top of page
Search

የዘላለም ፍርድ

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew



አንድ እግዚአብሔርን እጅግ የሚወድ ወዳጅ አለኝ። ነገር ግን ስለሲዖል ሲያስብ ግራ ይገባዋል። እግዚአብሔር ምን ያህል ፍቅር እንደሆነ እያወቀ፣ ስለ ሲዖል የሚሰጠውን ትምህርት ደግሞ ለመቀበል ይቸገራል። ልጆች ስላሉት ለዘላለም እግዚአብሔር ልጆቹን በእሳት ያቃጥላል የሚለው ትምህርት አይዋጥለትም። በልጆቹ ፈጽሞ የማይጨክነው እርሱ፤ እግዚአብሔር ፍቅር ሆኖ ሳለ በእጆቹ ውብ ሥራ የሰው ልጆች ላይ ይጨክናል የሚለው ይጸንነዋል። በርግጥ ይሄ እኔንም የሚከብደኝ ትምህርት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ሳይሆን ፍትሕ እና እውነትም እንደሆነ ስለምንዘነጋ እና ያን ደግሞ ፍቅሩን የተቀበሉት ከእርሱ የሚጠብቁት እንደሆነ ስለምንረሳ ነው። ማለትም እግዚአብሔርን ለማፍቀራቸው አንዱ የእርሱ ፍትሐዊነት እና እውነተኝነትም ነው።



 ይሄን በጥቂቱ ከማብራራቴ በፊት “የእኛስ ቅጣት ከእግዚአብሔር ይለያል ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ልጠይቅ በመጀመሪያ፤ ሲዖል በዋናነት የሚከብደን ኃጢአተኛ በመቀጣቱ ሳይሆን ፥ በጥቂቱ የሕይወት ዕድሜው በሠራው ኃጢአት እንዴት ዘላለም ይቀጣል፤ ያውም በገሀነም እሳት የሚለው ነው። ማለትም ‘ኃጢአት የሠራበት ዘመን እና የመቀጣቱ ዘመን ርዝማኔ አይመጣጠንም’ ነው እያልን ያለነው እንጂ “የሰው ልጆችን በእሳት ቼምበር አቃጥሎ ሥጋቸውን ያስፈጨው ሂትለር ያለቅጣት በይቅርታ ይታለፉ፣ የሰረቀ እና ከድኋው በክፋት የነጠቀ፣ ወንድሙ የዕለት እንጀራ አጥቶ እየተቸገር ለብዙ ዓመት የሚያጠራቅመውን ለዛውም በእውነት እና በሀቅ ባልሆነ መንገድ ሲሞትም ደስታ እና ሀሴት ይጠብቀው” እያልን እንዳልሆነ አምናለሁ። ይልቁንስ እያልን ያለነው “የኃጢአት ዘመኑን የሚመጥን ቅጣት ይጠብቀው ነው።” ፍትሐዊ አባባል ነው።



