top of page
Search

ሰዎች ለምን ይጣላሉ?

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 10
  • 4 min read

የሰንበት ዕይታ - 3

ree

ካርል ማርክስ እና ሼክስፒር በዚህ ጉዳይ ይለያያሉ። ካርል ማርክስ ሰዎች የሚጣሉት ስለሚለያዩ ነው ይላል። የተለያዩ ግቦች፣ ፍላጎቶች፣ አይዶሎጂ፣ የተለያየ ቁሶች ስላላቸው ነው የሚጣሉት ይላል። ሼክስፒር ግን በሮሚዮ እና ጁሊየት እና በሌሎችም ሥራዎቹ እንደገለጠው ሰዎች የሚጣሉት ስለሚመሳሰሉ ነው ይላል። እኔ ሼክስፒርን በሙሉ ስቀበል ፥ ካርል ማርክስን ደግሞ በከፊል ልክ ነው እላለው።


ብዙ ጊዜ የምንቀናው ከኛ በሀብት እና በንብረት ወይም በሆነ ነገር የሚመሳሰለንን ሰው እንጂ ከኛ በጣም በራቁ ሰዎች አንቀናም። በቢልጌት ወይም በኤለን መስክ እኛ አንቀናም። የምንቀናው ልንደርስበት በምንችለው ወይም አብሮን ከኛ ጋር በነበረ ሰው ነው። ቃዬል በአዳም አልቀናም በመንታ ወንድሙ አቤል እንጂ። ኤሳው በያዕቆብ ፥ የዮሴፍ ወንድሞች ከኛ እሱ በምን በልጦ ነው ብለው በወንድማቸው ዮሴፍ፣ አሮን እና ማርያም በወንድማቸው በሙሴ ቀኑበት ይላል። ይሄ ሁሉ የሚያሳየን ሰዎች የሚጠላሉት ስለሚመሳሰሉ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም በጣም በሚቀራረቡ ብሔሮች መካከል ነው ጥላቻ እና ግጭት ያለው። በትግራይ እና በአማራ፣ በትግራይ እና በኤርትራውያን፣ በኦሮሞ እና አማራ (በቁጥር ስለሚቀራረቡ)፣ በወላይታ እና በሲዳማ፣ በአኝዋክ እና ጉምዝ፣ በኑዌር እና ዲንካ እያለ ይቀጥላል። በዓለም ላይም ጥላቻ እና ግጭት በሚቀራረቡ መካከል እንጂ በሚራራቁ መካከል ጠብ የለም።


የሦስተኛው ክፍለዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሙሴን ለመከራ የዳረገው የሚራራቁት የዕብራውይ እና የግብጻዊ ጠብ ሳይሆን በሁለት ወንድማማቾች ዕብራውያን ጠብ ነው ለስደት የተዳረገው ይላል። ይሄንንም ሲገልጽ የሚለያዩ ነገሮች ጠብ ቀላል እና ውጪያዊ ነው ስለዚህም መገላገል ቀላል ነው ይላል። የሚመሳሰሉ ሰዎች ወይም የወንድማማቾች ጠብ ግን የመረረ ነው ፥ ለዚህም መገላገል እጅጉን ከባድ ነው። ይሄንንም ሲያጠቃልል እንዲህ በሚል ዘመን ተሻጋሪ አባባል ነው የዘጋው “ማንም ሰው ተቀናቃኙ በእርሱ ላይ የድል ኃይል እንዳለው ምልክት ካላገኘ በቀር በእርሱ ላይ ሐዘን አይሰማውም። ” ይሄ ማለት ሰው በሕጻን ልጅ ስድብ አይናደድም ፥ አቻው ወይም ወዳጁ ሲሰድበው ነው የሚናደደው። ማናችንም ተቀናቃኝ የምንላቸው አቻዎቻችንን ነው። በሞተ ሰው ወይም ከኛ በብዙ በሚያንሱ እና በብዙ በሚበልጡ ላይ ንዴት የለንም።



ካርል ማርክስ ደግሞ ያስተዋለው ሰዎች ለግጭት የሚሰጡትን ትንታኔ ነው። አዎ ማንም ሰው ግጭት ውስጥ ሲገባ “ስለቀናው ነው፣ እሱ ያለውን ስለተመኘው ነው፣ እሱን ስለተፎካከርኩት ነው፣ እሱ እንዳይደርስብኝ ነው” አይልም። ምክንያቱም ይሄ ግጭቱን ምክንያት ያሳጠዋል ፥ ተከታይ እና ደጋፊን ይነሳል። ለራሳችንም እንደዛ ብለን ማመን አንፈልግም።


የዚህ ጹሁፍ ዓላማ ምንድነው?


