June 24, 2023

ብዙ ሰዎች በወጣትነታቸው ሕይወትን ሌሎች ሰዎች ከኖሩት ውጪ የሚኖሩ ይመስላቸው እና ብዙ ለማሳካት ይጥራሉ። አንዳንዶች ያሳካሉ ፥ ልክ እንደ ብዙ ነገር አንዳንዶች ደግሞ የፈለጉትን ሳያገኙ ይቀራሉ። ያሳኩት ግን ፥ አጥብቀው የፈለጉት ነገር እጃቸው ላይ ሲገባ “ለዚህ ነበር እንዴ?” ይላሉ። የሕይወት ትርጉምን በሕይወታቸው መጨረሻ ድጋሚ ይጠይቃሉ። ስቲቪ ጆብ የሕይወት ታሪኩን ለሚጽፍለት ዋልተር አይዛክሰን ያለው ይሄን ነበር፤ “ምንድነው ሕይወት፣ በቃ ለዚህ ነበር የደከምኹት? ልክ ስትወለድ ብቻኽን እንደመጣኸው ስትሞትም ብቻኽን ልፋትኽን ሁሉ አራግፈክ ትሄዳለኽ።” የተሳካላቸው የምንላቸው ሰዎች ከሞላ ጎደል በሞታቸው አልጋ ላይ ይሄን ጠይቀዋል።
ሊዮ ቶልስቶይ የኢቫን ሞት በሚለው መጽሐፉ ፥ የስመጥሩን ዳኛ ኢቫን ሞትን የሰሙ ጓደኞቹ በዛው ሰከንድ ያሰቡት የእርሱን ቦታ ማናቸው እንደሚወስዱ እንደነበር ጽፎልናል። ልጆቻችን ሳይቀር በዚያው ሰከንድ የሚያስቡት ስለራሳቸው ቀጣይ ሕይወት ነው። ይሄ ዑድት በእነርሱ ሞት ሰዓትም ይቀጥላል።
የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢዮብ “ምንድነው የተፈጠረው?” ብሎ ግራ የተጋባ ሰው ነበረ። ለዚህም እግዚአብሔር ይምጣና ለጥያቄዎቼ መልስ ይስጥ አለ። ጓደኞቹ በተግባር ኃጢአት እንዳልሠራ ቢያምኑም በልቡ እና በቃሉ ግን በድለኽ ይሆናል ብለው ከሰሱት። ኢዮብ ግን ለዚያም መልስ ነበረው፤ “በቃሌም ኃጢአት ሠርቼ ከሆነ በልቤም በድዬ ከሆነ ኃጢአቴን በይፋ ይግለጠው። እኔም ንስሓ ልግባ” አለ። በመጨረሻም መከራን ከኃጢአት ጋር ያገናኙት የኢዮብ ወዳጆች ሲቀጡ ለኢዮብ ጥያቄ ግን እግዚአብሔር መልስ ሳይሰጥ ቀረ። ለምን? በሰጥቶ መቀበል መርሕ የተገነባው የሰው ልጅ ሕይወት “የጽድቅ ሥራ ዋጋ ሁልጊዜ በረከት ነው የኃጢአትም ዋጋ መቅሰፍት” ብሎ ያስባል። ይሄ አስተሳሰብ ከቅዱስ ዳዊት ጀምሮ እስከ ሌሎች ብዙኃን ቅዱሳን ግራ ያጋባ ነገር ነበር። ኃጢአተኛ ሲያብብ እና ሲለመልም አይተው “ጽድቅ መሥራታችን ታዲያ ምንድነው ዋጋው?” ብለው ነበር። ዛሬም ብዙዎቻችን “’ባክህ ሰው ሁሉ እንዲያ ነው የሚያደርገው” በማለት የክፋትን በር እናንኳኳለን።
እግዚአብሔር ግን ፍጥረቱን በፍትሕ ብቻ የሚመራ እንዳልሆነ ፥ የኃይሉን ስፋት እና የፍጥረቱን ብዛት ለኢዮብ በመግለጥ ፥ ኢዮብ በትህትና የዚህን ዓለም ሕይወት እንዲቀበል ሆነ። ጠቢቡ ሰሎሞን ይሄን በሚገርም አገላለጽ ጽፎታል። “እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።” መክ 9:11