የመጀመሪያው ጌታችን ወደ ቅፍርናሆም እና ቤተሳይዳ እያመለከተ ፥ ፍቅሩ እና የማዳን ሥራው እንደ ጊዮን ውሃ የፈሰሰላቸው እነዚህ ከተሞች ነገር ግን ጌታቸውን ያገለሉ እና ችላ ያሉ በፍርድ ቀን ከጢሮስ፣ ከሰዶም እና ከገሞራ ይልቅ የበለጠ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ነገሮናል። (ማቴ 10፥15፣ ማቴ 11፥22)። ምክንያቱም ሰዶም እና ገሞራ ለሰሩት ኃጢአት ፍርድን ወዲያው በምድር ላይ ተቀብለዋልና፣ በዘላለም ፍርድ ፍትሐዊው ፈራጃችን ያን እንደሚያስብላቸው ነገሮናል። በዚህም የቅጣት ፍርዱ ለሁሉም እኩል እንዳልሆነ አሳወቀን። ያነሰ ፍርድ የሚቀበሉ እንዳሉ ነግሮናል። የዘላለም የገሀነምን እሳት እንዳለ በቅጣት የሚቀበሉም እንዳሉ እንዲሁ። ከእነሱም ዋነኞቹ የመዳን ወንጌሉ ተሰብኮላቸው ፥ የፍቅሩ ተዓምር ተደርጎላቸው ያገለሉት ትልቁን ፍርድ እንደሚቀበሉ ነው የነገረን። ስለዚህ ፍርዱ በሚዛን እንደሚሆን ገልጦልናል። ያ ሚዛን ግን የእሱ ስለሆነ አሁን ላይ ምን እንደሚመስል ከዚህ በጠለቀ ሁኔታ አልተገለጸልንም። ይሄም ለእኛ ስለማይጠቅመን እንደሆነ አምናለሁ። ግን ትልቁን ጥያቄ መልሶልናል። ያም የቅጣቱ ፍርዱ እንደሚለያይ። እዚህ ጋር አንድ ማስመር የምፈልገው ጌታችን ከብሉይ ኪዳን በአሉታዊ መንገድ የጠቀሳት ብቸኛዋ ሴትን ነው። እሷም የሎጥ ሚስት ናት።(ሉቃ 17፥32)። ጌታችን ወደ ሐዋርያት ዞሮ የሎጥን ሚስት አስቧት ብሏቸዋል። ያቺ ከታላቁ የእምነት አባት አብርሃም ዘር የመቆጠርን ዕድል ያገኘችው፣ መላዕክት እጇን ይዘው የእሳትን ባህር የሚያሿግራት የሎጥ ሚስት። በመጨረሻም ፊትለፊቷ ካለው የጽድቅ ተራራ ይልቅ የሰዶም ውበት ትዝታ የሳባት እና ወደኋላ የዞረችው የሎጥ ሚስት። ይህችን ሴት ጌታ በተለየ ሁኔታ እንድናስባት አሳስቦናል። ጌታችን ይሄን ለሐዋርያት ነው የተናገረው። በዛ የፍርድ ቀን ለእናንተ ይብስባችኋል ሲል።



ሁለተኛው ጥያቄ የዘላለም ቅጣት ጉዳይ ነው። በዚህ ምድር ያለ የፍትሕ ፍርድ ቤት እንዴት እንደሚፈርድ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ለምሳሌ አንድ ሰው ተናዶ ወደ ቤቱ ሲመጣ ሚስቱ እና ልጆቹ የበለጠ ቢያናዱት እና በዛ የአንድ ደቂቃ ደም ፍላት ምክንያት ሽጉጡን አውጥቶ ሚስቱን እና ልጆቹን ቢገድል ፥ ይሄ ሰውዬ የሚጠብቀው ፍርድ ምን እንደሆነ አስባችኋል? ፍርድ ቤቱ የአንድ ደቂቃ የደም ፍላት ችግር ነው ብሎ እድሜ ልክ ከመፍረድ የሚቆጠብ ይመስላችኋል? የአንድ ደቂቃ ስህተት መሆኑ ለዛ ወንጀል የሚገባውን የእድሜ ልክ ፍርድ ከማሰጠት ያድነዋል? ብዙ ወንጀሎችስ በእውነት ቅጣታቸው ወንጀሉ ከተደረገበት የእድሜ ዘመን በላይ እንደሆነ አስባችሁ አታውቁምን? እነዚህ ቅጣቶች መቼ የፍትሕ ጥያቄ ይነሳባችኋል? ከወንጀል ድርጊቱስ በላይ የምንቀጣው የሰውዬውን የመግደል ፍላጎት እና የአዕምሮ ሁኔታ አይደለምን? ለመግደል ያነሳሳውን ፍላጎት እና ሁኔታ አይደለም ታሳቢ የምናደርገው? ለዛስ አይደለ ሰው የገደለ ሁሉ እኩል ቅጣት የማይከተልበት? ለምሳሌ በጦርነት ያለ ወታደር ምንም ሰው ቢገድል፤ ከአሸናፊው ወገን በመጨረሻ ከሆነ እንደ ገዳይ ሳይሆን እንደ ጀግና እና መልካም ሰው የምናየው የምንቀጣው ተግባሮችን ሳይሆን በዋነኝነት እነዛ ተግባሮች የቆሙበትን ፍላጎት፣ የማህበረሰብ ቀጣይ አኗኗር እና የሌሎች ሰዎችን ባህሪ እና መጠበቅ ታሳቢ በማድረግ አይደለምን? ይሄ የሚያሳየን ቅጣት ወንጀለኛው ለሠራው ክፋት ብቻ ሳይሆን፣ ሌላውንስ ከመውደድ፣ ማለትም በወንጀለኛው ክፋት የተጎዱትን እና የሚጎዱትን በማሰብም ጭምር እንደሆነ እንዴት እንዘነጋለን?



