top of page
Search

ዳንኤል ክብረት እንደሴኒካ

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew

Updated: Aug 7, 2024




ይሄ ጽሑፍ የዳንኤል ክብረትን ስም እና ክብር ለማጠልሸት ያለመ አያደለም። ምክንያቱም በሩቅ ዳንኤልን ከሚያዩት በተሻለ የማውቀው የለኝም። በእርግጥ በቤተክርስቲያን ጥቂት አውቀዋለኹ (ሁለቴ ሦስቴ አራት እና አምስት ሰዎች ባሉበት ቁጭ ብዬ አውርቼዋለኹ)። በቅርብ የሚያውቁትን ሰዎች ስለባሕርይው ከመጠየቅ እና ከዚያ ከሚመነጭ መረዳት በቀር አሁን ምን እያደረገ እንደሆነ ከግምት ትንሽ ከሚሻገር ዕውቀት የዘለለ የለኝም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካሪ ከሆነ በኋላ የሰጣቸውን ንግግሮች እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ያስተላለፋቸውን መልእክቶች ተከታትያለኹ። ያ ስለሚሠራው እና ስለሚያስበው የሚሰጠው ብዙ መረጃዎች አሉ። ከዚያ በዘለለ በቅርብ አግኝቶ ያናገራቸው ወዳጆቼ እና ለእኔ የነገሩኝ እንደ የስማ በለው መረጃ በሆነ መጠን ከማውቃቸው ጋር በማገናዘብ እዚህ ድምዳሜ ላይ አድርሶኛል። ስለዚህ ብዙ የማላውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አንባቢ እንዲረዳ እጠይቃለኹ።


የአገር አቀፍ ምርጫው እንደተካሄደ እና የትግራዩ ጦርነት በጋለ ሰዓት ክቡር ገና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰራጨው አንድ ጽሑፍ ዐቢይ አህመድን ከሮሙ ንጉሥ ኒሮ ጋር አቻ አድርጎ አስቀምጦት ነበር።


በ17 ዓመቱ ሥልጣን የያዘው ኒሮ ዕድሜው ቢጨምርም ሳይበስል የቀረ እና በ30 ዓመቱ ራሱን በማጥፋት የሞተ የመጀመሪያው የሮም ንጉሥ ነበር።


ኔሮ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በጣም ደግ እና በከፍተኛ ሁኔታ በባህል፣ በአርት እና ቅርጻ ቅርጽ ላይ በማተኮር በሮም ውስጥ የነበሩትን ታዋቂ ሰዎች (ሴለብሪቲ) ወዲያው ማማለል የቻለ ነበር። ወዲያው ግን መካሪዎቹን መስማት በመተው ያ ያለተገራ ጨካኝ ማንነቱን መግለጽ ጀመረ። በዚህም እናቱን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን በግፍ ገደለ።


በዘመኑ ሮም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ስቃይ ውስጥ ከመግባቷ በላይ ከጨካኙ እና አንደበተ ኮልታፋ ከነበረው፣ ኔሮ ከተካው ካላውዲዎስ በላይ የወጣለት አምባገነን ሆነ። በዚህም በ64 ዓ.ም ሮምን በእሳት በማቃጠል በክርስቲያኖች ላይ አሳቦ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ጨረሰ።


ኔሮ በጣም አባካኝ በመሆኑ እና በአላስፈላጊ የከተማ ሕንፃዎች የሮምን ካዝና በማራቆቱ ይሄን ለማካካስ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ጣለ። በተመሳሳይ ድግስ መደገስ፣ የሰረገላ ውድድር፣ ዳንስ እና የዘፈን ትርኢቶችን ማዘጋጀት በጣም ስለሚወድ የሮም ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎዳ። በአማካሪው ሴኒካ ጭምር የመግደል ሙከራ ቢቀነባበርበትም ከነዚህ ተርፎ ሴኒካንም አስገደለ። ሲገድል ደግሞ ራሱ ሳይሆን የሚገድለው ተገዳዩ ሰው ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ ነው የሚያደርገው። በመጨረሻም ሁሉም የዘራውን ያንኑ ያጭዳል’ና ኔሮ በገዛ እጁ ራሱን እንዲገድል ተደርጎ ከሥልጣን ተወገደ።


