top of page
Search

መከራ የሕይወት ጣዕም

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • 12 minutes ago
  • 2 min read

በአሜሪካ ውስጥ የሚወለዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ራሳቸውን ማጥፋት አሁን አሁን የተለመደ ወሬ እየሆነ መጥቷል። ይሄ ለምን እየሆነ እንዳለ ጥናት የሚፈልግ ነገር ነው። ብድግ ብዬ ተነስቼ የዚህን ምክንያት መናገር አልፈልግም። ሰዎች ውስብስብ ፍጥረት ነን። ለመኖርም ሆነ ለመሞት የሚያነሳሳንም እንደዛው ዘርፈ ብዙ ነገሮች ናቸው። ግን ራስን ስለመግደል የሚሰሩ ጥናቶች ከሚያሳዩት አንዱ ራስን መግደል ባደጉ ሀገራት የበለጠ እንደሆነ ነው።



የዛሬ ዓመት ገደማ ሉዊዚያና የሚባል ስቴት ፍርዴ ቤት አንድ የአሳይለም ኬዝ ነበረን። አሳይለም ጠያቂዋ ኢትዮጵያዊት በድንበር የገባች እና በድንበር ከገባችበት ቀን ጀምሮ ለብዙ ወራት የታሰረች ነበረች። እኔ እና በኛ የጥብቅና ኦፊስ የምትሰራ የዚህ ሀገር ሰው የሆነች ጠበቃ ነበር የወከልናት። የታሰረችው ሉዊዚያና ሆኖእና፣ ዳኛው ግን አሳይለሟን አልፈቀደውም። ለዚህ ሁሉ ፕሮሰስ ከፍተኛ ገንዘብ ነበር ያወጣችው። ምንአልባት በሕይወቷ ያጠራቀመችውን ጥሪት ሁሉ ሊሆን ይችላል እዚህ ላይ ያዋለችው። ፍርዱ ሲሰጥ በለቅሶ ስላስቸገረች፣ ዳኛው በፖሊሶች ተይዛ እንድትወጣ ሁሉ አድርጎ ነበር።



ሁላችንም በእርሷ ሁኔታ በጣም አዝነን ነበር። በተለይ ባልደረባዬ ራሷን ታጠፋ ይሆን ብላ ጠየቀችኝ? ሁኔታዋ ስላስፈራት። በእንደዚህ ዓይነት መከራ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች መከራ ውስጥ ገብተው ከማያውቁ ሰዎች በላይ የመኖር እና ሕይወትን የመቀጠል አቅም አላቸው። የሚደንቀው ደንበኛችን በነጋታው በጣም ተጽናንታ ነበር ያናገረችን። ቀጣይ ሂደቾችን ከተነጋገርን በኋላ፣ ማንኛውንም ውጤት ለመቀበል እና ሕይወትን እንደገና በሌላ ቦታ ለመግፋት እንዳሰበች ነገረችን።



ይሄ ታሪክም ሆነ ሌሎች ክስተቶች አብዝቶ የሚጠቁመኝ ነገር የሰው ልጅን ከመከራ ይልቅ ምቾት እንደሚገለው ነው። የሰው ልጅ መከራ አይደለም የሚገለው። መከራን የመሸከም ውስጣዊ ጥንካሬ ማጣት ነው የሚያደቀው።



በአሜሪካ በምዞርበት ሁሉ የማየው፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጆችን ገና በልጅነት ለኃላፊነት አያዘጋጅም። ለደረሰበት ስኬት በመከራ ውስጥ ማለፉ ያለውን አስተዋጽኦ ፈጽሞ ዘንግቶ፣ ልጆችን ከሕይወት መከራ ለጊዜው በመከለል ፥ ሲያድጉ ሊኖራቸው የሚገባውን የውስጣዊ ጥንካሬ ያሳጣቸዋል። በጓደኞቻቸው ቡሊ መደረግ፣ ትንንሽ ውድቀቶች የሚሰብራሯቸው ይሆናሉ።



