top of page
Search

ብቻህን አይደለህም!

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • 11 minutes ago
  • 4 min read

በዚህ ሥራ ላይ የመሰማራት ስቃይ ከሀገሬ ርቄ የሀገሬን ችግር በቅርብ በየቀኑ ማስተዋሌ ነው። ብዙ ኢትዮጵያኖች ወደ ሀገራቸው ተመለሱ ከሚባሉ መሞትን ይመርጣሉ። በተቃራኒው ከሌሎች ሀገሮች የመጡ ስደተኞች የአሳይለም ኬዛችሁ ተቀባይነት አላገኘም ሲባሉ፤ እየሳቁ ነው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱት። ያነሰ ምቾት እና ተስፋ እንደሚጠብቃቸው ቢያቁ እንኳ ሀገር ግን እንዳላቸው ያውቃሉ። ሊኖሩበት እና ጠንክረው ደግሞ ከሰሩ ሊለወጡበት የሚችሉበት ሀገር እንዳላቸው ያውቃሉ። የኛ ግን ይለያል። ከሀገር የወጣን ሰዎች መጀመሪያ የምናደርገው ልክ እንደ ስፓን የጦር ጄኔራል ኸርናን ኮርቴዝ መርከባችን ኢትዮጵያን ማቃጠል ነው። እስቲ ስንት የዩትዩብ እና የሶሻል ሚዲያ አካውንት አለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልጆች የምዕራባውያንን እውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና የታላቅነት ምስጢር ሊያስቀስም የሚችል መልዕክት የሚያስጨብጡ?


ይልቁንስ ጦርነት የሚያፋፍሙ፣ ነፍጥ አንስተው የደሃ ልጅ የደሃ ልጅን እንዲገድል የሚያደርግ እና አንዱ ዘር አንዱን ዘር ለጠብ የሚያነሳሳ የይቱዩብ ቻናል ነው እንደ እንጉዳይ የበዛው። ዲያስፖራው የሚሰባሰበው እና ገንዘብ የሚያዋጣው፣ መቀነቱን የሚፈታው መመለሻ ሀገር እንዲኖረው የሚያስችል ቴክኖሎጂዎችን እና አውታሮችን ለመገንባት ሳይሆን ፥ መመለሻ ሀገር እንዳይኖረው የሚያስችል ጦርነቶችን ፈንድ ለማድረግ ነው።



ኢትዮጵያውያን ባለንበት ሀገር ገነባን ቢባል ራሱ ቢበዛ የምንገነባው የሃይማኖት ተቋማት (ቤተክርስቲያን) እና ሬስቶራንት ነው። ከ10 ሺ የማይበልጥ ምዕመን ባለበት ከተማ ሰባት እና ስምንት ቤተክርስቲያ ታገኛላችሁ። ይሄ እንዴት አያሳፍረንም?! እነዚህን የቤተክርስቲያን ሕንጻዎች ራሱ ከሰኞ እስከ ዓርብ ወላጆች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲሰሩ እና ገንዘብ እንዲያከማቹ የልጆቻቸው መዋያ ወደ ማድረግ እንኳ መቀየር አልተቻለም። ባሉት የአንድ እምነት ቤተእምነቶች መካከል ያለው የዘር ልዩነት እና የመገፋፋት መጠን ፥ የትኛው አምላክ በዚህ እንደሚከብርበት ግር ይላል።



ምንድ ነው ግን የነካን?



ለእኔ ሁልጊዜ መልሱ “ሥር የሰደደ መኃይምነት እና ድንቁርና ነው።” ከዚህ በፊት በሰንበት ዕይታዬ አተኩሬ እንደጻፍኩት የአይሁድ ማህበረሰብ ያለውን ሕብረት ተመልከቱ። አሜሪካ ውስጥ ካጠቃላይ ማህበረሰቡ 2.4 ፐርሰንት ብቻ ናቸው። ከዚህ ውስጥ ሊብራል አሉ። ቀኝ ዘመም አሉ። እስራኤልን አስመልክቶ ግን አንዳቸውም ወለም ዘለም የለም። ይሄ 2.4 ፐርሰንት የሚሆን አስደናቂ ሕዝብ ነው የአሜሪካንን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ የሚዘውረው። ልጆቻቸውን በማስተማር ወደር የላቸውም። ሲያስተምሩ ደግሞ ለጋራ ነው። ብቻ የሚባል ነገር የላቸውም። በሁሉም መስክ የበላይነትን ለመያዝ ይሰራሉ። የጉግል ባለቤት አይሁዳዊ ነው። የቻት ጂፒቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አይሁዳዊ ነው። የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባለቤት ዙከበርግ አይሁዳዊ ነው። ዋል ስትሪት ላይ እነሱ ናቸው። የኢንተርቴመንት ማዕከሉን ይዘውታል። ይሄ ግን እንደ ማህበረሰብ ስለሰሩ እና ዓለም አይሁዳዊያን ላይ ምን ያህል ጨካኝ እንደነበረ ስላዩት ነው። ስለዚህ ከአይሁድ ውጪ ለአይሁድ ሌላ ማንም እንደ ሌለ ገባቸው። ደካማ ሆነው በታዩ ወቅት አጥንታቸውን ለመፍጨት የሚጨክን ዓለም እንዳለ እና ያንንም ስለ ፍትሕ ብሎ ለማስቆም የፈቀደ ታላቅ ሀገር እንደ ሌለ ስለተመለከቱ ነው።