እግዚአብሔር ፍቅር ነው ብለን፣ ሁሉን ያለፍርድ የሚያልፍ፣ በፍቅሩ ታምነው ቃሉን ለጠበቁት ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም በእርሱ እቅፍ የሚሰበስብ ከሆነ ... አምላካችን ስለዘላለማዊ ቅጣት የተናገረውን የእውነት ቃል አምነው፣ የዚህ ምድርን ጊዜያው ጥቅም እንደጉዳት የወሰዱ ሰዎችን ወዴት እናድርጋቸው? መከራን ስለመንግስቱ ሲሉ የተቀበሉትን ፥ መከራቸውስ ስለከንቱ ነውን?



ሰነፉን ተማሪ እና እንቅልፍ አጥቶ ያጠናውን ተማሪ ስለፍቅር ብሎ እኩል የሚሸልም እና የሚያሳልፍ መምህር ከሁሉ በላይ የጎዳው ፍቅርን አይደለምን? ምክንያቱም ፍቅሩን ከምር የወሰደው ተማሪ ሲጎዳ ፥ እርሱን ያላመነው ግን አላማመኑ እውነት እንደነበረ በውስጡ የተጠራጠረው ልክ አልነበረምን? የትኛውስ ፍቅር ያለፍትሕ ይቆማል? የትኛውስ ፍቅር ያለእምነት (እውነት) ይጸናል?



ብዙ የሚያጠራጥር ነገር በሞላበት ዓለም ውስጥ እየኖሩ፣ ለብዙ ጥያቄዎቻቸው መልስ ሳያገኙ፣ እሱን ግን አምነው ቃሉን የጠበቁት በከንቱ ነበርን? በእነሱ ላይ ያሾፉት እና በደካማው እና ምስኪኑ ላይ ፍርድን ያዛቡት፣ “የእናንተ እግዚአብሔር ቢኖር ይሄ ሁሉ ይፈጸማልን?” እያሉ ከደካማው ነጥቀው የሞላውን ጎተራቸውን የጠቀጠቁትን ፥ “እኔ ፍቅር ነኝ” በሚል ብቻ በመንግስቱ ስለእርሱ ሁሉን እያጡ መከራ ከተቀበሉት ጋር ከደመራቸው ፥ በዚህ ፍርድ አሸናፊው ማነው? ከእግዚአብሔርም ሆነ ከጻድቃን በላይ የዚህ የፍጻሜ ፍርድ አሸናፊዎች የክፋት ሰዎች አይደሉምን?



ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔር አይዘበትበትም፣ ሰው ሁሉ የዘራውን ያጭዳል” ያለው ውሸቱን ነበርን?። (ገላ 6፥8)። ይሄንንስ አምነው መልካም ዘር የዘሩት፣ እግዚአብሔር ላይ ያልዘበቱት፣ ክርስቶስ በፍጻሜ ፍርዱ የዘላለም እሳት አለ ያልኳቹ “ውሸቴን ነው ወይም ትቼዋለሁ፣ እኔ ፍቅር ሆኜ ሳለ ሰውን በገሀነም እሳት እንደኃጢአቱ መጠን ላቃጥል አይገባኝም፤ ስለዚህ ሁላቹሁ የአባቴ ወገን ናችሁና ኑ” ቢል፤ እነዚህ ስለእርሱ ሁሉን ያጡት ስለፍቅሩ ምን ይሰማቸው? ይሄ ፍቅርስ ከእነሱ ይልቅ ለኃጢአተኞች አይደለምንም? ሰነፍ ተማሪዎች መውደቃቸውን አይቶ፤ የጎበዞቹን ልፋት እንደምንም ሳይቆጥር ፈተናው ተሰርዟል ሁላችሁም አልፋችኋል የሚል መምህር፣ ከሁሉም በላይ ፍትሕ የማያውቅ፣ ፍቅሩ ለሰነፎች ያደላ አይደለምን? ፍቅሩስ ለሁሉ ቢሆን መጀመሪያ ያን ለሁሉ አይነግርምን? ይሄ አድሎ ደግሞ በእግዚአብሔር ሲሆን የበለጠ እንደሆነ እንዴት ይጠፋናል፤ ምክንያቱም መምህሩ አስቀድሞ ያን ያላለው ይሄን ያህል ተማሪ እንደሚወድቅ ስለማያውቅ ነው ብለን ልንምረው እንችላለን፤ አላዋቂነቱን አስበን፤ እግዚአብሔር ግን ሁሉን እያወቀ፣ ፍጻሜውን እያወቀ፣ አስቀድሞ ያን ከተናገረ ውሸት ተናግሯል ማለት ነው፤ ለማታለል፣ ሙሉ ለሙሉ ሰዎች ክፍዎች እንዳይሆኑ ሕጻን ልጅን በከረሜላ እንደሚደልሉት፣ የእሱን ፍቅር ያመኑትን ደልሏል ማለት ነው!?