ብዙዎቻችን ያደግንበት መንገድ ፍጹም ላይሆን ይችላል። ግን አሁን ላለንበት ደረጃ እንዳደረሰን አንክድም። መጥፎ ደረጃ ላይ ካለን አስተዳደጋችን ለዛ ግብአት አለው። ጥሩ ባታ ላይ ካለንንም ደረጃው ቢለያይም ያደግንበት ሂደት ለዚህ ግብአት አለው። ስለዚህ በእኛ ላይ የተሞከረው አንዱ ጠንካራ የአስተዳደግ ሥርዓት እና ለውጥ ያመጣው በልጅነታችን ለብዙ ኃላፊነቶች መጋለጣችን ነበር። ዛሬ በአሜሪካ አስራዎቹ ውስጥ የምታገኟቸው ልጆች እጅግ ለስላሶች፣ ከቤት ውጪ መኖር የማይችሉ፣ ስሱዎች፣ ቶሎ የሚከፋቸው፣ ኃላፊነቶችን አምናችሁ የማሰጧቸው ናቸው። ይሄን ደግሞ በእነሱ ላይ ማሳበብ አይቻልም። ልጆች እንዳሳደግናቸው ናቸው።



በሉቃስ ወንጌል ላይ የምናገኘውን የጠፋውን ልጅ ታሪክ ተመልከቱ። ያ ፍቅር የሆነ አባት ታናሹ ልጅ ሀብቴን አካፍለኝ እና ልሂድ ሲለው፤ በልጁ ሕይወት ላይ ፈርዶ ነበር ሀብት ሰጥቶት የሸኘው። ልጁ ሊሞት እንደሚችል እያወቀ እንኳ ሊያግተው እና ሊያስቆመው እምብዛም አልሞከረም። ምክንያቱም የሰው ልጅ ከውድቀት የሚማር ፍጥረት ነው። ሰው የፍጽምና መለኪያ የሌለው ነው። ምን ጥሩ እና ምን መጥፎ እንደሆነ በማነጻጸሪያ ካልሆነ አይረዳም። ስለዚህ ምቾትን እና ጥሩ ሕይወትን እንዲያደንቅ ስቃይን እና መከራን መቅመስ እና በዛ ውስጥ ማለፍ አለበት። ያ ታናሽ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ አባክኖ ጨርሶ፣ የአሳማ ምግብ ሳይቀር ተከልክሎ ረሀብን በደንብ እስከሚያይ ድረስ የአባቱ ፍቅር እና የቸርነት ቤት አልታየውም ነበር። ያን የሚያደንቅ አዕምሮ አልነበረውም።



ልጆቻችሁ ከመከራ እና ከኃላፊነት በማገድ የምታስቆሙት ሕይወታቸውን ነው። ሲያድጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገኛቸው ያ ትንሹ መከራ ይገላቸዋል። የተኛበትን አልጋ እንዲያነጥፉ፣ ቤቱን እንዲያጸዳ፣ እቃ እንዲያጥብ፣ ለቤተሰቦቹ ምግብ እንዲያበስል፣ እንዲላላክ እና ከዛም ያለፉ ኃላፊነቶችን እንዲወስድ ያልተደረገ ልጅ፣ ነገ የትኛውንም ኃላፊነት የመወጣት አቅም አይኖረውም። ልጆቻንን ለሪስክ፣ ለመከራ እና ለአስቸጋሪ ሁኔታ ሆን ብለን ዛሬ ካላጋለጥናቸው ፥ አንድ ቀን ሕይወት ያንን ፊታቸው ስትደቅን መልሰው እኛኑ ነው የሚረግሙት። በዛ ሜዳ ተረተው እና ተሸንፈው ነው የሚቀሩት።ከሕይወት ወላፈንዲዎች ውስጥ አንዱ መከራ ነው። መከራ የሕይወት ጣዕም ነው። ችግር የመኖር ትርጉም ነው። ያንን መጋፈጥ፣ መረታት፣ መውደቅ፣ ለማሸነፍ መተናነቅ እና ማሸነፍ ነው በዚህ ዓለም ብዙ ርቀት የሚያስጉዘን። ለዛ ማይንድሴት የተዘጋጁ ናቸው የሕይወትን አውደ ውጊያዎች የሚሳተፉት እና የሚረቱት።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page