ቅርብም ሩቅም ለውሳኔ መጥፎ ነው።


በሀገራችን “ሰማይ ላይ ያለ ሰው” ይባላል። አንድ ሰው ከሩቅ ሆኖ ችግር ውስጥ ላለ ሰው አስተያየት ወይም ሀሳብ ሲሰጥ። ምክንያቱም የዚያን ሰው ቁስል፣ ያለበትን መከራ ወይም ሁኔታ እርሱ በሚሰማው መጠን አያውቅም። ከቁስሉ እና ከመከራው ሩቅ ነው። ለዚህ ሰው አስተያየት መስጠት በጣም ቀላል ነው። መተቸት በጣም ቀላል ነው። ግን ከእውነታው ሩቅ ነው። አስተያየቱ መሬት ላይ ያሉትን ሰዎች ያላገናዘበ ነው። መሬት ላይ ሊተገበርም የማይችል ነው።
በተመሳሳይም አንድ ሰው በሀዘን እና መከራ ውስጥ እያለም የሚወስነው ውሳኔ ጤናማ ነው ብለን አንቀበለውም። ሰውም በዚህ ዓይነት ጥልቅ ሀዘን ወይም ሕመም ውስጥ ሆኖ ከውሳኔ ቢርቅ ይመከራል። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ነገር አትሥራ ብለን በዚህ መከራ ወይም ቁስል ውስጥ ያለን ሰው እንገስጻለን። ቁስልህ ያልፋል ውሳኔህ ግን ይቀራል ብለን ከውሳኔ ለጊዜው እንዲርቅ እንነግረዋለን።
ስለዚህ ሰዎች ቁስላቸው ወይም ከመከራቸው በጣም ርቀው ወይም በጣም ለዛ መከራ ቅርብ ሆነው የሚሰጡት አስተያየት ወይም የሚያስተላልፉት ውሳኔ ብዙ ጊዜ ልክ ያልሆነ ነው። ከመከራው በጣም የራቀ ሰው የሚሰጠው ከአስተምሮ ወይም ከንድፈ ሀሳብ አንጻር ጥቅም ይኖረው ይሆናል እንጂ ከእውነታ ጋር እምብዛም የተገናኘ አይሆንም።
በተመሳሳይ በቁስል ውስጥ ያለም ሰው የሚሰጠው ውሳኔ የመረረ እና የተጋነነ፣ ሩቅ የሚያይ አይሆንም። ያሉትን በጎ ነገሮች ሁሉ ያላገናዘበ ነው የሚሆነው።
ለዚህም ይመስላል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግስተ ሰማያትን የስንዴ እርሻ አድርጎ መስሎ የነገረን። ማቴዎስ 13፥24። መልካሙን የስንዴ ዘር የእርሻው ጌታ ባሮች በዘሩበት ዕለት ማታ ደግሞ ጠላት እንክርዳዱን በዛ ማሳ ውስጥ መቶ በተነው። ዘሪዎቹ ለእርሻው ባለቤት ሄደው እንክርዳዱን እንድናጭድ ትወዳለህንህ አሉት? የእርሻው ጌታ ግን ተው፤ አብረው ይደጉ። በዚህ ነው ስንዴው ሳይጎዳ እንክርዳዱን ማጨድ የምንችለው አላቸው።
ጠላት የእነዚህን የእርሻውን ጌታ አገልጋዮች ባህሪ ስላወቀ ነበር እንክርዳዱን የዘራው። ደክመው ዘርተው በዛ ድካማቸው ላይ ያንን እንክርዳድ ሲያዩ እንደሚናደዱ እና ተናደውም እርምጃ እንደሚወስዱ ስለሚያውቅ ነው ያንን ያደረገው። እንጂ እንክርዳዱን እና ስንዴውን መለየት አይችሉም ብሎ አይደለም። ዘሪዎቹ ምን እንደዘሩ ያውቃሉ። ግን ዘራቸው ሲበላሽ ግን ቁስሉ ለእነርሱ በጣም ቅርብ ነው። ድካማቸውን ያውቃሉናል። የእርሻው ጌታ ግን ስለ ስንዴው ነው የሚያስበው። ስለ ባሮቹ ድካም አይደለም። ለድካማቸው ተገቢውን ክፍያ ይሰጣቸዋል። ለእርሱ ግን ትልቁን ስዕል ማየት ይቻለዋል። የእርሻው ባለቤት ነውና። የጠላትንም ስልት ይረዳዋል። ይሄ ከጠላት ሲመጣበት የመጀመሪያው አይደለም እና። የዚህ እርሻ ባለቤት ሆኖ በጣም ብዙ መኸሮችን አሳልፏል። ብዙ ስንዴዎችን አሳጭዶ እና እንክርዳዶችንም አሶግዶ ያውቃል። ስለዚህ እርሱ የባሮቹን ድካም የጠላትንም ክፋት፣ የስንዴውንም ፍጻሜ የእንክርዳዱንም መጨረሻ ከሁሉም በተሻለ ያውቀዋል። በዚህም ከሁሉም የተሻለ ውሳኔ ይሰጣል። እንደ ባሮቹ ከድካሙ (ከቁስሉ ተነስቶ) ውሳኔ አይሰጥም። ስላልተጎዳ ሳይሆን ከሁሉም በተሻለ ፍጻሜውን ማየት ስለሚችል እንጂ። ከሩቅም እንዳለ እንደ ባሮቹም ካልደከመ እና እንደ ጌታውም እርሻው የራሱ እንዳልሆነ ሰው ውሳኔ አይሰጠም። ባሮቹን የቀጠረ፣ ለድካማቸው ዋጋን የሚሰጥ፣ እርሻውም በጠላት የተደፈረበት፣ ስንዴዎቹም ውሃን ከእንክርዳዶቹ ጋር ተሻምተው እንዲጠጡ ጠላት በማድረግ የስንዴውን ውበት ያቀጨጨበት፣ በመጨረሻም ይሄ ጥቃት በእርሱ ላይ ነው በዋናነት። ስለዚህ ከሩቅ እንዳለ ታዛቢም ሆኖ አይደለም ውሳኔ የሚሰጠው።