ይሄ ከእኛ ይራቅ። እርሱ በባህሪው ንጹሁ ነው። ውሸት ከእርሱ ጋር ፈጽሞ ሕብረት የለውም። ለቃሉም ተማኝ ነው። አዳምን ያን ፍሬ ከበላክ ትሞታለህ ብሎታል፤ በዚህም አራራለትም። ሞትን ለዘላለም አስጎነጨው እንጂ። የእጁ ሥራ ቢሆን እንኳ፤ እርሱ ለቃሉ ታማኝ ስለነበረ፣ ከገነት አባረረው። ወደ ሞት ዓለም ጣለው። ሊምረው ሲያዝንለት እንኳ ቃሉን ሳይሽረው አደረገው። ምህረቱ ፍርዱን አላሸነፈውም። ፍርዱም ምህረቱን አላጠፋውም። የትኛውም ኃጢአት ያለቅጣት እንደማያልፍ ነገረን እንጂ። በገሀነም የማይቀጣ ኃጢአት ካለ፣ ያ ኃጢአት በመስቀሉ በቀራንዮ ተቸንክሯል ማለት ነው። “የሞት ሞት ትሞታለህ ቃሌን የሻርክ ቀን” ላለው ቃሉ አንድያ ልጁን ኃጢአት አደረገው። (2ኛ ቆሮ 5፥21)። በዚህም በክርስቶስ ኢየሱስ የማይምኑት ሁሉ፣ ከልጁ ሞት ጋር አልተባበሩም እና የኃጢአት ደሞዝን ይቀበላሉ። በእርሱ ጭካኔ ግን አይደለም፣ በወላጆቻቸውም በደል አይደለም፣ በራሳቸው ኃጢአት እንጂ። እርሱማ አዳምን ለዘላለም ሞት ቢጥለው ያ ጭካኔው ሳይሆን ቃሉ እና ፍርዱ ነበር። አትብላ ብሎታል። በላ። ስለዚህ ሞተ። ማንም ባያድነን የሚከሰው የለም። ግዴታ የለበትም እና። ቃሉ እና ሕጉን ነው የፈጸመው። ነገር ግን እንዲሁ ወዶናልና፣ የእጆቹን ውብ ሥራ ለሞት ይተወው ዘንድ ፍቅሩ እና ክብሩ አልፈቀደሉትም። ቃሉን ይሽር ዘንድ ደግሞ እርሱ አይለዋወጥም። ስለዚህ ያን ሞት እርሱ ተሸከመ።



ቀንበሩ ከባድ የሆነን እቃ አጎንብሰን፣ ዝቅ ብለን ትከሻችን ላይ እንደምንጭነው፣ ከዛም ቀና ብለን፣ አሁን በትከሻችን ላይ ያለውን ያ መሬት ተቀምጦ የነበረውን ከራሳችን ጋር እንደምናነሳው፤ በቃሉ ሸክም መሬት የወደቀውን ለማንሳት ዝቅ አለ፣ በትከሻው ላይ በአባቱ ፈቃድ አኖረው፣ ከራሱ ጋር ያን መሬት የወደቀውን ይዞት ተነሳ። እርሱ ወዳለበት ቦታም ወሰደው። ፍርዱን ሳይሽር ፍቅር መሆኑን ገለጠልን። ራሱን ከወደቅነው በታች አድርጎ፣ በፍቅር ትከሻው ይዞን ተነሣ። በዚህም ፍቅሩ ካለ ፍርዱ ሙሉ እንደማይሆን በኛ በሰዎች የዕለት ሕይወት ውስጥ የተገለጠውን እውነት የበለጠ አሳየን።


513 views0 comments

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page