ስለኔሮ በተጻፈው ቦታ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ስም ብትከቱ ሁሉም ልክ ነው። ስለኔሮ ጉግል ብታደርጉ እኔ እዚህ የጠቀስኩትን ሁሉንም ነገር ልክ ሆኖ ታገኙታላችኹ። ምንአልባትም ልክ ከልጅነት አስተሳሰብ ሳያድግ አንድጎለመሰው፣ ከዛም ከስልጣን እንደተወገደው ኔሮ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይንም ወዳጆቹ አቡሽ፣ አቡሹ የሚሉት ይሄን ማንነቱን በማሰብ ይሆናል።


ስለኔሮ ሲጠቀስ ግን ሴኒካን አለማንሳት ፈጽሞ አይቻልም። ሴኒካ እነ ታላቁ ጎርጎርዮስ እና ቅዱስ አውግስጢን ጽሑፉን አንብበው ከእኛ እንደ አንዱ የሆነ ክርስቲያን ነው ያሉለት ነበር። ሴኒካ ግን በጣም የተወሳሰበ ማንነት ያለው ሰው ነው። በዚህ ዓለም ሲኖር የሶቅራጦስን ዓይነት ኑሮ ለመኖር የሚመኝ ሰው ሁሉ የሴኒካን መጻሕፍት ማንበብ ይኖርበታል። ምክንያቱም ሴኒካ እንዴት ልዕልና ያለው ኑሮ መኖር እንደሚቻል የጻፈ፣ ብዙ መጻሕፍትን በተለያዩ የስቶይክ ዘርፎች ያበረከት፣ በንግግር እና በጽሑፍ ችሎታው የተደነቀ ሰው ነበር። ሴኒካ ስለትዳር፣ ስለዝሙት፣ ስለልጆች አስተዳደግ፣ ስለልግስና፣ ስለእኩልነት እና ሌሎች ማኅበራዊ እና ግብረገባዊ ጉዳዮች የጻፈውን አንብቦ ቅዱስ ነው የማይለው ላይኖር ይችላል። እኔም ከሴኒካ ጽሑፎች ብዙ ተምሬያለኹ። ነገር ግን ሴኒካ ግለሰባዊ ሕይወቱ በአደባባይ ከሚገልጸው ለጓደኞቹ ሳይቀር ከሚናገረው በጣም የራቀ ነበር። ለእናቱ ሳይቀር በሀዘኗ ወቅት የሚጽፈው ደብዳቤዎች አንድ ቀን ለአደባባይ ሊበቁ ይችላሉ ብሎ በማሰብ ነበር የሚከሽናቸው፤ ለዚህ ነው የሴኒካን እውነተኛ ማንነት ለማወቅ ጊዜ የፈጀው።


ሴኔካ ራሱን በዘመኑ በነበሩ የንግግር እና የፕሎቶኒክ ትምህርቶች ያስተማረ በጣም የተካነ ሰው ነበር። በዚህም ነው የላይኛው የማኅበረሰብ ክፍል አባል ባይሆንም ለፐብሊክ ተከሽነው በቀረቡ ጽሑፎቹ እና ንግግሮቹ ወደ ሮም ቤተመንግሥት መዝለቅ የቻለው። በካሊጉሏ ጊዜ በዝሙት ምክንያት ግብፅ ተወስዶ የታሠረ ነበር። ከመታሠሩ በፊት ግን ሰው ከሚስቱ ውጪ መሄድ እንደሌለበት የሚያትቱ ጽሑፎችን በጠንካራ ፍልስፍናዎች አስረግጦ ጽፎ ነበር። በግብፅ በአክስቱ ምክንያት የነበረበት ሁኔታ ብዙ ምቾት ያለበት ቢሆንም እንዲታዘንለት ግን መከራ እንዴት የሰውን ልጆች ባሕርይ እንደሚያንጽ እና ያም እርሱን እንዴት ከፍ ላለ ሞራላዊ ሕይወት እንዳበቃው በሮም ላሉ ጓደኞቹ ይጽፍላቸው ነበር። ደብዳቤዎቹም ድንገት በንጉሡ እጅ ከገባ ብሎ አረመኔውን ሥርዓት በማሞገስ የተሞሉ ነበሩ። ይሄም እንዲፈታ እና ወደሮም ተመልሶ የአግሪፒና ልጅ (በሰዓቱ ስምንት ዓመቱ ነበር) ኔሮ አስተማሪ እንዲሆን ዕድልን አገኘ። በእርግጥ ከከላውዲዎስ ሚስት አግሪፒና ጋር የቆየ የዝሙት ግንኙነት ስላላቸው ነበር አግሪፒና ወደ ሮም ያስመጣችው ይባላል። በዚህም የወደፊቱ አረመኔውን ንጉሥ ኔሮ የንግግር አስተማሪ ሆነ። በዚህ ወቅት ነበር በጥበብ ታማኝ ወዳጆቹን ቤተመንግሥት አካባቢ መሰግሰግ የጀመረው።