ይሄ የስንዴ እርሻ ታሪክ እኛም በሕይወት ውስጥ ውሳኔ ለመስጠት ይጠቅመናል። ከማን ነው ምክር መስማት የሚገባው በሚለው ላይ በተለይ። ብዙ ጊዜ እኛ ከሩቅ ሆነን፣ እሳት ውስጥ ምናችንም ሳይቃጠል ወይም የምናጣው ምንም ነገር በሌለበት ጉዳይ ላይ በልበ ሙሉነት ሀሳብ እንሰጣለን።
ያንተ ቆዳ በሌለበት ጦርነት (skin in the game) ውስጥ በዜና እና በንባብ (intellectually) ያገኘኸው ነገር ያን ጦርነት ወይም ሀገር ያሳወቀኸ ከመሰለህ ከትዕቢት ውጪ ያተረፍከው ምንም የለም። አንድን ነገር በእውቀት ማወቅ እና በዛ ውስጥ ራስኽ ማለፍ ምን ያህል ልዩነት እንዳለው ለማወቅ መከራ የገጠማቸውን ሰዎች ለማጽናናት ያነጎድከው ዲስኩር በአንተ መከራ ወቅት ከሸንበቆ የቀጠነ ደካማ ምርኩዝ እንደነበረ ማስታወስ ብቻ ይበቃኸል። ያ ዲስኩር ሊያጽናናኽ ይቅርና ተመሳሳይ ነገር ሊነግሩኽ እና ሊያጽናኑ የሚፈልጉትን እንኳ እንዴት እንደምትጠየፋቸው ታውቃለኸ። ቲኤስ ኤሊኦት እንዳለው “ስለሌሎች ለማወቅ መባዘናችንን ማቆም የለብንም። ነገር ግን የዚህ የማወቅ አሰሳ መጨረሻው መነሻችን ጋር መድረስ መሆን አለበት። የአሰሳው ፍጻሜ መነሻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ አጥርተን ለማወቅ ነው።”
በተመሳሳይ ሰዎች በጣም ቅርብ ለሆኑለት ነገርም ሩቅ የሆነው ሰው ልክ ንድፈ ሀሳባዊ እንደሚሆነው፤ ቅርብ የሆኑት ደግሞ ስሜታዊ ይሆናሉ። ስሜት የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ነው የሚያሳያቸው። ለምሳሌ አንድ መንገር የሚጠቅሳት እናት አለች። ልጇ ጦርነት ሄዶ እንደሞተ የሰፈር ሰው ሁሉ ያውቃል። ምንም እንኳን ሬሳው ተገኝቶ ልጅሽ ሞቷል ተብሎ ባይነገራትም። ይቺ እናት ግን ሁልጊዜ ልጄ ይመጣል ብላ ትጠብቃለች። ለልጇ ያላት ፍቅር ብዙዎች ያዩት እውነትን ጋርዶባታል።
ብዙ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ክፉ ነገር የሚነግራቸውን ሰው እንደ ክፉ ነው የሚቆጥሩት። እውነት ነው ወይስ ውሸት ብሎ ከማጣራት ይልቅ። ለልጃቸው ያላቸው ፍቅር ፥ ከዛ ፍቅር ተቃራኒ የሆነን ነገር ሁሉ እንዲያገሉ ያደርጋቸዋል። በሕመም ውስጥ ያለ ሰውም ከዚህ በፊት የነበረው ደስታ እና ወደፊት ሊኖረው የሚችለው ተስፋ አይታየውም። ትልቁ የዛ ሰው ሀሳብ ሕመሙ እና ከዛ ሕመም በምንም ሁኔታ መውጣት ነው።
ለዚህ ነው አንድን ነገር በትክክል የማናይባቸው ወቅቶች ያሉት። በጣም ስንቀርብ እና በጣም ስንርቅ። ለምሳሌ አንድን ጹሁፍ በጣም ወደ ዓይናችሁ አቅርባችሁ ለማንበብ ሞክሩ። ማንበብ አትችሉም። በተቃራኒው በወረቀት የተጻፈን ጹሁፍ በመቶ ማይል ላይ አስቀምጡት፤ ካልቀረባችሁ በቀር በትክክል ማንበብ አትችሉም።
በውሳኔ አሰጣጥ ጉዳይም ይሄ እውነት ነው። በሕይወት ውስጥ በጣም ቅርብ ወይም በጣም ሩቅ በሆንባቸው ጉዳዮች ያሉን እይታዎች የተዛቡ ናቸው። እኛ ሀሳብ መስጠት ይቻለን ይሆናል። ግን ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ የሚፈልግ ማንም የኛ ሀሳብ ላይ መመስረት የለበትም። ርቀታችን ወይም ቅርበታችን እይታችንን አንሸዋሮታል።



Comments