
ሙያተኛ ስትሆኑ ሰዎች በእናንተ ላይ ሊደገፉ ይፈልጋሉ። የመጨረሻውን ውሳኔ እናንተ እንድትሰጡላቸው ይመኛሉ። ግንበእውቀት እና በልምድ ከፍ ስትሉ እርግጠኝነት የእውቀት እና የልምድ እጥረት ውጤት መሆኑን ታውቃላችሁ። ስለዚህ ያን የበለጠ ታሶግዳላችሁ። ከእናንተ በእውቀት የሚያንሱ ሰዎች ያን እርግጠኝነት ሲያጡ ፥ ከእውቀት እና ልምድ ጋር ያያይዙታል። ስለዚህ ለአጭበርባሪዎች ወይም ላነሰ እውቀት ላላቸው ይሰጣሉ።
ወደ ጌታችን የፍጻሜ ዘመን ስብከት ሂዱ። ከሁሉ አዋቂ አባቱ ዘንድ የመጣው ልጅ ፥ ስለፍጻሜው ዘመን ምልክት እንጂ እርግጠኝነት በርሱ ቃላት ውስጥ አልነበረም። ያ በእውቀት ማነስ የመጣ ግን አልነበረም በእውቀት መብዛት እንጂ።ከርሱ እውቀት ጋር የማይነጻጸሩት የሐዋርያትን የፍጻሜ ዘመን ስብከት ደግሞ ተመልከቱ ፥ “ጌታ አሁን ይመጣል” ነበር ያሉን። ምንአልባትም በእነርሱ የእድሜ ዘመን ወይም ከእነርሱ በጥቂት ዘመን ተሻግሮ ክርስቶስ እንደሚመጣ ይሰብኩ ነበር። ያም እርግጠኝነት በተሞላበት መልኩ ነበር። ያ ግን አልሆነም። ከሦስት ሺ ዘመን በኋላም ያን ክስተት እየጠበቅን ነው። በሌላም ዘርፍ እርግጠኝነት አንድን ነገር በጥልቀት የመረዳት እጥረት ነው።
ሪስክ የሚወስዱ ሰዎች ናቸው በብዛት የሚያተርፉት። በተመሳሳይ ሪስክ የሚወስዱ ሰዎች ናቸው የሚከስሩት። አሉታዊያን በሕይወት ላይ ብዙ ጊዜ ልክ ናቸው። አዎንታዊያን ግን በሕይወት ደስተኛ ናቸው። ምክንያቱም እነሱ የማይቻል የነበረውን የሚቀይሩ ናቸውና። እርግጠኝነትን መፈለግ የውሳኔ ሽባነትን ያመጣል። ሕይወት ልንሞክራት፣ የማይቻል የሚመስለውን ነገር ፈራ ተባ እያልን ልንገፋው የተሰጠን ስጦታ ናት። ይሄ ሕይወት አንድ ብቸኛ ዕድላችን ናት። አንድ ብቸኛ ዕድል ከዚህ በፊት የነበሩ ሰዎች ባስቀመጡልን ሥሪት ብቻ በመመራት ማለቅ የለበትም። ትንሽ ድንበሮችን መግፋት፣ ትንሽ የተገነቡ ነገሮችን አፍርሶ በተሻለ ለማቆም የምንጥርበትም መሆን አለበት። ለዛ ደግሞ ከእርግጠኝነት ይልቅ የመሆን ዕድልን (probability) ነው ማጤን ያለብን። የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለን ነገር እርግጠኛ ስላልሆንን ብቻ ማቆም የበጎ ለውጥ መቅሰፍት ነው።
አንገት የሚያጎነብሱ ሰዎችን ሳይሆን አንገትን ቀና የሚያደርጉ ትውልዶችን ስለማፍራት ነው ማሰብ ያለብን። በሆነ መጠን በእውቀት እና በድፍረት እንቢ የሚሉ ሰዎች ብቻ ናቸው ድንበር የሚሻገሩ፣ አይቻልም የሚባሉ ተግባሮችን አስችለው ያሳዩን። እነዚህ ሰዎች እርግጠኝነት ደባሪ የሆነባቸው እና መሞከር የሚያረካቸው ናቸው።
ስለሚመጣው ነገር በርግጠኝነት የምናውቅ ቢሆን፤ ሕይወታችን ከሕይወት የተላቀቀ ይሆን ነበር። መደነቅ እና ደስታ የጎደለው፣ መደንገጥ እና መረበሽ የራቀው ፥ መሳቅ እና መቦረቅ የሸሸው ይሆን ነበር። አለማወቅ ነው ተራራ ጫፍ የወሰደን። አለማወቅ ነው ያስወደደን ያስከዳን። እርግጠኝነትን የሚሰጠን ሁሉ ከእውነትም ከሕይወትም የተጣላ ነው። ወይም የኛን ደካማ ጎን ለጥቅሙ የሚያውል ነው። በዚህ ዓለም ላይ ሞት ሳይቀር እርግጠኛ እንዳልሆነ ፥ ሔኖክ እንዳልሞተ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን እናያለን። እንደ ብራየን ጆንሰን ያሉ ሰዎች የሞትን እርግጠኝነት እየተጋፉ ነው። ምን አልባት ይሳካላቸው ይሆናል፤ ግን ይሄ ድንበርን መግፋት ነው የሰው እውነተኛ ተፈጥሮ። ማመጽ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው። የሚጠቅመው ቢሆን እንኳ የሆነን ነገር በአታድርግ ትዕዛዝ መቀበል እንደማይፈልግ የመጀመሪያው ሰው አሳይቷል።
ውሳኔ ስንወስን የማይታወቅ ሪስክ ካለው ልምድ እና እውቀት ላይ እንደገፍ፤ የሚታወቅ ሪስክ ከሆነ ደግሞ የመሆን ዕድል (probability) እና አመክንዮ ላይ እንመርኮዝ። እንጂ ከእርግጠኝነት ወዳጅ አንሁን።
Opmerkingen