ኔሮ 17 ዓመት ሲሞላው ሴኒካ አግሪፒናን በድብቅ በመምከር ከላውዲዎስ እንዲመረዝ አደረገ። በተለይ የቤተመንግሥት ወታደሮች ጠባቂ ከነበረው ‘በረስ’ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ስለነበረው ኔሮን የሚቀናቀነው እና ሕጋዊ ወራሽ የነበረውን ቢሪታኒከስን ከቤተመንግሥት በማሸሽ ኔሮ ሥልጣን እንዲይዝ ተደረገ። ኔሮን ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ በማሠልጠን የእርሱ ጥገኛ እንዲሆን ስላደረገው ሥልጣኑን ከጀርባ እቆጣጠራለኹ ብሎ አስቦ ነበር። በዚህም የኔሮንን የንግግር ብቃት እንጂ የማሰብ እና የማስተዳደር አቅም እንዳይዳብር ሆን ብሎ የእነዚህን ጥበቦች እንዳላስተማረው የታሪክ ጸሓፍት ይናገራሉ። ኔሮ በማኅበረሰቡ ወዲያው ተቀባይነት እንዲኖረው እና በሚናገራቸው እና በሚጽፋቸው ጽሑፎች የሮምን የገዢ መደብ እና በከላውዲዎስ የተማረረውን ሕዝብ ለመማረክ ሴኒካ ትልቅ ድርሻ ነበረው።


ነገር ግን ሰዎችን ከጀርባ የምንቆጣጠርበት ገደብ አለው። ሰው ሁልጊዜ ሰው ነው። ያምጻል። ኔሮ ከሴኒካ ውጪ ምክር መስማት ጀመረ። በዚህም የሴኒካንን ተጽዕኖ ያልወደዱ ሰዎች ሴኒካ ከቤተመንግሥት እንዲባረር ኔሮን አሳመኑት። በተለይ ሴኒካ ስለገንዘብ ከንቱነት እና ቁሳዊ መሆን እንደሌለብን የስቶይክን ፍልስፍና እያስተማረ በጎን ግን በሰዓቱ ቢሊየነር የሚባል የሀብት ደረጃ መድረሱ ብዙዎችን አበሳጨ። አስመሳይ እና አድርባይ በሚል እንዲጠላ ምክንያት ሆነ። በተለይ በዙሪያው ያሉት ሰዎች በሁለት ዓይነት ስብዕናው በመናደድ ፥ ከፊሎቹ ደግሞ በቅናት በማበር ከቤተመንግስት እንዲባረረ ምክንያት ሆነ። ኔሮም እብድነቱ በዝቶ እናቱን ጭምር ገደለ።


