top of page
Search

ምልክቶቻችን

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew


May 12, 2023



በየቀኑ እናሳየለን። በየደቂቃው አንዳች ነገር እንለቃለን። ጎበዝ መሆናችንን፣ ስኬታማ መሆናችንን፣ ቆንጆ መሆናችንን የሚያሳዩ ምልክቶችን፣ ብልጭታዎችን በየደቂቃው እንለቃለን። ብዙ ጊዜ ጎበዝ መሆናችንን ወይም ቆንጆ መሆናችንን በይፋ እንዲህ ነን ብለን አንገልጽም። አንድም ጉራ ስለሚመስልብን፣ አንድም ሰዎች እንደዚህ ስንል ሊጠየፉን ስለሚችሉ እና ጉራን ብዙ ሰዎች ስለሚጠሉ በቃላት ከመግለጽ እንቆጠባለን። ታዲያ ምንድነው የምናደርገው? ምልክት እንሰጣለን።



ትሁት ነን ብለን መናገር አንፈልግም። ያ’ማ ትዕቢት ሆነ። ስለዚህ ትዕቢትን በትህትና ምልክት እንደብቃለን። አንገትን ቀንጥሶ ሰላም ማለት፣ ጎብጦ መሄድ፣ ቆንጆ ሆነን ሳለ “ቆንጆ ናችሁ ስንባል ፥ አረ ምናምን” ማለት፣ ጎበዝ ሆነን ሳለ “እኔ ካንተ በላይ አላውቅም” የሚሉ የቃላት ጫወታዎችን መጫወት የትህትና ምልክት መስጠት ነው።



ሀብታም ነን፣ ገንዘብ አለን ብለን ማውራት አንፈልግም። ግን ምልክት እንሰጣለን። በምንነዳው መኪና፣ በምንኖርበት ቤት ምልክት እንሰጣለን። ጫማችን፣ መጠጣችን፣ ሰዓታችንን የምናሳልፈበት ሁኔታ ምልክት ነው። ለዓለም የምንሰጠው ምልክት ነው። ድብቅ ቋንቋዎች ናቸው።



ምልክቶች ለሰዎች ስለማንነታችን የምንሰጠው ውድ ቋንቋዎች ናቸው። ለምሳሌ ምንም ገንዘብ ሳይኖረን ገንዘብ እንዳለን ምልክት የምንሰጥ ከሆነ፤ ያ ምልክት በጣም ውድ ምልክት ነው። እንደዚህ ዓይነት ማሳያዎች ብዙ ጊዜ እና አቅም ይወስዳሉ። ምክንያቱም የምናሳየው ምልክት ታማኝ እንዲሆን ብዙ ዋጋ መክፈል ይኖርብናል።



ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰው ትልቅ ወጪ አውጥቶ የሚገነባው ከሰባት ሰዓት በላይ የሚያሳልፈበትን መኝታ ቤቱን አይደለም፤ አጥሩ ላይ እንጂ። ወይም ለሰዎች ዕይታ የሚውሉ ቁሶች ላይ ኢንቨስት ማድረግን ይመርጣል። በመሠረታዊነት ሕይወቱን የሚለውጡ ጉዳዮች ላይ ገንዘቡን እና አቅሙን ከማዋል ይልቅ።



ሰዎች የሚሰጡንን ምልክት በጥንቃቄ መገንዘብ ይኖርብናል። ምክንያቱም የዛ ሰው አጠቃላይ ስነልቦናዊ መዋቅር ከእነዛ ምልክቶች ጋር የተያያዘ ነው። ምልክቶችን ችላ ማለት ሰዎችን አለመገንዘብ ያስከትላል። ናሲም ታሌብ አንድ ታሪክ አለው። ከታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎችን ብቻ የሚቀጥር ሆስፒታል ውስጥ ታማችሁ ብትሄዱ እና ሁሉም ዶክተሮች ጽዱ የለበሱ፣ የተመረቁበትን ሠርተፊኬት በቢሯቸው ግርግዳ ላይ የለጠፉ ቢሆኑ፤ ከእነዚህ ግን አንዱ ዶክተር ጸጉሩ የተንጨባረረ፣ ግርግዳው ላይ ምንም ሠርተፊኬት ያለጠፈ፣ አለባበሱም እንደነገርየው ቢሆን፤ እናንተ ወደዚህ ሆስፒታል ብትሄዱ እና ከማንኛው ዶክተር ጋር መታከም እንደምትፈልጉ ምርጫ ቢሰጣችሁ፤ ከዛ በፊት ስለማንኛውም ዶክተሮች ምንም እውቀት ባይኖራችሁ የትኛውን ዶክተር ነው የምትመርጡት?