አላን ዋትስ “የሕይወት ግብ መኖር ብቻ ነው” ይላል። ስኬትን የሕይወት ግብ አድርጎ የሚያስብ ሰው በሕይወት ጎስቋላ ፍጻሜ ከሚኖረው አንዱ ነው። ሕይወት ሕይወት ብቻ ነው ግቧ። በሕይወት ጥበቃቸው አንስተኛ የሆኑ ሰዎች ደስታቸው በጣም ትልቅ ነው። ሁሉ ነገር በእነሱ ሊደርስ እንደሚችል ያምናሉና።በናዚ ኦሽዊትዝ ካምፕ ውስጥ ዘግናኝ ሕይወትን ያሳለፈው ቪክቶር ፍራንክል በካምፑ ውስጥ ከሁሉም በፍጥነት የሞቱት “optimist”ቶች ነበሩ ይላል። ሴኒካ ለጓደኛው በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ለምንድ ነው ሞት የሚያስፈራ?” ፥ “በሕይወት ያለ ብቻ እኮ ነው የሚሞተው” ይለዋል። ይሄ ማለት ሞት የሕይወት ምስክር ነው። ይሄ ማለት መከራ የመልካም ነገር ትንሣኤ ነው።እያለን ነው። ግን ሁልጊዜ በሕይወት የሆነ ነገር ማግኘት አለብን ብለን ስለምናስብ ፥ ሕይወትን ሳናውቃት እናልፋለን። የኢዮብ መጽሐፍ ጸሓፊ የሚጋብዘንም ለእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ሥራዎች ምክንያት መፈለግን እንድንተው እና የሆነውን ነገር መቀበል እንድንለምድ ነው። መተው መቀበል ጥቂት ሰዎች የታደሉት የስብዕና ደረጃ ነው።
ይሄ የገባት የታላቁ ሊቅ እና ምጡቅ አእምሮ ባለቤት የቅዱስ አውግስጢኖስ እናት ሞኒካ ነበረች። አውግስጢኖስ በዘመኑ ከነበሩ አዋቂዎች የሚወዳደረው ያልነበረ እና በዚህም ከአልጄሪያ ካርቴጅ ተነሥቶ የሮም ንጉሥ የቫለንቲኒያን የንግግር አስተማሪ የነበረ ነበር። በሃያዎቹ መጨረሻ ክርስቲያን እስከሚሆን ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን የሕፃናት ተረት ተረት ነበር የሚለው። ለእርሱ የአመክንዮ አእምሮ አንሶበት ነበርና። አውግስጢኖስ ከእናቱ ጋር ምሳ ሲበሉ ብዙ ጊዜ ስለብዙ የዓለም ሁኔታዎች የማውራት ልምድ ነበራቸው። ክርስቲያን ከሆነ በኋላ የሚያስታውሰው አንድ ታሪክ ነበረው። እርሱም ምሳ በልቶ እንደጨረሰ የበላውን ነገር ረሳው። ከዚያ እናቱን ምን እንደበላ ጠየቃት። እርሷም ስቃ ዝም አለች። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ሲያወሩ “ይሄ ለአዕምሮዬ አይመጥንም” አላት። እሷም “አሁን የበላኸውን ምሳኽን የረሳው አዕምሮ ነው እሱ?” በማለት በደቂቃዎች ውስጥ የተፈጸመን ነገር የሚረሳ አዕምሮው ክርስቶስን ለማወቅ መደገፊያው መሆኑ ምን ያህል ስህተት እንደሆነ አሳየችው። ሕይወት ከአዕምሮአችን በላይ ነው። ለሕይወት በአዕምሮአችን ብቻ ትርጉም የምንፈልግለት ከሆነ ፥ ምስኪን ብኩን ሆነን ነው የምንቀረው።
