ያለ ሰው ሲበልጠው ይደነግጣል። በዙሪያችን ያለ ሰው ከበለጠን ወይም ከኛ ትኩረትን ከተጋራ ይፈራል። ምክንያቱም በእንስሳት ዓለም መበለጥ ዋጋ ያስከፍላል። የበለጠን ሰው የኛ የሆነውን ሁሉ ሊወስድ እና ሊያጠፋን ይችላል። ውስጣቸው ነጭ ወረቀት ነው የምንላቸው ሕጻናት በቅናት ይጠቃሉ። የሦስት ዓመት ልጅ አዲስ በተወለደው ሕጻን ልትቀና ትችላለች። አዲሱ ሕጻን የወላጆቹን ትኩረት መሳቡ እንድትጠላው ያደርጋታል። ምክንያቱም ወላጆቿን እንደቀማት አድርጋ ነው የምትቆጥረው። ከወላጆቿ ይልቅ ምንም ራሷን መከላከያ የሌላት ልጅ ይሄን እንደ ትልቅ አደጋ ነው የምትቆጥረው። ስለዚህ በአዲሱ ሕጻን ትቀናለች። ችግሩ የሕጻኗ መቅናት አይደለም፤ አድገንም ሰውነታችን ይሄን መድኋኒት ለመበለጥ እንደ መፍትሔ ሲሰጠን ተቀብለን መዋጣችን ነው። ይሄን ነው ለማዳን ትልቁ ፈተና። ራሳችንን ለማዳን የምንወስደው መድኃኒት።
በሰዎች በልጅነቱ የተጎዳ ሰው ወይም በቤቱ ውስጥ የሌሎችን ትኩረት ለማግኘት የሚቸገር ሰው፤ ሰዎችን ለማስደሰት የሚሰራ ይሆናል። ምክንያቱም በዚህ ቤት ውስጥ ሰው ሆኖ ለመቆጠር ሌሎችን ማስደሰት ነበረበት። በዚህም የራሱን ስሜት የመተው እና የማይፈልገውን ነገር እንቢ የማለት አቅም ያጣል። ብዙ ሰዎች ወደ ሱስ የሚሄዱት በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለተቀበሏቸው ነው። ሌላ ቦታ ፍቅርን ያጡ እና ቅቡልነት ወይም ትኩረቱን ያላገኙ ሰዎች ሱስ ያን ከሰጣቸው ስሜታቸውን ለማከም ይገቡበታል።
ወላጆቿ ቢዚ ከመሆናቸው የተነሳ ጊዜ የማይሰጧት ልጅ፤ በመጨረሻ ራሷን በምላጭ መቁረጥ የጀመረችበትን ታሪክ አንብቤያለሁ። ምክንያቱም በደማች ቁጥር እናቷ ወይም አባቷ ከሥራ ቤት ቀርተው አብረዋት ይሆኑ ነበር። ራስን የማዳን ተልዕኮ ይሄ ነው። ብዙ የሰዎች ባህሪያት ለስሜት ማከሚያነት የተለበሱ ናቸው።
ራሳቸውን በፍጹም ሥራ የሚወጥሩ ሰዎችን አውቃለሁ። እነዚህ የማሰቢያ ጊዜ ካገኙ ማስታወስ እና ማከም የሚፈሩት ሀሳብ ስለሚወጥራቸው ሊሆን ይችላል። ወይም አንዳች የሚያሳዳቸው ድብቅ በእነርሱ ዓለም ብቻ ያለ አውሬ አለ።
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኃን ይሄን ሽሽት “እንዳይነግርህ አንዳች እውነት!” በሚል ግጥሙ ገልጿታል፤
“ደንስ ጎበዝ፦ ደንስ ጀግና
.
.
.
ርገጥ፥ ጨፍር፥ ደንስ ጀግና!
ያን የሙዚቃህን ናዳ፥ የኮንትራባሱን መብረቅ
ልቀቀውና ይደብለቅለቅ
ምንም-ምንም እንዳታስብ፥ ሁሉሉ-ሁሉን እንድትረሳ
ደንስ! ካካታው ይነሳ
ጭንቅላትክን ግዘፍበት፥ እስኪያሰጥመው አጓራበት
ጭንቅላትክን ግዘፍበት፥ ውቀጥበት፥ ውገርበት ....
ዝግ ብሎማ ያስብ እንደሁ፥ ይነግርሃል አንዳች እውነት!”
ብዙ ሰው ለጤናማ እና በአግባቡ ለሚያስብ ሰው ግራ አጋቢ ሕይወት ውስጥ ገብቶ ታገኙታላችሁ። ማህበረሰብን ለማስደሰት ብቻ ወይም ሰው ምን ይለኛል የሚልን ለማስቀረት ብቻ ለራሱ ፍላጎት ተጻራሪ የሆነ ሕይወት ውስጥ የተዘፈቀ ይኖራል። ወይም ከሰው ጋር መቀላቀል፣ ከሌሎች ጋር አብሮ መተባበር እና የተሻለ አካባቢ መኖር ለጤናውም ሆነ ለሕይወቱ የተሻለ ሆኖ ሳለ ፥ መጋፈጥ የማይፈልጋቸው የስሜት ቁስሎች ይዘውት በብዙ ምሽግ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ። በብቸኝነት ምሽግ ውስጥ፣ ወይም በአልኮል እና እፅ ሱስ ምሽግ ውስጥ፣ በሥራ ማብዛት ምሽግ ውስጥ፣ በገንዘብ ማሳደድ ምሽግ ውስጥ፣ በቅናት እና ምቀኝነት ምሽግ ውስጥ፣ በፍርሃት እና ሁሉን ላስደስት በሚል ምሽግ ውስጥ፣ ሰውን ላለማስቀየም ባለ ምሽግ ውስጥ እና ሌሎች ውስጥ ያሉ አሉ። የማርክ ትዌን ድመት እኛ ውስጥም አለች። በጭቅጭቅ ቤት ውስጥ ያደገ ሰው አውቃለሁ። መከራከር እና ኮስተር ያለ ውይይትን እና ንግግርን ሁሉ ይሸሻል። ጠንከር ብለህ ስለ እንከኑ ልትነግረው ስትል ፥ ከመጋፈጥ ይልቅ ሮጦ ይሄዳል። ምክንያቱም እንደ ድመቷ እንደዚህ ዓይነት ንግግር የሚጭርበት የልጅነቱን ያ ከባድ የአባት እና የእናት ጭቅጭቅ እና ድብድብ ነው።
እኛ ግን እንስሶች ብቻ አይደለንም። ሌላ የምክንያታዊ ክፍልም አለን። ሞኝ የምንሆነው የእንስሳነት ክፍላችንን አሳንሰን ካየን ነው። የእንስሳው ክፍላችን እንደ ዝሆን ግዙፍ ነው። የምክንያት ክፍላችን እንደ አይጥ ድንቢጥ ናት። በኋይል አይጧ ዝሆኑን አትጎትተውም። ግን በጥበብ አይጧ ዝሆኑን ወደ ምትፈልገው ቦታ መምራት ትችላለች። ይሄ በጥበብ እና በትሪክ (trick) ብቻ ነው የሚሆነው።






Comments