ናሲም ታሌብ እንዲህ ይላል፦ የኔ ምርጫ ይሄ አለባበሱ እንደነገሩ የሆነ፣ ከታላቅ ዩኒቨርስቲ መመረቁን የሚያሳይ ምልክት ያለጠፈው፣ ጸጉሩን በአግባቡ ያላበጠረው ዶክተር ነው። ምክንያቱም ይላል ታሌብ እንደዚህ ባለ ታላቅ ሆስፒታል ውስጥ እንደዚህ ያለ ዶክተር በሥራው ለመቀጠል አቻ የሌለው ሙያ ሊኖረው ይገባል። ሁሉም በዚህ ተቋም ለመቀጠል ምልክት ማሳየት እና የተቋሙን የእይታ ፕሮቶኮል መጠበቅ ግዴታቸው ነበር። ይሄ ዶክተር ግን ያን ውጪያዊ ፕሮቶኮሎች ችላ ብሎ እንዲቀጥል የተፈቀደለት አንዳች ማንም የሚተካው ሙያዊ ብቃት ስላለው ነው። ልብ በሉ ይሄን ምርጫ እንድትመርጡ የተገደዳችሁት ስለማናቸውም አስቀድሞ ምንም እውቀት ከሌላችሁ ነው።



በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር ጥሩ ውሳኔን የመወሰን ችሎታን የሚተካ ምንም ችሎታ የለም። ጥሩ ሕይወት ማለት የተከታታይ ጥሩ ውሳኔዎች ውጤት ነው። ብዙ ውሳኔዎች ደግሞ በእንደዚህ ዓይነት ጥበባዊ ብቃት ካልሆነ በፊታችን እሣት እና ውሃ ቀርቦልን ወደ ፈለከው እጅህን ክተት የሚል ዓይነት አይደለም። ውሃው እሣት በሚመስልበት፣ እሣቱ ውሃ በሚመስልበት ዓለም ውስጥ ሆነን ነው ጥሩ ውሳኔ እንድንወስን የተጋበዝነው። ስለዚህ ምልክቶችን መረዳት በጣም ወሳኝ ነው።



ለምሳሌ በቤታችን ብዙ ወርቅ ቢኖረን ምን ውስጥ ነው የምናስቀምጠው? ምን ዓይነት ምልክት (signal) ነው ቤት ውስጥ በድንገት ለሚገቡ ሰዎች መስጠት የምንፈልገው። ወርቁን ወርቅ በመሰለ ዕቃ ውስጥ ነው የምንደብቀው ወይስ ሌባ ቢገባ ችላ ሊለው በሚችል ተራ ዕቃ ውስጥ ነው የምንደብቀው? ማንም ወርቁን ከሌባ ለመደበቅ የሚሻ ሰው ሌቦች ቤት ውስጥ ድንገት ቢገቡ ወርቁ ሊኖር ይችላል ብለው በማይጠረጥሩት ዕቃ ውስጥ ነው ወርቆቹን የሚደብቀው።



እንደ መንሱር ጀማል ያለ ሰው ዘወትር ስለሀብቱ ምልክት መስጠት አለበት። ምክንያቱም ሀብት የለውም እና። እንደ ኃይለ ገብረሥላሴ ያለ ሰው ሀብቱን የገነባው በባንክ ብድር እንደሆነ፣ ከፍተኛ የባንክ ብድሮች እንዳሉበት ምልክት መስጠት አለበት። ምክንያቱም ከፍተኛ ሀብት አለውና።



