top of page
Search

ፕሮፌሽናሊዝም

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew

 

ከዩኒቨርስቲ እንደወጣው የመጀመሪያ ሥራዬ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሕግ ክፍል ኢንተርንሽፕ ነበረ። ምንም ልምድ እና ተጋላጭነት (exposure) ሳይኖረኝ በአንዴ ወደ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የተቀላቀልኩበት ወቅት ነበር። በዚህም ዛሬ ሳስባቸው የሚያሸማቅቁኝ ብዙ ተግባሮችን አድርጌያለሁ። በአንድ ወቅት አንድ ባልደረባችን ኩኪሶች አምጥታ ጠረጴዛዋ ላይ አስቀመጠች። በጣም የምንግባባ ስለነበርን፤ ከተግባቦታችን አንጻር አንድ ኩኪስ አንስቼ በላው። ስትመጣ አንድ ኩኪስ ተነስቷል። “ማን ነው ያነሳው? አለች።  “እኔ ነኝ” አልኩኝ። አበደች። ያልተገባ ድርጊት እንደፈጸምኩኝ ተናገረች። እኔም እጅግ ብዙ ነገር ተማርኩ።

 

ዛሬ ላይ ስመለከት፣ በተለይ የሀገራችን ማህበረሰብ ከምዕራባውያን አንጻር ብዙ ለፕሮፌሽናሊዝም ያልተገቡ ባህሪዎች አሉን። ፍቅራችንን ለመግለጽ እና መቀራረባችንን ለማሳየት የምናደርጋቸው ነውር የሆኑ እጅግ ብዙ ተግባሮች አሉ። ሰዎች ሲያወሩ ይቅርታ ሳንጠይቅ፣ ሳናስፈቅድ ዘው ብሎ ስለእኛ ጉዳይ ማውራት በመንግስት መስሪያ ቤቶች የተለመዱተግባሮች ናቸው። ሰውን ያለአገግባብ መንካት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ፥ የሰዎችን ድንበር (private space) ሳያከብሩ ጉንጭን፣ ጺምን ማሻሸት የመሰሉ አጸያፊ ባህሪያት የፍቅር እና የመቀራረብ መገለጫ ሆነው ይታያሉ።

 

የሰውን ፈቃድ ሳይጠይቁ ቢሮ ውስጥ ዘው ብሎ መግባት፣ ሰዎች በስልጣን፣ በእርከን ወይም በደሞዝ ከኛ ስለሚያንሱ እንደ አገልጋዮቻችን ማየት፣ በኛ እና በእነሱ መካከል ያለው የግንኙነት ውል ፕሮፌሽናል ሥራችን መሆኑን ዘንግተን ፥ ፍጹም ክብር ያላቸውን ሰዎች የኛ አገልጋይ አድርጎ ማየት ይሄ በኛ የባህል ደም ሥር ውስጥ ያለ ይመስላል።

 

ቤተክርስቲያን ስትሄዱ ደግሞ ይሄ ባህል እንደ ኩራት ሆነው፣ ስልጡን ማህበረሰብ ያሉት የስነምግባር መገለጫዎች ጭራሽ አፈር ድሜ በልተው፣ አሳፋሪ ደረጃ ደርሶ ታዩታላችሁ። በአገራችን በብዙ ነገር ድንቅ ስልጣኔን ያስተዋወቀችው ቤተክርስቲያን ፥ ዛሬ ላይ ግን ራሷን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን ራሱ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ባህሎች ታቅፋ ታያላችሁ። በዕለተ ሰንበት ወደ ቤተክርስቲያን ሂዱ፣ እርስ በእርስ በክብር ስም ሲጠራሩ እና አንዱ አንዱን የዚህ ታላቅ ደብር፣ የዚህ ታላቅ ሀገረ ስብከት፣ የዚህ ታላቅ ጉባኤ መሪ፣ አባት እየተባባሉ ወይም ታላቁ ያቋቋም፣ ታላቁ ዝባዝንኬ ሲባባሉ ሰዓታችሁን በአግባቡ ከያዛችሁ ብዙ አልተሞጋገሱም  ወይም ሰላምታ አልተሰጣጡም ከተባለ ዝቅተኛው ግምሽ ሰዓት ነው የሚፈጀው። በዛ ላይ ምንም ነገር ሰዓት አይጠብቅም፣ ከጸሎታቱ እና ከቅዳሴው በቀር ምንም ነገር በመርሐ-ግብር እና ወጥ በሆነ መልኩ ሲካሄድ አታዩም።


ለምዕመናን ሰዓት፣ መንፈሳዊ ተመስጦ፣ እና ሰዎች ቤተክርስቲያን ሲመጡ እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉት ሥርዓት የተሞላበት ሂደት ምንም እውቀቱም የሌላቸው፣ ማህበረሰቡ ስላለበት ደረጃ እና የአናኗር ዘዬ መገንዘብ የማይፈልጉ ሰዎች ነው የተጠራቀሙበት።