መጽሐፉ ቅዱስ ላይ ከአብርሃም እስከ ኤልያስ፤ ከኢዮብ እስከ ጳውሎስ አንድ ንግግር ተናግረው ነበር። “ብቻዬን ነኝ። ብቻዬን ቀረው።” የሚል። የእስራኤል አምላክ መልስ ግን ሁልጊዜ አንድ ነበር። “ብቻህን አይደለህም” የሚል ተግሳጽ ነበር ለእነዚህ ቅዱሳን የሚደርሳቸው ድምጽ። ብቻ ተኮኖ የሚሰራ ምንም ዓይነት ጽድቅ የለም። የምስጋና ጥማት ይዞት የፈጠረን አምላክ የለም። ፍቅሩን የማጋራት ፍላጎት ነው ፍጥረትን ሕያው ያደረገው።



ኢትዮጵያኖች ትልቁ መኃይምነታችን እዚህ ጋር ነው። ብቻ የመድመቅ ፍላጎት። ተልይቶ የመጥገብ እና የማብለጭለጭ ዝቅተኛ አስተሳሰብ አለን። ባህላችን ምቀኝነት መገለጫው እስኪሆን ድረስ። ይሄን መኃይምነት የምለው ማናችንም ቢሆን በመጨረሻ ጠንካራ እና በኢኮኖሚ ያደገ ማህበረሰብ ከሌለን በቀር ብዙ ርቀት መሄድ እንደማንችል ስለምንዘነጋ ነው። ብቻችን ፈጥነን ለጊዜው መሄድ እንችል ይሆናል። ሩቅ ግን አንሄድም። ቤተሰባችን ውስጥ ያሉ ታናናሾቻችንን ለመርዳት የማንፈጥን ካልሆነ፣ ማህበረሰባችን ውስጥ ሩቅ አስበን፣ ስትራቴጂክ ሆነን ወጣቶች ላይ መስራት ካልቻልን ነገ አደጋ ቢደርስብን ጠንካራ ሆኖ ሊቆምልን የሚችል ማህበረሰብ አይኖረንም።



ፖለቲካውን ይሄው ለባለፈው አርባ እና ሃምሳ ዓመት ሞከርነው። ቢያንስ ለምድነው በረጅም ጊዜ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስትራቴጂዎችን ማሰብ የማንችለው? በታላላቅ የምዕራባውያን ተቋማት ውስጥ ያለንስ ሰዎች ገፈን መጣል የምንችለው ማንነት ያለን ይመስል ያልሆነውን ለመሆን ከምንጥር ፥ ቢያንስ እኛ ከደረስንበት በላይ የነገው ትውልድ እንዲደርስ ጥቂት ግን ዘላቂ ነገሮች ላይ አተኩረን ለምን አንሰራም? በሞታችን አልጋ ላይ ሆነን ፥ በዚህ ዓለም ላይ ብቻችን እና ራሳችንን ብቻ አበልጽገን እና አዋቂ አድርገን ማለፋችን አይቆጨንም?


እንዴት ሁላችንም መፍትሔ የሌለው የዘር ፖለቲካ ውስጥ ራሳችንን ሁልጊዜ ነክረን እንሞታለን? የነበረንን አንድ ሕይወት፣ አንድ ሰማንያ እና ሰባ ዓመት አሁን ስልጣን የያዘው ትግሬ ነው፣ አማራ ነው፣ ኦሮሞ ነው ብለን ስንነታራክ ብቻ ጨርሰነው ስንሄድ እንዴት አያሳፍረንም? ወይም ቤተመቅደስ ብቻ በየቦታው እየገዛን ፥ ለትውልድ ግን ችግርን እና መከፋፈልን አስረክበን ስናልፍ እንዴት አያሳፍረንም?