ሴኔካም በግዞት እያለ ቤተመንግሥት ውስጥ ከነበሩ ወዳጆቹ ጋር ሆኖ ሴራ ሲሰርብ ተገኝቶ ራሱን እንዲያጠፋ አስገደደው። ዘመኑን ሁሉ በሰዓቱ ለሮም ትልቅ ሞዴል የነበረውን ሶቅራጥስን ለመሆን ሲጥር ስለነበረ ሞቱንም ከሶቅራጥስ ጋር ለማመሳሰል ጥረት አደረገ። ልክ ሶቅራጥስ ወዳጆቹ ከበውት እንደሞተ ፥ ሴኒካም ወዳጆቹን ሁሉ ጠራ። መጀመሪያ ሶቅራጥስ እንዳደረገው ሄምሎክ የሚባለውን መርዝ ጠጣ። (ሶቅራጥስ መርዙን እንደጠጣ ወዲያው ሰውነቱን ዘርግቶ ነበር የሞተው)። መርዙ ግን ሴኒካን ሊገድለው አልቻለም። ከዚያ የደም ሥሩን ቆርጦ ራሱን ለመግደል ጣረ። አሁንም ሞት የለም። በመጨረሻም ደሙን እያንጠባጠበ በመታጠቢያ ቤት በመግባት በእንፋሎት ታፍኖ ሞተ። ይሄን የሴኒካን ስቃይ የሞላበት አሟሟት በቦታው በመገኘት የጻፈው በሰዓቱ ታዋቂ የታሪክ ጸሓፊ የነበረው ኮርኒለስ ታኪተስ ነበር። ሴኒካ ልክ እንደ ሶቅራጥስ መርዙን ከመጠጣቱ በፊት ረዥም ንግግር ቢያደርግም ታኪተስ ግን ይሄን ንግግር ለታሪክ ላለማስቀመጥ ወሰነ። ምክንያቱም ሶቅራጥስ አንድም ነገር የማኅበረሰብ ምስሉን (public image) ለመቅረጽ የሠራው ነገር አልነበረም። ተከታዮቹ እነ ፕላቶ በኋላ ላይ ንግግሩን በጽሑፍ አስቀሩለት እንጂ አንድም ጽሑፍም ሆነ መጽሐፍ አልከተበም። ይሄንንም ከትሕትና አንጻር ነበር ያደረገው። ሲሞት የተናገረውንም ተዘጋጅቶበት ያደረገው ሳይሆን ሊያስመልጡት ለመጡ ወዳጆቹ የተፈረደበትን ፍርድ መቀበል እንዴት ተገቢ እንደሆነ እና እውነተኛ ፈላስፋ ለመሞት እና ወደ አምላኩ ለመሄድ የሚፈጥን እንጂ ከሞት የሚያመልጥ እንዳልሆነ ለማስረዳ የተናገረው ነበር። (“Phaedo” በሚለው መጽሐፍ ፕላቶ እንደከተበው። በነገራችን ላይ ይሄን መጽሐፍ ያነበቡ ብዙ ሰዎች በሶቅራጥስ “ሞት ከሕይወት የተሻለ እንደሆነ” ባስረዳበት ክርክር በማመን ራሳቸውን አጥፍተዋል)።


ሴኒካ ግን ሆን ብሎ ማኅበራዊ ምስሉን ለመቅረጽ የጣረ የውሸት ሶቅራጥስ (pseudo-socrates)) ነው በማለት ነው ታኪተስ ንግግሩን ለታሪክ ከማስቀመጥ የተቆጠበው። በዚህም የሴኒካ የመጨረሻ ንግግር እስከዛሬም ምን እንደሆነ አይታወቅም።


ዳንኤል ክብረት እንደሴኒካ ነው ስል ምን ማለቴ ነው? ብዙ ሰዎች ዳንኤልን በስብከቶቹ እና የዳንኤል ዕይታ በሚለው ነው የሚያውቁት። ዳንኤል ከብዙ የሃይማኖት መምህራን የሚለየው እና ከሴኒካ ጋር የሚያመሳስለው ማኅበረሰቡን በሞራል ለመቅረጽ ባለሙ ምልከታዎቹ እና ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ጉዳዮችን በተረት፣ በሚይቶሎጂ፣ በታሪክ እያዋዛ የማቅረብ ብቃቱ፣ ራሱን በንባብ ያስተማረ መሆኑ፤ እንደሴኒካ ከክፍ አገዛዞች ጋር ላለመጣላት የሚሄድበት የጥንቃቄ መንገዶች፣ በተለይ በቀደመው የሕወኃት ዘመን በሥርዓቱ ውስጥ ላሉ ሰዎች ብዙ ያልቆረቆራቸው መሆኑ ትልልቁ ማሳያዎቹ ናቸው።