ከዛ ካህናቶቹን እና አገልጋዮቹን ቀርባችሁ ስታዩ ደግሞ የእናንተን በጎ ፍቃድ በትህትና በመጠየቅ እና የራሳችሁ ሕይወት እና እቅድ ሊኖራችሁ እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ አቀራረብ ሳይሆን የምታዩት ፥ በመንፈሳዊ ማንነት የሰጣችዋቸውን ክብር እና ፍርሃት በዝብዞ ለመጠቀም የመፈለግ እና በድፍረት ያን የማድረግ ተግባርን ነው። የቅዱስ ጳውሎስ አንድ ምዕራፍ ብቻ የሆነውን ወደ ፊልሞና የተጻፈውን መልዕክት እባካችሁ አንብቡ። ቅዱስ ጳውሎስ እንደምን ባለ ትህትና እና ፍጹም በሆነ ሥነ-ምግብር ፊልሞና የተባለውን ምዕመን አናሲሞስ የተባለው ባሪያው ከድቶት ስለሄደ፤ ፊልሞና ይቅር እንዲለው እና እንዲቀበለው እጅግ በሚገርም ትህትና እና የፊልሞናን የመወሰን መብት ባከበረ መልኩ ሽማግሌው ጳውሎስ ይማጸናል። ወደ ጉዳዩ ከመግባቱ በፊት በዛ 25 ቁጥር ብቻ ባዘለ አንድ ምዕራፍ መልዕክት ውስጥ ጳውሎስ እስከ ቁጥር 10 ድረስ ፊልሞናን በማክበር፣ ስልጣን (autonomy) በራሱ ጉዳይ እንዳለው ግን ጳውሎስ በጌታ ሊያዘው እንደሚችል ፥ ከማዘዝ ይልቅ በፍቅር እሺ እንዲለው ሲማጸን ታዩታላችሁ። ይሄ ነው የክርስቲያኖች ሥነ ምግባር። ከቅዱስ ጳውሎስ የሚበልጥ በመካከላችን አለ ብለን መቼስ አናምንም። ታዲያ ይሄ ትህትና እና የሰውን ድንበር፣ ሰዓት፣ክብር፣ በራሱ ላይ የመወሰን ስልጣንን የማክበር ባህሪ ወዴት ራቀን?


 ሲ ኤስ ሉዊስ ሥርዓት ያለው ነገር ፈጽሞ የሰይጣን ሆኖ አያውቅም ይላል። "ሰይጣን ሥርዓት ያለው ሙዚቃ ሳይቀር ይረብሸዋል" ይላል ሉዊስ። ሥርዓት የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ ነው። እስኪ ሥርዓት የሌለው ግን ታላቅ ስልጣኔ የነበረ አንድ ጠቁሙን? ሥርዓት መደላደሉ ካልሆነ ያ ስልጣኔ ወይ በመፍረስ ላይ ያለ ነው ወይ ገና ወደ ሥልጣኔ መንበር እየተሸጋገረ መሆን አለበት።


እውነት ለመናገር ፕሮፌሽናሊዝምን ብናክልበት ሰዎች ፍቅራችንን እና ቅርበታችንን የበለጠ ያደንቁታል። በጣም የሚቀርበኝ እና በብዙ ነገር ከእኔ የሚበልጥ ወዳጅ አለኝ። ለመደወል ሲያስብ ግን ሁልጊዜ መጀመሪያ መልዕክት (text) ይልካል። አሁን ይመቸኝ እንደሆነ ጠይቆ፤ እሺ ካልኩት ብቻ ነው የሚደውለው። ከእኔ በላይ እጅግ በተጣበበ ሰዓት ውስጥ የሚኖር ቢሆንም ለእኔ ሰዓቶች ግን ከፍተኛ ክብር አለው። ለዚህ ወዳጄ ያለኝ ፍቅር እና ክብር በጣም ጨመረ እንጂ ይሄን በማድረጉ የራቀኝ ወይም መቀራረባችን የተጎዳ መስሎ አንድም ቀን ተሰምቶኝ አያውቅም።

 

በሕይወት፤ በየትኛውም የሕይወት ዘርፍ ቅርበታችን እና አጉል ፍቅራችን እንጂ ፕሮፌሽናሊዝም ለጠብ እና ለመቀያየም አይዳርገንም። ብዙ በአጉል መቀራረብ እና በአጉል ፍቅር የተጣሉ ሰዎችን አይቻለው፤ ፕሮፌሽናል የሆነ አክብሮት እና ሥርዓት በማሳየታቸው የተጣሉ እና የተቀያየሙ ሰዎች ግን እስከዛሬ አልገጠሙኝም።



 

430 views1 comment

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

1 Comment


Haiyleyesus Abayneh
Haiyleyesus Abayneh
Jun 13, 2024

ይገርማል። ነገሮችን በዚህ መልክ ይሁነኝ ብዬ ተመልክቼ አላውቅም። እኔ በምሰራበት አካባቢ ስለ ሰው የምናወራው ነገርና ለዛ ሰው ያለን ተግባራዊ አኪብሮ የዜሮ ብዜት ውጤት ነው የሆነቢኝ። አመሰግናለሁ።

Like
  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page