ብዙዎቻችን እንቀናለን ፥ የምንቀናው ደግሞ በጎረቤታችን ወይም በብዙ በሚመስለን ነው።(መጽሐፍም ባልጀራን ውደደው ያለው ፥ ባልንጀራን መውደድ ከባድ ስለሆነ ነው።)ይሄን ለማወቅ ከፈለጋችሁ ዓይናችሁን ጨፍናችሁ ስኬታቸውን ስትሰሙ ወዲያው ደስታ የማይሰማችሁ ሰዎችን አስተውሉ። ወይም በሆነ ነገር ከናንተ ሊያንሱ የሚችሉበትን ነገር ሲያገኛቸው ደስ የሚላችሁ ሰዎች እነማን ናቸው? እነዚህ ሰዎች በብዙዎቻችን ሕይወት ውስጥ አሉ። በእህት እና ወንድም ወይም በእህትማማቾች፣ በጣም በቅርብ ጓደኞች መካከል ነው ባብዛኛው የሚኖረው። ይሄ ስሜት ሲመጣብን ፈጥነን ለማውገዝ አንቸኩል። ይሄ ስሜት ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው። ረጋ ብለን ለምን እንደዛ እንደተሰማን እንጠይቅ፣ እኛ ከቁስ እና ከውድድር በላይ የራሳችን ውበት እንዳለን እናስተውል። ሕይወት ለእያንዳንዳችን የተለየች ናት። ስለዚህ ከዚህ ዓለምም የምናገኘው ነገር እንደዛው የተለያየ ነው። የሌላው ስኬት ሁልጊዜ ለኛ ሊጠቅም ስለሚችልበት ነገር እናስብ። እንድንፎካከራቸው ከሚጋብዙን ሰዎች በብዙ ኬሎሜትር እንራቅ። እንደዛ ስሜት ከሚሰማን ሰዎች ወይም እንዲሰማን ከሚያደርጉን ለጊዜው እንሽሽ ፥ የራሳችን ሕይወት ላይ እናተኩር። ከዛ በተረፈ ግን የምንቀናባቸው ሰዎችን ከኛ መነጠል የማንችል ከሆነ ፥ በተቻለ መጠን በጎ ነገራቸው ላይ ለማተኮር እና ሆን ብለን ለመርዳት እንሞክር። በእነሱ ፊት ላለማስመሰል እንጣር።


የምንቀናባቸው ነገር የምናደንቅላቸው ነገር ስለሆነ እኛ ያ ነገር ቢኖረን እንደምንመኝ እና በዛ ነገራቸው እንደምንቀናባቸው እንንገራቸው። ያ የሚያሳፍር ቢመስለን እንኳ በውስጣችን ያለውን መጥፎ የፉክክር ስሜት ግን ይገለዋል። ስለዚህ ራሳችንን እናድናለን።