እምብዛም ደስታ እና ፍቅር የሌላቸው ፍቅረኛሞች ፥ ፍቅር እና ደስታ እንዳላቸው በየጊዜው በማህበራዊ ድረገጽ በሚለጥፉት ፎቶዎች ያን መግለጽ አለባቸው። ምክንያቱም ጉድለት በቤታቸው እንዳለ ይሰማቸዋልና። ሰውን እናንጨርጭረው ብለው ፎቶ የሚለጥፉ ሰዎች ሞልተዋል።



ምልክቶችን መረዳት በጣም ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ትልልቅ ውሳኔዎችን በሕይወት የምንወስነው ሰዎች በሚያሳዩን ምልክቶች ነው። በቅርብ በቤተክርስቲያን ቅዳሴ ወቅት ከአጠገቤ በነጭ ሽበት ጸጉር እና ጺም የተዋቡ ትልቅ ሰው ቆመዋል። አዕምሮዬ እኚን ሰው እንደ ቅዱስ መሳል ፈለገ። ወዲያው ግን “ለምንድነው እኚን ሰው እንደዛ ያየኸው?” ብዬ ራሴን ጠየኩኝ። መልሱ ሽበታቸው ነው የሚል ብቻ ነው። በቅዱሳን ስዕል አድኅኖ ላይ ዘወትር የምናየው እንደዛ ዓይነት ገጽታ ስለሆነ፥ አዕምሮዬ እኚን ሰው በአንዴ በውስጤ ከተመዘገበው ስዕል አድኅኖ ጋር በማያያዝ ቅድስና ሰጣቸው። ግን እኚ ሰው መልካም እና ክፉ የመሆናቸው ዕድል ተመሳሳይ ነው። ገጽታቸው ብቻውን ለምንም ነገር በቂ ምልክት አይደለም። እንደዚህ ዓይነት ሪፍሌክሽን የማያደርግ ሰው፣ እኚ ሰው ተጠግተውት ገንዘብ አበድረኝ ከዛም በሳምንቱ እከፍልሃለው ቢሉት እና ሌላ ተመሳሳይ ሽበት የሌለው ሰው ቢጠይቀው፤ በሽበት ለተሞላው ሰው የበለጠ እምነት ይኖረዋል። ምክንያቱም ምልክቶችን ያለምንም ሪፍሌክሽን ተቀብሎ አስተናግዷል።ሊዮ ቶልስቶይ እንዲህ ይላል “ውበትን መልካም ከመሆን ጋር የምናመሳስለው ነገር እጅግ አስደናቂ ግራ መጋባታችን ነው።”



አንዳንዴ ደግሞ ምልክት መስጠት ሳንፈልግ ምልክት እንሰጣለን። ማለትም በጣም ሀብታም ሆነን ሳለ ድሀ የሚውልበት ሥፍራ መታየት እንፈልጋለን። መስጠት የምንፈልገው ምልክት “ትሁት ነው” የሚልን ነው። “ራሱን አይቆልልም” የሚለውን ነው። ወይም እሱ አያካብድም የሚለውን ምልክት መስጠት ስለምንፈልግ አለባበሳችንን እንደነገሩ፣ አነጋገራችንን እንደዘመኑ፣ ወይም የገባው ነው የሚለው ስያሜ እንዲሰጠን ለዛ ተስማሚ የሆኑ ምልክቶችን እንሰጣለን። ለምሳሌ ሥርዓት ላይ አለመጠንቀቅ ወይም በጣም ሀብታም ሆነን ሳለ በቲሸርት መታየት ወይም ቀሎ መገኘት ምክንያቱም የገባው ነው የሚለውን ስያሜ እንፈልገዋለን። ይሄ ማለት ምልክት መስጠትን ባለመፈለግ ምልክት መስጠት ማለት ነው (the act of signaling something by not signaling that thing)። ለምሳሌ በጣም ሀብታም የሆኑ ወላጆች እና ሀብታቸው የታወቀላቸው ‘ልጆቻቸው ዘንጠው ስለመታየታቸው’ እምብዛም አይጨንቃቸውም፤ ምክንያቱም ሀብታም ሆኖ የመታየት ጭንቀት የለባቸውምና። በጣም ጎበዝ ተማሪ ለምሳሌ ጎበዝ መሆኑን ለማሳየት ጥያቄ ለመመለስ እጁን ለማንሳት አይሯሯጥም፣ አንድም ዶክተሮች የእጅ ጹሁፋቸው አስቀያሚ የሚሆነው ፥ የተገነባ ክብር ስላላቸው በእጅ ጹሁፋቸው ማስመስከር የሚፈልጉት ነገር የላቸውም። የተደላደለ ጥሩ ዝና ያለው ሰው ለትንንሹ ነቀፋ ሁሉ መልስ ሲሰጥ አይውልም። በጣም ጎበዝ የሆነው ዶክተር በግርግዳው ላይ የተመረቀበትን ሠርተፊኬት የመለጠፍ ፍላጎት የለውም።



