top of page
Search

ከፈተና ሽሹ

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • 8 hours ago
  • 2 min read

በሆመስ ኦድሲ መጽሐፍ አስራ ሁለተኛው ክፍል ላይ የኢቲካውን ንጉስ ኦዲሲየስን ከሁሉም የሚለየው ታሪክ ተጽፏል።


ኦዲሲየስ ማንም ያላደረገውን ድንቅ ሥራ ሊሰራ ነው። ሳይረን የተባሉ በድምጻቸው ውበት ማንም የማያልፋቸውን እነዛን ሴቶች ማድመጥ ግን ደግሞ ደሴቲቱንም መሻገር። ያን ደሴት የተሻገረ አንድም ንጉስ ወይም ኃያል ከዛ በፊት አልነበረም። ምክንያቱም የእነዛ ሳይረን ሴቶች ሙዚቃን ለመስማት ሁሉም እዛ ደሴት ላይ ሲቆሙ ይጠፉ ነበር። ያንን ድምጽ ሰምቶ ወደ እነሱ አለመሄድ ፥ ሄዶ ደግሞ በሕይወት መቆየት የማይታሰብ ነበር።



ኦዲሲየስ ግን ያን ለማድረግ ወሰነ።



ግን በጥበብ ነበር። ወታደሮቹ ከመርከቡ ጋር ጠፍረው እንዲያስሩት አዘዛቸው። በምንም ተዓምር ፍጻሜያቸው ጋር ሳይደርሱ እንዳይፈቱት አስጠነቀቃቸው። ፍቱኝ ብሎ በመኃል ቢያዛቸው እንኳ። ከዛ ወታደሮቹ ጆሮ ውስጥ ደግሞ ዋክስ ከቶ ደፈነው። ምንም እንዳይሰሙ። አንድም ያን ሙዚቃ ሰምተው እነሱም ማለፍ አይችሉም። አንድም የእሱንም ፍቱኝ የሚል የጭወት ትዕዛዝ ሰምተው እንዳይፈቱት በማሰብ ያንን አደረገ።



ኦዲሲየስ እዛ ደሴት ጋር ሲደርስ የእነዛን አሳሳች ሴቶች ሙዚቃ አደመጠ። ፍቱኝ እያለ ጮኸ። ግን የመጀመሪያ ትዕዛዙን ሰምተው ወታደሮቹ ይሄኛውን ዝም ብለው አለፉት። በሰማው ድምጽ ቢታወክም ግን የታሰረበትን አላቆ ወደዛ ደሴት መሄድ ተሳነው። ስለዚህ ኦዲሲየስ የሳይረኖችን ድምጽ ሰምቶ ያን ደሴት የተሻገረ የመጀመሪያው ንጉስ ሆነ።



ኦዲሲየስ ራሱን አላመነም። በራሱ ስሜትን የመግዛት አቅም አልተደገፈም። ይልቁንስ ከፈተና በፊት ራሱን ጠበቀ። ብዙ ሰዎች ያልገባቸውን ቁምነገር ኦዲሲየስ ገብቶታል። ስትራቴጂው ስሜትን እገዛለው የሚል ሳይሆን ስሜትን ያለማመን ነበር።



በዚህ ዓለም ትልቁ ጠላት ፈተና አይደለም። በራስ መተማመን ነው። በራሱ ስሜትን የመግዛት፣ በራሱ ጥበብ፣ በራሱ እውቀት፣ በራሱ ራሱን የመግራት ብቃት የሚተማመን ሁሉ ይሸነፋል። ራሱን የሚጠራጠር እና ለዛም ከፈተናው በፊት አጥርን የሚያበጅ ሰው ፈተናዎችን ይሻገራል።



ዲሴምበር ላይ ሚኒሶታ ላይ የICE ሰዎች ሲመጡ አንዱ ደንበኛዬ ጥሎ ከሀገር ሊወጣ ነበር። ይሄ ነገር መቼ ነው የሚያበቃው ሲለኝ አላቅም አልኩት። እንደሚያቆም ግን ነገርኩት። አምስት ስድስት ወራት ወይም ሁለት እና ሦስት ወራት። ወይም ከዛ በላይ። ግን ያበቃል። ምን ትመክረኛለህ ሲለኝ በተቻለ መጠን ከዚህ የረብሻ ዜና ራስህን መጠበቅ ነው የምመክርህ አልኩት። ብዙ ሰዎች ከሚገጥማቸው መከራ በፊት በመከራው ዜና አስቀድመው ይሞታሉ።



ኦዲሲየስ ድምጹን ሰምቼ አልፋለሁ ብሎ በራሱ አልተመካም። ከዚህ በፊት የነበሩት ሁሉ ያን ብለው እንዳልቻሉ ያውቃል እና። ግን ራሱን በገመድ አሰረ። በወታደሮቹም አልተመካም። የእነሱንም ጆሮ በዋክስ ደፈነ። በፈተና ወቅት ነጻነት የባርነት በር እንደሆነ ገብቶታል። ገደብ በፈተና ፊት ነጻነት ነው።



ጥበበኞች ፈተናን እንጂ የሚያርቁት በፈተና ፊት ዲሲፕሊን ለመሆን አይደለም የሚጥሩት። ስሜታዊው ሰው ምክንያታዊውን ሰው ሁልጊዜ በፈተና ፊት ያሸንፈዋል። እውቀት ያላቸው ሰዎች ለዚህ ነው በውጥረት ወቅት የጅልነት ጭቃ ውስጥ የምናገኛቸው። መጪው ባልታወቀ መጠን ብዙ ገደቦች በዙሪያችን ያስፈልገናል። ጠንካራው ሰው ፈተናን የሚጋፈጠው አይደለም። መጋፈጥን አላስፈላጊ የሚያደርገው እንጂ።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page