
ብድግ በል ፥ ተነስ። ማድረግ ያለብህን ነገር ሁሉ በሕይወት አድርግ። ስንፍና እና እንቅልፍ ማብዛት በሽታ ናቸው።ማማረር እና ሰበብ ማብዛት እንደ ካንሰር ሰርስረው የሚገሉት አንተኑ ነው። በራስህ ጉዳይ ኃላፊነት ውሰድ። ሕይወት ለአንተ ከሌሎች ሰዎች በላይ ከብዶ ሊሆን ይችላል። ከአንተ አስር እጅ ሕይወት የከበደባቸውን ሰዎች አስብ።
በዚህ ምድር ላይ ያለህ ውድ ነገር፣ ማንም የማይሰጥህ፣ በዕንቁ ወይም በማንኛውም የከበረ ነገር የማትለውጠው ጊዜህ ነው።ጊዜህን የሚያባክንብህ ሰው አንደኛ ጠላትህ ነው። በቶሎ ራቀው። ጊዜህን ተጠቀምበት። በወሬ እና በክፉ ነገሮች ክቡር የሆነውን ጊዜህን እንዳታሳልፍ ተጠንቀቅ። በቻልከው መጠን ሁሉ በየቀኑ ሩጥ። ሰውነትህን አድምጠው። ሲደክምህ በማረፍህ ደስ ይበልህ። ከድካምህ ስታርፍ ግን ተነስተ ተራመድ። ፈጽሞ እንዳትቆም ዳኽ ፥ እየተንፋቀክም ቢሆን ወደፊት ሂድ። አሁን ከአየኸው በላይ፣ አሁን ከያዝከው በላይ ለማየት፣ ለመጨበጥ ሩጥ። አምላክህ የሰጠኽን ጸጋዎች በእጥፍ አባዝተህ፣ አበርክተኽ ታስረክበው ዘንድ ፈጽሞ መዘናጋትን ለራስህ እንዳትሰጥ።
ምርጥ ለመሆን አትስራ ፥ በተሰማራሕበት መስክ የማትተካ ብቸኛ እና አንደኛ ለመሆን ብቻ ልፋ። ለዚህ መተው ያለብህ ነገር ካለ ተው።መቧጠጥ ያለብህ ካለህ ቧጥጥ። ሥራ ያዝናና። ሥራክ የሰዎችን እና ያንተን ሕይወት እንዴት የተሻለ እያደረገ መሆኑን በመመልከት ተደሰት። "በምንድነው የምትዝናናው?" ሲሉ በሥራዬ በላቸው። በዚህ አትፈር። ያንተ ሕይወት ለሌሎች ደባሪ ሊሆን ይችላል። ላንተ ሳቢ እና ማራኪ መሆን እንጂ የሚጠበቅበት ለሌሎች ማማለል የለበትም።
"ጥሩ እና ይሁን እስቲ" በሚባሉ የሕይወት ኩሬዎች አትዋኝ። ራስህን ዘወትር በአዲስ የለውጥ ውሃ ውስጥ ንከረው። መለወጥ አይቻልም የሚባሉ የሕይወት ዘርፎች ያሉት እስከሚለወጡ ድረስ ብቻ ነው። "ወፍ ብቻ ነው የሚበረው" ብለው የሚያምኑ ሰዎች የነበሩበት ዘመን ነበር፤ አይሮፕላን እስከሚፈጠር ድረስ። "በሩቅ ሀገር ካለ ሰው ጋር በመልክ እየተያዩ ማውራት በመለኮት ኃይል እንጂ ማንም ተራ ሰው ማድረግ አይቻለውም" ብለው የሚያምኑ ሰዎች ነበሩ፤ ኢንተርኔት እና ስማርት ስልክ እስከሚመጣ ድረስ። ስለዚህ ሰዎች አይቻልም ሲሉህ ብዙ ጊዜ እነደዚያ ያሉ ሰዎች እንደነበሩ እና ጥቂቶች እንደሚቻል እንዳሳዩ አስታውሳቸው። ለውጥን አምጥተህ እስከምታሳይ ድረስ ሰዎች ባንተ ባለማመናቸው አትደነቅ። አንተ ግን ለውጥ እንደሚቻል እመን።
በውጤቱ ሳይሆን በሂደቱ መደሰትን ተለማመድ። ለስንፍና እና ለክፋት እንቢ በማለትህ እና መልካምን ነገር ለማምጣት በመሥራትህ ተደሰት። ትግስት ግን ውጤቱን እንደሚቀይር እመን። የትግስት ማጣት ውጤቱን ይለውጠዋል።
ያንተ ሕይወት ያንተ ሕይወት ነው። የሌሎች የሌሎች ነው። ያንተ ስኬት የነሱ ቢሆን ሁሉም ይመኙታል። ያን የማድረግ ዲሲፕሊን ስላጠራቸው ነው አንተን ሊያሸማቅቁ የሚፈልጉት። በሌሎች ማስመሪያ ያንተን ሕይወት አትለካ። ያንተ ሕይወት ያንተ ሕይወት ነው። አንተን እንጂ መምሰል ያለበት ሌሎችን መምሰል የለበትም። ይሄን ስጦታ ሕይወትን ሳታባክን ተጠቀምበት።
በመጀመሪያ ስለ ሃሳቡ እጅግ አመሰግናለው ይህችን ሃሳብ ግን ብታብራራልኝ"ምርጥ ለመሆን አትስራ ፥ በተሰማራሕበት መስክ የማትተካ ብቸኛ እና አንደኛ ለመሆን ብቻ ልፋ"