በተጨማሪም ቅናት ምን ያህል ፍትሐዊ ስሜት እንዳልሆነ እንገምግመው። ምክንያቱም የምንቀናበትን ሰው ሁሉ ነገሩን አንፈልግም። ያ የምንቀናበትን ጥቂት በጎ ነገር እንጂ። ለምሳሌ የስቲቪ ጆብ (የአፕል ስልክ መስራች) ጓደኛ ሆነን በሱ እንቀናለን እንበል። የምንቀናው በሱ ስኬት ብቻ እንጂ፤ ፈጣሪ ስቲቪ ጆብን ላድርጋችሁ ቢለን ማናችንም እንቢ ነው የምንለው ምክንያቱም ከ40ዎቹ ዕድሜው ጀምሮ በካንሰር በሽታ የተሰቃየውን በ56 ዓመቱ የሞተውን ስቲቪ ጆብን ማናችንም መሆን አንፈልግም፤ የፈለግነው ያ ስኬቱን ብቻ ነው። ሕይወት ግን እንደዚያ አየሰራም። ልጅን ወዶ ንፍጡን ተጠይፈን አይሆንም እንደሚባለው፤ ቅናት እንደዛ ነው። ልጁን ያለንፍጡ መፈለግ። ለዚህ ነው ፍትሐዊ ስሜት እንዳልሆነ እና እኛ የምንቀናበት ሰው የሌለው ውበት በኛ ሕይወት ውስጥ እንዳለ ማየት ያለብን። ይሄ ማለት ግን የኛ ሕይወት ከዛ ሰው የበለጠ ነው ማለት አይደለም። የተለየ እና የራሱ ውበት ያለው ነው ለማለት ነው። ቅናት ግን ይሄን ውበት ያጨልመዋል። ለምሳሌ ሙዚቀኛው ሙሉቀን መለሰ በጥላሁን ገሰሰ ይቀናበታል ይባላል። ያ እውነት ነው እንበል። ሙሉቀን ግን የጥላሁን ገሰሰን ሕይወት ይሰጥኽ ቢባል ፍቃደኛ አይሆንም ምክንያቱም የጥላሁን ሕይወት አንገት መታረድ፣ እግር መቆረጥ፣ በጊዜ መሞትም አለበትና። ለዚህ ነው ቅናት የህሊና ፍትህ መታወር ውጤት የሆነው።



ሌላው የዚህ ጹሁፍ ዓላማ ፥ ወደ ግጭት ስንገባ እንደግለሰብም ሆነ እንደተቋም እና ሀገር ራሳችንን መጠየቅ ያለብን “የሄ ግጭት ከመመሳሰል ከመጣ ቅናት ወይስ ስትራቴጂክ ፍላጎቴን የሚጠቅም ግጭት ነው?” ብለን ነው። ድፍረት አይሆንብኝ እና ከ90% በላይ የሚሆኑት ግጭቶች የቅናት ውጤቶች ናቸው። በዚህም ከመመሳሰል የመጣ፤ የረጅም ዘመን (long-term) ጥቅማችንን ያላማከለ፣ ስሜት የሚነዳው እና በመጨረሻም ሁሉንም ለከፋ ውጤት የሚዳርግ ነው። ምክንያቱም ቅናት ሌላው የሚያጣ ከሆነ በራሱ ማጣት ሀዘን አይሰማውም። ቅናት ሌላው ሁለት ዓይኑን የሚያጣ ከመሰለው የራሱን አንድ ዓይን አሳልፎ ለመስጠት የሚፈቅድ ነው። ቅናት እንደጥንብ አንሳ የሌሎች መቀርናት የሚስበው ፥ መልካም ጠረናቸው የሚገለው ነው። በሚገርም ሁኔታ እንደ ኮሚኒዝም ያሉ የፖለቲካ ፍልስፍናዎች ሳይቀር በቅናት ሞተርነት የተንቀሳቀሱ ድሃውን ከበርቴ ማድረግ ሳይሆን ከበርቴውን ድሃ በማድረግ የተጠናቀቁ ነበሩ። ጥቂቶች በእነዚህ ሥርዓቶች የተደሰቱት ሃብታም ስለሆኑ ሳይሆን ሌሎችን ከእነሱ እኩል ድሃ ስላደረገላቸው ነበር። የሚያስቡ ሰዎች፣ የራሳቸውን ረጅም ጊዜ ጥቅም በጥልቀት ለመመርመር የሚችሉ እና ስሜታቸውን ለመፈተሽ የሚፈቅዱ ግለሰቦችም ሆነ ልሂቃን ግጭቶች በቅናት እንዳይመሩ ወይም እንዳይቀሰቀሱ ለራሳቸው ስሜት መጠበቂያ ያደርጋሉ። ወደ ግጭት ከመግባታቸው በፊት የዛ ሰው፣ ተቋም ወይም ሀገር ስኬት ለእነሱ ምን ማለት እንደሆነ፣ ያ እንዴት ለእነሱ ጥቅም እንደሚውል ያስባሉ። ውድቀቱ የሚያስደስታቸው ከሆነ ያ ግጭት ከቅናት የተነሳ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ተገቢ ነው።ምክንያቱም ከመመሳሰል የሚነሱ ግጭቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አጥፊዎች (distractive) ናቸውና።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page