ዳንኤል ለውጡ ሲመጣ ወደ ቤተመንግሥት ገባ። ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ተስፋ መሆኑን ሰበከን። ከዚያ በተጨማሪም “ዐቢይ አምባሳደር አድርጎ ሊሾሞው ፈልጎ ሲጠይቀው እንቢ እንዳለው እና የእርሱ ግብ ሌላ እንደሆነ” በሚዲያ በመንገር ለኦርቶዶክስ አማኙ "ቤተመንግሥት ውስጥ ዳንኤል አለ" በሚል መንፈስ እንዲኖር ረድቷል (በናቡከደነጾር ቤተመንግሥት ዳንኤል ስለእስራኤል እንደነበረው፣ አስቂጭ ክፍሉ ዳንኤል ይሄን ታሪክ ተርጉሞ በመጽሐፍ አሳትሟል)። ዳንኤል ግን አገራችን ከፍተኛ መከራ በገጠማት ሰዓት ወጥቶ ለሕዝብ የሚናገራቸው ንግግሮቹ፣ አስደንገጭ አጫጭር የማህበራዊ ሚዲያ መልዕክቶቹ እና ከፍተኛ የሃይማኖት ሥነ ምግባር እና የሞራል ልዕልና የታየባቸው ጽሑፎቹ ለየቅል ነበሩ። ፖለቲከኞች እንኳ ሊናገሩት የማይደፍሩትን ሕዝብን የማይመጥን እና የመዝለፍ ንግግሮች ሰምተናል። አሁንም እያነበብን ነው።


ቤተክርስቲያኒቷን የሚከፍል እንቅስቃሴ በመንግስት ጠንሳሽነት በእነ ብፁዑ አቡነ ሳዊሮስ መሪነት ሲጀመር ፥ ቤተክርስቲያኒቷ በይፋ ከገለጠችው አቋም በተቃራኒው ትደራደር የሚል መመሪያ በማኅበራዊ ድረገጽ አስተላለፈ። በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሰላማዊ አመጽ ቤተክርስቲያኒቷ መንግሥትን ስታስገድድ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካባቸውን ቀይረው አስታራቂ ሆነው ሲመጡ ፥ “የሰበክኹትን እና ያስተማርኹትን ክርስቶስን አየኹት” በማለት የእርሱ ሚና በዚህ ሰላም መምጣት ውስጥ እንዳለበት የሚያሳይ ነገር ጻፈ። በነጋታው ግን መንግሥት ድጋሚ አመነታ። ትግሉ ሊቀጥል እንደሚችል መንግሥት ሲሰጋ ነው መጨረሻ ላይ ነገሮች የተገለበጡት እንጂ ዳንኤል ሊነግረን እንደፈለገው የሱ ሥራ ውጤት አልነበረም። (በእውነት እርሱ የክፋት ቃል አቀባይ ከመሆን የዘለለ ተፅዕኖ ቢኖረው የትግራይ አባቶች ቤተክርስቲያኒቷን ከመክፈላቸው በፊት መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ያን ሁሉ ተማጽኖ ቤተክርስቲያን ስታደርግ ድምጿን እንደአስቴር ባሰማላት ነበር።)


ከዚያ በኋላም በሀገራችን የተከሰቱ መከራዎች አይደለም እንደ ዳንኤል በግብረገብ አስተማሪነት እና በሃይማኖት ሰባኪነት የሚታወቅ ይቅርና ሙሉ ለሙሉ ከሕሊናው ጋር ያልተጣላ ሰው ሥርዓቱን ከምታካሂዱት አደገኛ እና ከድሮ የከፋ ዋልጌነት እና አረመኔነት ተመለሱ በሚልበት ሰዓት ዳንኤል ግን የሥርዓቱን ክፉ መልክ ለሕዝቡ በማሳመር እንደተጠመደ ነው። ይሄን ነው ዳንኤል ልክ እንደሴኒካ ነው ያልኩት። ልክ ሴኒካ ስለዝሙት ሞራላዊ ዝቅጠት እና ሰው ከሚስቱ ሳይቀር ያለው የግንኙነት መጠን ሥርዓት የጠበቀ መሆን አለበት እያለ በሚሰብክበት እንደበቱ እሱ ከተማሪው እናት ጋር እንደሚዘሙተው ፥ ዳንኤል ክብረትም ግብጽን ከረሀብ መዓት የጠበቀውን የፈርዖን አማካሪ የዮሴፍን ታሪክ ተርጉሞልን ከቤተመንግስት ይለቅልናል። የዳንኤል ፈርዖን ግን ሀገራችንን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስድ ነው።ቁሳዊነት እንዴት የሰውን ልጅ ነፍስ አፍኖ፣ ስብዕናውን እንደሚያሳጣው ሴኒካ እየሰበከ በጎን ግን እሱ ሚሊዮን ገንዘቦችን የቤተመንግስት ቅርበቱን ተጠቅሞ ያከማች ነበር። የዳንኤልም ትላንት የጻፋቸው ጹሁፎቹ እና ስብከቶቹን አይቶ የዛሬውን ዳንኤል ለሚያይ ሰው ያስደንግጣል። የሰው ልጅ በዚህ ደረጃ ከራሱ ጋር እንደሚጣላ እና ራሱን በዚህ መጠን መቃራን እንደሚችል ማየት በራሱ አስፈሪ ነው።