ጆን ስቴንቤክ እንዲህ ይላል “በዚህ ምድር ላይ በጣም ውበት ያላቸው ነገሮች ምንም ጥቅም የሌላቸው ነገሮች መሆኑን አትርሱ፤ ለምሳሌ ፒኮክ እና ሊሊ አበባን ተመልከቱ።”



በብዙ የሥራ ቦታዎች ሰዎች ታማኝ መሆናቸውን እና ጠንካራ ሠራተኛ መሆናቸውን ምልክት መስጠት አለባቸው። ስለዚህ እውነተኛ ታማኝ ከመሆናቸው በላይ፣ ሥራቸውን በጥራት ከመሥራታቸው በላይ ቁምነገሩ ምልክት መስጠታቸው ይሆናል። በአንድ ወቅት እሠራ በነበረበት የሕግ ቢሮ ውስጥ ያለው የጠበቆች ረዳት ጠረጴዛው በወረቀት እና በፋይል የተሞላ ነበር። ጠጋ ብዬ በዚህ ሁኔታ ፋይሎች ሊጠፉ ስለሚችሉ ጠረጴዛውን ንጹሁ እንዲያደርገው፣ እርዳታም ከፈለገ ላግዘው እንደምችል ነገርኩት። እሱ ግን “ጠረጴዛዬ ንጹሁ ከሆነ አለቆች ሥራ እየሠራው አይመስላቸውም፣ ብዙ ሥራ እየሠራው መሆኔን እና የተጨናነኩኝ እንደሆንኩ ለማሳየት ጠረጴዛዬ እንዲህ በፋይል እና በወረቀት መሞላት አለበት” አለኝ። የሕግ ቢሮው ከእውነተኛ ሥራ ይልቅ ማስመሰልን የሚያስቀድም መሆኑ አሳዘነኝ። ይሄ ልጅ ከፋይል መጥፋት እና ሥራው በአግባቡ ከመሠራቱ ይልቅ የቢዚነትን ምልክትን የሚያበረታታ ባህል በዚህ ትልቅ የሕግ ቢሮ ውስጥ እንዳለ ስለገባው ፥ ይሄን የቢሮ ፖለቲካ በአግባቡ እየተጫወተው ነበር።



ምልክት የሰዎች ቃላት አልባ ቋንቋ ነው። ባህል፣ ድንበር እና ማንነትን ተሻግሮ ያለ ነው። ብዙዎቻችን እነዚህን ምልክቶች አንብበን የተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን። ለምሳሌ በጣም የምንወዳት አርቲስት ያስተዋወቀችውን ቅባት ልንገዛ እንችላለን፣ ምንም እንኳ ያቺ አርቲስት አንድ ቀንም ያን ቅባት ተጠቅማ ባታውቅም። ጥሩ የለበሰን ሰው ታማኝ አድርገን እንወስዳለን። ቀልድ አዋቂን ሰው ብናገባ በትዳራችን ሁሉ ሲያስደስተን የሚያኖረን ይመስለናል። መልኳ ያማረችን ሴት ከጥሩ ባህሪ ጋር አንድ እናደርጋታለን። የሚያቆላምጠን ሰው የሚወደን ይመስለናል። ስለምልክቶች እና የድብቅ ምልክቶች (ማለትም ሀብታም ሆኖ ድኅ፣ ቆንጆ ሆኖ አስቀያሚ ለመምሰል) ማወቅ ለጥሩ የሕይወት ውሳኔ ጥቅም አለው። እኛም ስለምንሰጠው ምልክቶች እናስተውል። ምን ያህል እውነተኛ እና ተገቢም እንደሆነ እንመዝን።



36 views0 comments

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page