በርትራንድ ራስል ስለኢዮብ የሚነግረን የሚመስል ምሳሌ አለው:- የዶሮዋ ሕይወት። ዶሮዋ በየቀኑ ጌቶቿ ይመግቧታል። ይሄ በየቀኑ እና ለብዙ ጊዜ ከመካሄዱ የተነሳ ዶሮዋ በየቀኑ በጌቶቿ መመገብ የማይቀር የሕይወት ሐቅ አድርጋ ቆጥረዋለች። አንድ ቀን ግን ያ ሁሉ መግቦት በጌቶቿ ቢላዋ ይተካል። ይሄ መታረድ ፥ ይሄ ቢላዋ ልትገምተው የምትችለው አይደለም። ምክንያቱም ሲከሰት አንዴ ነው። ከተከሰተ ደግሞ ትምህርት የሚወሰድበት ዕድልም የለም። ብዙዎቻችን ለሕይወት መጥፎ ነገር እንዘጋጃለን። መጥፎ የምንለው ነገር ሳይቀር ግን ትላንት በሌሎች ላይ የተከሰተ ነው። ከዛ ውጪ መጥፎ ነገር አዕምሮአችን እራሱ ሊያስብ አይችልም። ዶሮዎ ትላንት ያደረገችውን ነገር እስካደረገች ድረስ ፥ ዛሬም ሕይወት በተመሳሳይ መቀጠል አለባት ብላ ታስባለች። ያ ግን ሁልጊዜ እውነት አይደለም። ኢዮብ በመጽሐፉ እንደሚነግረን በየቀኑ ለእራሱ ብቻ ሳይሆን ለልጆቹ ጭምር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ነበር። በዚህም የጽድቅ ዋጋ የሆነውን ነገር አላጣም ፥ ያ ቢላዋ እስከሚመጣ ድረስ። ለዚህ ነው ትርጉም ያጣለት። ለዚህ ነው ትርጉም የፈለገው።
አጼ ቴዎድሮስ ራስ ጉግሳን ከማረኩ በኋላ የደበከውን ወርቅ አምጣ ብለው በፈረስ ጭራ አስጎተቱት። በኋላ የቀበረውን ወርቅ ሲያወጣ ፥ “ይሄን ሁሉ ለምን ነበር ቆፍረኽ የቀበርኸው?” ሲልቱ “ለክፉ ቀን ብዬ” አለ። አጼ ቴዎድሮስ ፈገግ ብሎ “በበጎ ቀን የተቀመጠ ለክፉ ቀን መውጫ ከሆነማ ፥ ምን ክፉ ቀን አለ!” አሉት።
ሰር ሚካዬል ሀዋርድ በ1973 ዓ.ም በሰጠው ሌክቸር “በውጊያ ውስጥ የጦር መሪዎች እና ወታደሮች መማር ያለባቸው ፈጽሞ የማይገመተው፣ ማንም የማይጠብቀው ነገር ሲመጣ እንዴት ያንን መቀበል እና በዛ ውስጥ ማለፍ እንደሚገባ ነው” ይላል። የጦር ስትራቴጂስቱ ካርል ቫን ክላስዊትዝ “ጦርነት ማለት የሁለት ሰዎች ጥል (two persons duel) ወደ ሀገራት ከፍ ብሎ ማለት ነው” ይላል። ፕሮፌሰር ሎረንስ ፍሬድማን ደግሞ ያልታሰበ ነገር (suprise) በጦርነት ብቻ ሳይሆን ፥ “ሀገራትም 100% ሰላም ነን፣ ችግር የለም ብለው በተቀመጡበት ራሳቸውን በጦርነት፣ በጥልቅ ችግር እና በአሳፋሪ ሁኔታ የጠላትን ሴራ ቀድመው መንቃት ተስኗቸው ያገኙታል” ይላል። ልክ እንደጦርነት ሕይወት ፈጽሞ ያላሰብነው ፥ መቼም ያልጠበቅነው ነገር የምታስተናግድ ናት። ይሄን ቀና እንዳሉ ፥ ከነሞገሳቸው እንደ ኢዮብ የሚያስተናግዱት ግን ጥቂቶች ናቸው። ለምን? ብዙዎቻችን “በሰጥቶ መቀበል” እና “በአመክንዮ” መታወራችን ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ሴኒካ ለሉሲለስ ሲጽፍለት “ካንተ የሚወሰድብህ ነገር ሁሉ ያንተ አይደለም። ያንተ ባልሆነ ነገር መደገፍን አሶግድ” ይለዋል። የእኛ የሆነ ነገር ፥ ሊወሰድብን የማይችል ምን አለ?
Commentaires