በእርግጥ ሴኒካ የተናገረውን ባይኖር እንኳ የሞራል አስተምሮቱ እና ዕውቀቱ ከ2 ሺ ዘመናት በኋላ ሳይቀር ተከታዮች አፍርተውለታል። ዳንኤል በዚያ ደረጃ ያለሰው ነው እያልኹኝ አይደለም። ግን ከታሪክ የምንማረው ነገር ይኖራል። ሴኒካ እንዳለው “ወንጀል ወንጀለኛውን በመጨረሻ ይበላል፤ የማስመስል ካባም ይቀደዳል”። ሴኒካ ሶቅራጥስን ለማስመሰል ቢጥርም ሞት ሳይቀር የሶቅራጥስን ክብር ነፈገው። በተመሳሳይ ዳንኤል በናብከዶነጾር ቤተመንግሥት ያለ ዳንኤልን ለመምሰል ቢጥርም ቤተክርስቲያንም ሆነ አገራችን ከቀን ወደ ቀን በዐቢይ አህመድ ሥርዓት መከራ እና ስቃይ ብቻ የሚበዛባቸው ሆነዋል። ሴኒካ እንዳለው ወንጀል ወንጀለኛውን መጨረሻ ሳይበላው አይቀርም’ና ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል። ታሪክ የሚጻፈውም ሆነ የምንማረው ሰው መማር ስለሚችል ነው። ዐሥር ጊዜ ብልጣ ብልጥ ሆነን የግፍን ገፈት አንቀምስም ብለን ብናስብ ከሴኒካ በላይ ግን አስመሳይ እና ብልጥ፣ በፈጠረው በጎ ምስል ታላቁ ጎርጎርዮስን ሳይቀር ያታለለ ሰውን መሆን አንችልም። ይልቁስ እውነት ብቻ ነጻ ታወጣናለች። ለብዙ ጊዜ የማይካቬሊን፣ የሮበርት ግሪን መጽሐፎችን እና ታሊላርድ ዓይነት ሰዎች ታሪክን መስጦኝ አነብ ነበር። በመጨረሻ የነዚህ ሁሉ ሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወትም ሆነ ፍጻሜያቸው እጅግ ክፉ እንደነበር ነው የተማርኩት። (ወይም እኛ ከምንጠብቀው በላይ ሰዎቹ የጻፉትን የማይኖሩ፣ ይልቁስ መልካም ባህሪን መርሀቸው ያደረጉ ናቸው። ለምሳሌ ሮበርት ግሪን ሕይወቱ እና መጽሐፎቹ አይገናኙም።)


ምንኛ ጎበዝ አስመሳዮች እና አድርባዮች ብንሆን ከነዚህ ሰዎች በላይ አንሆንም። ግን ፈጽሞ የሰላም፣ የዕለት እንቅልፍም ሆነ ያማረ ፍጻሜ አይኖረንም። ሰውነታችን እና ተፈጥሯችን ሳይቀር ልክ እንደ ሴኒካ ያምጽብናል። ለዚህ ነው ለዳንኤልም የምመኘው እውነተኛውን ዳንኤል ለመምሰል እንዲጥር እንጂ የውሸት-ሶቅራጦስ (pseudo-Socrates) እንደተባለው እንደሴኒካ እንዳይሆን ምኞቴ ነው። ቢያንስ በትምህርቶቹ እና በምክሮቹ ተጠቃሚ የነበርን ሰዎች መዳኑን እንጂ የእርሱን መጥፎ አንመኝም።


 


 







 

 

 

147 views1 comment

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

1 Comment


yared kibrekidusan
yared kibrekidusan
Aug 17, 2024

በንቀትና በዝቅተኝነት ስሜት የተጻፈ እኔ ምንም እንኳን ለቤተክርስቲያን ባለበረክት በዚህ አጋጣሚ እንደምበልጥ ላሳይበት በሚል የተጻፈ ረብ የለሽ ጽሁፍ!

Like
  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page