አንዳንድ ጅሎች ደግሞ አሉ። ይሄን ጹሁፍ ሲያነቡ እኔ ምን ላድረግ፣ የኔ አቅም ደካማ ነው፣ ስልጣን የለኝ ወይም ፖሊሲ ላይ ያሉ ሰዎች ይሄን ካለወጡ እኔ ምንም አቅም የለኝም የሚሉ። እንደዚህ ዓይነት ጅሎች በሕይወት ይገጥሙናል። መስራት የማይወዱ። ስልጣን ሲይዙ ብቻ መስራት የሚችሉ የሚመስላቸው። ወይም ሁሉን የመቀየር ስልጣን ካልተሰጣቸው በቀር የእነሱ ኃላፊነት የማይታያቸው። ልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ሺ ዲናር ተሰጥቶ ፥ የተሰጠው አንድ ሺ ብቻ መሆኑ ላይ አተኩሮ ጌታው እንደ መጣበት ሰነፍ ያሉ።



ማዕበሉ ብዙ አሣዎችን እየገፈተረ ወደ አሸዋው ያወጣቸዋል። በዚህ ሰዓት በዚህ ዓለም ላይ ብቻውን እንዳልሆነ የገባው አንድ መልካም ሰው የሚችለውን አሣዎች እያነሳ ወደ ባህሩ ይመልሳቸዋል። ማዕበሉ ባያቋርጥም የእርሱ ድርሻ ግን የሚችለውን ማድረግ እንጂ የማይችለውን ማዕበል ማስቆም እንዳልሆነ ስለገባው አሣዎችን ወደ ባህሩ መመለሱን ቀጠለ። በዚህ ሰዓት ሁልጊዜ ብቻውን እንደሆነ የሚታየው አንድ ሰነፍ ተከሰተ። እየገላመጠው ፥ “ምን ሆነሃል?” አለው። “ምን ሆኛለው?” አለው። “ይሄ ሁሉ አሣ በማዕበሉ ተገፍትሮ እየወጣ ያንተ ሁለት አሣዎች እያነሱ ወደ ባህሩ መመለስ ምን ሊፈይድ ነው?” አለው! ቂልነቱ እያሳዘነው ፥ ወደ እጆቹ ወዳሉት አሣዎች እያመለከተው ፥ “የማደርገው ነገር ለእነዚህ አሣዎች ይረባል” አለው።



የችግሮችን ማዕበሎች እያሳዩን በእጃችን ያሉትን ፥ እርዳታችንን ልንሰጣቸው የምንችላቸው ሰዎችን ሳይቀር እንድንተዋቸው የሚነግሩን ሰነፎች አሉ። እነዚህ ሰነፎች ሁልጊዜም አሉ። በኛ ማህበረሰብ ደግሞ በብዛት አሉ። ከእነዚህ ጋር ያለን ትግል ጥቅም የለውም። በመካከላችን የተማርን እና የነቃን ካለን ፥ ቤተሰቦቻችን ውስጥ የእህት ልጅ፣ የአክስት ልጅ፣ የአጎት ልጆች ካሉ ፥ እነርሱን መርዳት፣ ከቲክቶክ እና ኢንስታግራም ይልቅ መጽሐፍት ላይ እንዲያተኩሩ፣ የተሻለ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ካደረግን ቢያንስ በእጃችን ላይ ያሉ ነፍሳትን አድነናል። በዚህ ቤተሰብ ስኬት ብዙ ሌሎች ነገ ይነቃቃሉ። አካባቢያችን የኢትዮጵያኖች ቢዝነሶች ካሉ እነርሱን እናበረታታ። ነገ ልጆቻችን የሚያዩት እና የሚነሳሱት በኢትዮጵያዊ ስኬት ነው። ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት እና ከፍ ለማድረግ እንጣር። ጦርነትን፣ መለያየትን ለሚያበረታቱ የገንዘብ መቀነታችን አይፈታ። የእምነት ተቋሞቻችን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ማስፋፋት ላይ ሲያተኩሩ እንቢ እንበል። ይልቁንስ ትምህርት ቤት እንዲሰሩ ወይም እንዲገዙ እናስገድዳቸው። እኔ በበኩል በዚህ ጉዳይ ፍጹም አቋም አለኝ። ይሄ ባህል መቆም አለበት። ለምንድነው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያኖች ልክ እንደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት እና የነገው ትውልድ የሚፈጠሩበት ተቋሞች ላይ ማትሰራው? ኢትዮጵያዊ ተሰባሰበ ማለት ቤተክርስቲያን መግዛት እና መስራት ላይ ብቻ ለምን ያተኩራል? ይሄን ለባለፉት አርባ እና ሃምሳ ዓመታት አደረግን። ስደትን አላቆመ። ረሃብን አላቆመ። ከመንፈሳዊነት አንጻር ራሱ መከፋፈልን አላቆመ ወይም አንድነትን አልፈጠረ። ምክንያቱም መኃይምነትን የሚቀንሱ ተቋሞች ላይ ስለማንሰራ ነው። እንደዚህ ዓይነት ሃሳብ ለማንሳት ደግሞ ብቻችን ነን ብለን እናስባለን።

 
 
 

コメント


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page